እንኳን ከዘመነ ማርቆስ 2010 ዓ.ም. ወደ ዘመነ ሉቃስ 2011 ዓ.ም. በሰላምና በጤና አሸጋገራችሁ !!
አዲሱ ዓመት መልካም የሚሆንላችሁ በዘመን መለወጫ ቀን መጠጥ ስለ ጠጣችሁ አይደለም ። በተቃራኒው ዓመቱ መልካም የሚሆንላችሁ በዘመን መለወጫ ቀን (መስከረም አንድ) እና በተቀሩት ቀናት በእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዙ ተግባሮችን ካደረጋችሁ ነው ። አንድ ቀን ከሌላ ቀን አንዳች አይለይም ፤ ቀኖች መልካምና ክፉ የሚሆኑት ከራሳቸው ተፈጥሮ ሳይሆን ከኛ ቅንዓትና ስንፍና ነው ። የጽድቅን ሥራ ከሠራችሁ ቀኑ መልካም ይሆንላችኋል ። ኃጢአትን ከሠራችሁ (ቀኑ) ክፉና ስቃይ የሞላበት ይሆናል ። ስለ እነዚህ ነገሮች በጥልቀት ተመስጣችሁ ዕለት ዕለት እየጸለያችሁና ምጽዋት እየመጸወታችሁ ሙሉውን ዓመት እንደ መልካም ትመለከቱታላችሁ። ነገር ግን ስለ መልካም ምግባራት ግድ የለሽ ከሆናችሁ የነፍሳችሁንም እርካታ የወር መጀመሪያና የቀኖች ቊጥር ላይ ካደረጋችሁ መልካም የሆነውን ነገር ሁሉ ከራሳችሁ ታርቃላችሁ ።
መንፈሳዊ ጸሎት እንጂ አብዝቶ መጠጣት ፣ የተማርነው የእግዚአብሔር ቃል እንጂ ወይን ደስታን አይፈጥርም ። ወይን ሁከትን ያመጣል ፣ የእግዚአብሔር ቃል ግን እርጋታን ። ወይን ወደ ረብሻ ይወስዳል ፣ ቃለ እግዚአብሔር ግን ብጥብጥን ያርቃል ። ወይን መረዳትን ያጨልማል ፣ የእግዚአብሔር ቃል ግን የጨለመውን ያበራል ። ወይን አስቀድሞ ያልነበረ ጭንቀትንና ኀዘንን ያመጣል ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን የነበረውን (ጭንቀትና ፣ ኀዘን) ያርቃል። በክርስትናችን አስተምህሮ መሠረት የአሁኑን ነገር እንደ መናቅ ፣ የሚመጣውን ነገር በናፍቆት እንደ መጠበቅ ፣ ደኅንነትን ለማስጠበቅ አንዳችም ሰዋዊ ጉዳዮችን እንደ አለማሰብ እርካታንና ደስታን የሚሰጥ ነገር የለም ። ይህ ከሆነ (በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን) ሁልጊዜ በዓልን ማክበር ትችላላችሁ ።
ክርስቲያን በዓልን ማክበር ያለበት ለወራት ፣ ለአዲስ ዓመት ፣ ለጌታ ቀንም (ብቻ) አይደለም። በተቃራኒው ዘወትር በሕሐሕሐሐሐሐሐሐሐሐሐገገገይወቱ ለእርሱ የሚመጥነውን በዓል እንዲያከብር (ግድ ይለዋል) እንጂ ። (ለክርስቲያን) የሚመጥነው በዓል የቱ ነው? ጳውሎስ ሲናገር እንስማው፡- “በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም።” (1ኛ ቆሮ 5 ፥ 8) ።
ንጹሕ ኅሊና ካለህ ዘወትር መልካም በሆኑ ተስፋዎች ተሞልተህ የሚመጡትን መልካም ነገሮች በመግለጥ በዓልን ታከብራለህ ። እነዚህንም ነገሮች በድፍረት ካላደረግሃቸው በብዙ ኃጢአቶችም ከወደቅህ እልፍ በዓሎች ቢኖሩም ከሚያዝኑ ሰዎች የተሻለ ሁኔታ ላይ አትሆንም ። ነፍሴ በአሳብዋ ከጠለሸች ለእኔ የብሩህ ቀን ጥቅም ምንድር ነው ? ይህ ከሆነ ከአዲስ ዓመት ጥቅምን ማግኘት የሚሻ ሰው ይህንን ያደርጋል ። ዓመቱ ሲጠናቀቅ ስትመለከቱ ዓመታትን አሳልፏችኋልና ዘመንንምም አሻግሯችኋልና ጌታን አመስግኑ ። የሕይወት ዘመናችሁን እየቆጠራችሁ ልባችሁን አጽኑ ራሳችሁንም እንዲህ በሉት፡- “ቀናት ያልፋሉ ፣ ዓመታት ይሞላሉ ፤ አብዛኛውን መንገድ ተጉዘናል እስካሁን ምን በጎ ነገርን አደረግን? እናደርገው ዘንድ መልካም ነገር ወዴት አለ? ከዚህ ከሁሉም ጽድቆች ባዶ ሆነንና ተራቁተን እንወሰዳለን ፤ ፍርድም በደጅ ይጠብቀናል ። የቀረውም ሕይወታችን ወደ ሽምግልና ያደርሰናል ።
እነዚህን ነገሮች በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ቀን በጥልቀት እያሰላሰልን በመመሰጥ መጪዎቹን ቀናት እናስብ ። ለአይሁዳውያን በነቢዩ፡- “ቀኖቻቸውም በከንቱ አለቁ ፥ ዓመቶቻቸውም በችኰላ ።” (መዝ 77(78)፥33) ተብሎ እንደ ተነገረላቸው አይደለም ። ይህ አስቀድሜ የተናገርኩት የማያቋርጠው ፣ ዓመታት በማለፋቸውም የማይዘገየው ፣ በቀናት የማይወሰነው ፣ ድሀውም ሀብታሙም በአንድ ዓይነት መንገድና አኳኋን የሚያከብሩት በዓል ነው ። እዚህ ላይ የጽድቅ ሥራ እንጂ ሀብት አሊያም ጊዜአዊ መግቦት አያስፈልግም ። ሀብት የለህምን ? ነገር ግን ከሁሉም ሀብቶች በላይ ፍሬያማ የሆነ ፣ የማይጠፋ ፣ የማይለወጥ አላቂም ያልሆነው ፈሪሃ እግዚአብሔር አለህ። ሰማያትን ፣ ሰማየ ሰማያትን ፣ ምድርን ፣ ባሕርን ፣ አየሩን ፣ ብዙ ዓይነት የሆኑትን እንስሳት ፣ እጅግ ብዙ የሆኑትን እጽዋትን ፣ የሰውን መላ ተፈጥሮ ተመልከት ! መላእክትን ፣ ሊቃነ መላእክትን ፣ በላይ ያሉትን ኃይላትን አስተውል ።እነዚህ ሁሉም የጌታህ ፍጥረቶች እንደሆኑ አስታውስ ። መጋቢ ለሆነው ጌታ ባሪያ መሆን ፣ እርሱንም መጋቢህ ማድረግ እነዚህን ማግኘት ነው እንጂ ድህነት አይደለም ። ቀኖችን መጠበቅ የክርስትና አስተምህሮ ሳይሆን የሄለናውያን/የግሪካውያን/ የስህተት (ትምህርት) ነው ።
እንደ ዜጋ በታጫችሁበት በላይኛዋ/በሰማያዊቷ ከተማ በዚያ ትታወቃላችሁ ። በዚያ ብርሃን ለጨለማ ዕድል በማይሰጥበት ፣ ቀን በሌሊት በማይተካበት በተቃራኒው ሁልጊዜ ቀንና ብርሃን በሚሆንበት ከመላእክት ጋር አንድ እንሆናለን ። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ያለ ማቋረጥ እንሻ ። (ሐዋርያው) እንዲህ ይላልና፡- “ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ ።” (ቆላ 3፥1) ። የፀሐይ እንቅስቃሴ ዑደት ከሆነበት ቀንንም ከሚወልድበት ከምድር ጋር አንዳች አንድነት የላችሁም ። ነገር ግን በጽድቅ የምትኖሩ ከሆነ ሌሊቱ ቀን ይሆንላችኋል። በዝሙት ፣ በስካርና በሆዳምነት የሚኖሩት ቀናቸው ወደ ምሽትና ጨለማነት ይለወጣል ። ይህም የሚሆነው በፀሐይ መግባት ሳይሆን ልቡናቸው በስካር ስለሚጨልም ነው ።
