የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቅዱስ ቂርቆስ ሰማዕት

“እኔ ክርስቲያን ነኝ”

በኢትዮጵያ ፣ በቢዛንታየን ፣ በካቶሊክና በኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት የታወቁና ክብር የሚሰጣቸው ቅዱሳን ቂርቆስና ኢየሉጣ በዚህ ቀን ይታሰባሉ ፤ እነዚህ የ4ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታት በጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ትልቅ አርአያ ተደርገው ይወሰዳሉ ። ሕፃኑ ቂርቆስም ሠለስቱ ደቂቅን/ሦስቱን ወጣቶች የሚያስታውስ ሐዲስ ሰማዕት ነው ። ቅድስት ኢየሉጣ እግዚአብሔርን በመፍራት የኖረች ሴት ናት ። እግዚአብሔርን መፍራትዋ ከሰማይ ክብርን ሲያስገኝላት በምድር ግን ስደትን አምጥቶባታል ። እርስዋም ዋጋን ከምድር ሳትጠብቅ ከሞቀው ኑሮዋ ከሮም ከተማ ተሰደደች ። በስሜ ትሰደዳላችሁ ያለው ጌታ ቃሉ በእርስዋና በቤተሰብዋ ላይ ሲፈጸም በማየትዋ ዕድለኛ ነኝ ብላ ተደሰተች ። የቅዱሳን ደስታቸው መንገዱ አልጋ ባልጋ መሆኑ ሳይሆን ቃሉ በኑሮአቸው ተዳሳሽ ሲሆን በማየት የሚገኝ ነው ። ሰው ገድለው በሚሸሹበት ዓለም ስለ ክርስቶስ ስደተኛ መሆን ትልቅ ሐሤትን የሚሞላባቸው እውነት ነው ። ስለ እኔ ትሰደዳላችሁ ያለው ጌታ ቃሉ እውነት የሚሆነው በክርስቲያንነት ሲሰደዱ ብቻ ነው ። ስደት ከተማችንን አገራችንን ልቀቁ የሚል የክፋት አዋጅ ነው ። ጌታ ክርስቶስ ፣ ቤት ብቻ ሳይሆን አገርንም የሚለቁለት ፣ አገርን ቢከስሩም አሁንም ትልቅ ማትረፊያ የሆነ ንጉሥ ነው ። እርሱ ክርስቶስ ቤትና የቤት ራስ ፣ አገርና ንጉሥ ነው ። በምድር ላይ ተመላልሶ ያስተማረን ምቾትን ሳይሆን ትግልን ነው ። ደግሞም ሰው በበሽታ ተበጣጥሶ በሚሞትበት ዓለም ስለ እርሱ ሰማዕት መሆን ቅዱሳን ሁሉ ሲለምኑት የኖሩት ዕድል ነው ።

ቅድስት ኢየሉጣ በተሰደደችበት አገርም መኖር አልቻለችም ። ክርስቲያንነትዋ ሊደበቅ አልቻለም ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትምና ። ጴጥሮስን ከቃሉ የተነሣ የክርስቶስ ወገን ነህ እንዳሉት ኢየሉጣንም እንዲሁ አወቅዋት ። ወደ አገረ ገዥው አምጥተው ለጣዖት እንድትሰግድ ቢጠይቋት ዓይን እያለው ለማያይ ፣ ጆሮ እያለው ለማይሰማ አልሰግድም ። የዚህን እውነት የሦስት ዓመቱ ልጄ ቂርቆስ ይንገርህ ብላ አመለከተች ። ቅድስት ኢየሉጣ ለመሰደድ የሚበቃ ቆራጥ የክርስትና አቋም ነበራት ። በገዥዎች ፊትም ለመመስከር የምታምነውን ክርስቶስ የምታውቅ ሴት ነበረች ። ደግሞም ልጅዋን ገና በሕፃንነቱ ስለ ክርስቶስ ጌትነት እየነገረች ያሳደገች ናት ። ከዚህች ቅድስት እናት የምንማረው ብዙ ነገር አለ ። ልጆችን ገና በሕፃንነት ስለ ክርስቶስ ፍቅር እያስተማሩ ማሳደግን ነው ። ልጆች ከተማሩ በኋላ ወደ ኋላ ብንል እንኳ መልሰው ያበረቱናል ። ቅዱስ ቂርቆስ እናቱን ቅድስት ኢየሉጣን “አትፍሪ” እያለ ሲያበረታታት ነበር ። ልጆቻችንን ፣ ደቀ መዛሙርትን ማስተማር በደከመን ጊዜ የሚያበረታታ ለማግኘትም ነው ። በዕለተ ሆሳዕና በአፈ ሕፃናት የከበረው ጌታ በቅዱስ ቂርቆስም አንደበት ጌትነቱ ተመሰከረ ። የሰሙት ሁሉ የዕድሜውን ለጋነትና የሚናገረውን እውነት ማጨባበጥ አልቻሉም ። ቅዱስ ቂርቆስ የሚታወቅበት ንግግሩ “እኔ ክርስቲያን ነኝ” የሚለው ነው ።