እነዚህን ቀናት በጉጉት መጠበቅ ፣ በቀናቱም ታላቅ የሆነን ደስታ መቀበል ፣ በማኅበርም ላይ መብራትን ማብራት ፣ አበባም መጎንጎን የልጆች (ዓይነት) ሞኝነት ነው ። እናንተ ግን እንዲህ ካለ ደካማነት ተላቃችሁ ጎልምሳችኋል። ለሰማያዊቱ ከተማ ዜግነትም ታጭታችኋል ። ስለዚህ ግዙፍ የሆነ/በዓይን የሚታይ መብራት በማኅበር አታብሩ ።ነገር ግን በልባችሁ መንፈሳዊ ብርሃን ይብራ። መጽሐፍ እንዲህ ይላልና፡- “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ ።” (ማቴ 5፥16) [ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “አባታችሁን ” ሳይሆን “አባታችንን ” ብሎ ይጠቀማል።]
ይህ መብራት ብዙ ሽልማትን ያሰጣችኋል። የቤተ መቅደሱን[1]በር አታስዉቡ ።ነገር ግን ከክርስቶስ እጅ የጽድቅ አክሊል እንድትቀዳጁ (መልካም) የሆነ አኗኗርን አሳዩ ። አንዳች ነገር በችኮላና በጥድፊያ አሊያም ቀለል ተደርጎ አይደረግ ። ስለዚህም ምክንያት ጳውሎስ እንዲህ ብሎ አዘዘ “እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት ።” (1ኛ ቆሮ 10፥31) [2]
ስትበሉ ወይም ስትጠጡ ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉ ሲል ምን ማለት ነው? ድሀዎችን (በቤታችሁ) ጥሩ ፣ ክርስቶስን የማዕዱ ተካፋይ አድርጉ መብላትና መጠጣታችሁ ለእግዚአብሔር ክብር ይሆናል ።
ነገር ግን ለእግዚአብሔር ክብር እንድናደርግ የሚመክረን ይህን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ነገሮችንም ነው ። ወደ ማኅበር መሄድና ቤት መቀመጥ እነዚህ ሁለቱ ለእግዚአብሔር ክብር ይደረጉ ። እነዚህ ሁለቱ ለእግዚአብሔር ክብር የሚሆኑት እንዴት ነው? ቤተ ክርስቲያን በምትመጡበት ፣ ጸሎት በምትካፈሉበት ፣ መንፈሳዊ ትምህርት በምትማሩበት ጊዜ ሁሉ ይህ ተግባር ለእግዚአብሔር ክብር ሁኗል ።
እንደገና ለእግዚአብሔር ክብር ቤት መቀመጥም አለ። ይህ እንዴት ይሆናል? (አንድ ሰው ቤት የመቀመጥ ተግባር በማድረጉ ብቻ እንዴት እግዚአብሔርን ያከብራል?) በማንኛውም ጊዜ ረብሻ በምትሰሙበት ፣ ሥርዓት የለሽነትንና ዲያብሎሳዊ ተግባር በምታዩበት ፣ ጉባኤው ክፉና ርኩሳን በሆኑ ሰዎች ሲሞላ ቤት ተቀመጡ። ከዚህ ረብሻና ሥርዓት አልበኛነት ነጻ ሆናችሁ ለእግዚአብሔር ክብር (ቤታችሁ) ተቀመጡ ።
ቤት መቀመጥና ከቤት መውጣት ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ እንደሚቻል ምስጋናና ተግሣጽንም ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻላል ። አንድ ሰው ለእግዚአብሔር ክብር ማመስገንና መገሠጽ ምንድር ማለት ነው? ይላል ። ብዙ ጊዜ በሥራ ቦታ ትቀመጣላችሁ ፣ ክፉና መጥፎ ሰው ሲያልፍ ትመለከታላችሁ ። ይህ ሰው የእብሪተኛነት ምልክት የሆነውን ቅንድቡን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ በኩራት ተሞልቶ ብዙ ተከታዮችንና ሸንጋዮችን አስከትሎ ውድ የሆኑ ልብሶችን በመልበስ ፣ በኩራት መንፈስም ተከቦና በንፉግነት ሁሉን የራሱ በማድረግ ሲመላለስ ትመለከታላችሁ ። አንድ ሰው “ይህ ሰው አያስቀናምን ? የተባረከስ አይደለምን ?” ሲል ትሰማላችሁ ። ስለዚህ እናንተ (እንዲህ የሚለውን ሰው) ገሥጹት ። ዝም በል ፣ እዘን እንባህንም አፍስስ በሉት ። ስለ እግዚአብሔር ብሎ መገሠጽ ማለት ይህ ነው ።
“ይህ ሰው የተባረከ ያልሆነው ስለምንድር ነው?” የሚላችሁን ሰው እንዲህ በሉት ። እርሱ (የተባረከ የሆነው) ድንቅ የሆነ ፈረስ ፣ ወርቃማ ልጓም ፣ እጅግ ብዙ ባርያዎች ስላሉት ውድ ልብስ ስለሚለብስ ፣ በየቀኑም በስካርና በሀብት ስለሚኖር ነውን ? ነገር ግን በዚህ ምክንያት ክፉና የተረገመ ይሆናል። ብዙ እንባም ያስፈልገዋል ። ይህ ከሆነ ስለዚህ ሰው አንዳች የምታደንቁት ነገር እንደሌለ ነገር ግን ውጫዊና የእርሱ ያልሆኑትን ነገሮችን ማለትም ፈረሱን ፣ ልጓሙን ፣ ልብሱን ብቻ ስታደንቁ ይታየኛል ። ፈረሱ ፣ የፈረሱ ልጓም ፣ የልብሱ ውበት ፣ የባሪያዎቹም ጥንካሬና ኃይል እነዚህ ሁሉ ሲደነቁ ነገር ግን እርሱ ሳይመሰገንና ሳይደነቅ ሲያልፍ ከዚህ በላይ የሚያሳዝን ምን ነገር እንዳለ እስኪ ንገሩኝ ? ከዚህ ሰው በላይ ምስኪን ማን አለ? አንዳች የራሱ መልካም የሚባል ነገር ፣ አልያም ከዚህ ይዞት የሚሄደው አንዳች ነገር የሌለው ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ውጫዊ በሆኑ ነገሮች ከሚመሰገንና ከሚደነቅ (ከዚህ ሰው በላይ ምስኪን አለን?) ። የእኛ የሆኑ ማጌጫዎችና ሀብቶች የነፍስ መልካምነት ፣ የጥሩ ምግባር ሀብትና በእግዚአብሔር ላይ ያለ መታመን ናቸው እንጂ ባሪያዎች ፣ ልብስና ፈረስ አይደሉም ።
እንደ ገና ሌላ (ሰው እናስብ ። ይህ ሰው) የኔ ቢጤ ፣ የተጣለ ፣ የተናቀ ሕይወቱንም በድህነት የሚያሳልፍ መልካም ምግባርም ያለው በወዳጆቹም ዘንድ እንደ ኀዘነተኛ የሚቆጠሩ ሰው ነው ። ይህን ሰው አመስግኑት ፤ የዚህ ሰው ኑሮ ጠቃሚና መልካም የሆነ የሕይወት መንገድ ተግሣጽና ምክር ነው ። ይህ ሰው ምስኪንና አሳዛኝ ነው ካሉ ይህ ሰው እግዚአብሔር ወዳጁ ስለሆነ ፣ ሕይወትንም በመልካምነት ስለሚኖር ፣ የማይጠፋም ንብረት ባለቤት ስለሆነ ንጹሕ ኅሊናም ስላለው ከሁሉም በላይ የተባረከ ነው በሏቸው ። ይህ ሰው ሰማይንና የሰማይን መልካም ነገሮች የሚወርስ ሆኖ ሳለ (ቁሳዊ) ሀብት ስለሌለው ምን ይጎዳል ? እናንተ ራሳችሁ በዚህ መንገድ ካሰባችሁ[3] ሌሎችንም ካስተማራችሁ ሁለቱንም ለእግዚአብሔር ክብር በማድረግ ከማመስገንም ከመገሰጽም ከሁለቱም ታላቅ ሽልማትን ትቀበላላችሁ ። እኔም እነዚህን በማለት ስሜታችሁን በከንቱ አልስብም ፤ ነገር ግን እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ ለቆረጡ ሰዎች ታላቅ የሆነ ሽልማት በእግዚአብሔር ዘንድ እንዳለ እናገራለሁ ። ስለ እነዚህ ነገሮች ማለትም ክፋትን የሚሠሩ እንደሚናቁ እግዚአብሔርንም የሚፈሩ እንደሚከብሩ ነቢዩ እንዴት በግልጽ እንዳስቀመጣቸው ተመልከቱ ።