ክርስቲያንነት በተራራም በሸለቆም ፣ በከፍታም በዝቅታም የሚሸፈን አይደለም ። ባላፈረብን ክርስቶስ ማፈር አይገባም ። እኛ ወደ ኋላ ብንል እግዚአብሔር ሕፃናትን ያስነሣል ። ልጆቻችንን ለክርስቶስ መኖርን ብቻ ሳይሆን መሞትንም ልናስተምራቸው ያስፈልጋል ። ክርስትና ከሰማዕትነት የተለየ አይደለምና ። ቅዱስ ቂርቆስም በመንፈስ ቅዱስ ረዳትነት ወንጌልን ሰበከ ። የሰሙት ሁሉ አመኑ ። ብርሃናዊ ፊቱንና የሕይወት ቃሉን ሰምተው “በእውነት ክርስቶስ ጌታ ነው” ብለው ሰገዱ ። አገረ ገዥውም አንዲትን ሴት አስክዳለሁ ብሎ ሕዝቡን ሁሉ ከሰረ ። የሮማ ባለሥልጣናት ቄሣሮችንና ጣዖታትን የሚያስመለኩ እንቢ ያለውንም የሚሠዉ ነበሩ ። በዚህ ምክንያት ቅዱስ ቂርቆስ በጥር 15 ቀን ሰማዕትነትን ሲቀበል በማግሥቱ ጥር 16 ቀን እናቱ ቅድስት ኢየሉጣም ሰማዕትነትን ተቀብላለች ። ሕፃኑ እናቱን በሰማዕትነት ቀደመ ። ሕፃናት በፍቅረ ኢየሱስ ካደጉ በሰማዕትነት ይቀድሙናል ። ዛሬ ላሉት ሕፃናት የምንጨነቀው ክርስቶስን እንዲያውቁ ነው ወይስ የፈረንጅ ቋንቋ እንዲያውቁ ነው ? ቅዱስ ቂርቆስን ስናስብ የሕፃናት አገልግሎት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ሊበረታታ እንደሚገባው ነው ። በሕፃንነቱ የገባ እስከ ማታ ይቆያል ። ብንወድም ባንወድም ነገ የዛሬዎቹ ሕፃናት ናት ። ቤተ ክርስቲያን ተተኪ ሕፃናትን ማስተማር ለሰማዕትነትም ማዘጋጀት ይገባታል ። ክርስቶስ የምንኖርለት ብቻ ሳይሆን የምንሞትለትም ነው ።

በዓለ ሰማዕታት የሚዘጋጀው በረከት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ምእመናን የሰማዕትነት ልብ ይዘው ዛሬ ገንዘብን ፣ ነገ ሰይፍን እንዲንቁ ለማድረግ ነው ። ዛሬም ሰማዕትነት በደጅ ደርሶ እያንኳኳ ነው ። ብዙዎች ቀድመውናል ። የማይቀረውን ሞት ለክርስቶስ ሰጥተው ባለ አክሊል ሆነዋል ። ቀጣይ ዘመንም ለቤተ ክርስቲያን ሜዳ ሳይሆን አቀበት ነውና ምእመናን ጣዕመ ዓለምን በመናቅ ፣ ለሰማዕትነት ክብር በመዘጋጀት ሊኖሩ ያስፈልጋል ። በቤዛነት የጀመረው ክርስትና በሰማዕትነት ይቀጥላል ። የምንሰደደው አገራችን በምድር ስላልሆነ ነው ። የማንከበረው ሰው ያለ አገሩ ስለማይከብር ነው ። ዘመነ ሰማዕታት ክርስቲያኖችን የሚያፋቅር ነው ፣ የምቾት ዘመን የሚያጣላ ነው ። በተገፋን ቍጥር ወደ ክርስቶስ እንቀርባለን ። በተገፋን ቍጥር ወደ ሰማይ እናድጋለን ። እሳቱ አፈሩን ይበላዋል ፣ ወርቁን ያወጣዋል !

ለሕፃናት ገና ከአራስ ቤት ጀምሮ ፍቅረ ኢየሱስን እየነገርን ካሳደግን የማያሳፍሩን ፣ እኛን የሚያበረታቱን ቆራጥ አማንያን ይሆናሉ ። ሰማዕታት ሁሉ ሰማዕት የሆኑት ስለ ክርስቶስ በመመስከር ነው ። ሰማዕት ማለት ትርጉሙ ምስክር ማለት ነው ። በቃልም በጽናትም የመሰከሩ ሰማዕታት ተብለው ይጠራሉ ። እኛስ ስለ ክርስቶስ ለመመስከር ፣ ብሎም ስለ እርሱ መከራ ለመቀበል ፈቃደኞች ነን ? ስለ ክርስቶስ መከራ የሚቀበሉ ስማቸው በወርቅ ቀለም ተጽፎ ይኖራል ። የዘመን አቧራ ሊሸፍናቸው በፍጹም አይችልም ። ለዚህም ይህ ቀን ምስክር ነው ። ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ የተደረገውን አትረሳም !

ከሰማዕቱ ከቅዱስ ቂርቆስ ረድኤት በረከት ያሳድርብን !

ዲያያን አሸናፊ መኮንን
ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