ለራስህ የምታለቅሰው ፣ የምወደው እንደ መንፈቅ መንገድ ምነው ራቀኝ የምትለው ፣ ልትለብስ ስታነሣው ልብስህን ብል የጨረሰው ፣ አለልኝ ብለህ ስታወራ ወዳጅህን ክዳት የበላው ፣ የድብቅ ልቅሶህ በሰማይ ተሰምቷልና አንተ ልጅ እንደምን አለህ ? ልቅሶ ያለ አላቃሽ አያረካምና ለራስህ አልቅሰህ አልረካ ያለኸው ፣ በሰዋራ መንገድ በተዘጋ ቤት በእንባ ፈሳሽ ለምትታጠበው ፣ ያለ ድንበር ቀርበህ ድንበር ለሚያስቀምጡብህ ፣ ያለ ስስት አሳድገህ ልጆችህ ለሚነፍጉህ ፣ ዘመድ ባላጋራ ፣ ትዳር ረመጥ የሆነብህ ፣ አባትን መገላገል ፣ እናትን መምከር የሰለቸህ አንተ የተጎዳኸው ልጅ እንደምን አለህ ?
የችግሩን ዛፍ ስትቆርጠው ቁጥቋጦው የሚበዛብህ ፣ መምህሩን ላርቀው ስትል የክፋት ተማሪዎች የሚፈሉብህ ፣ አገር ያላመድካቸው አገር ያሳጡህ ፣ አንገት የለሾች ወርቅ አበድረህ ጠጠር የመለሱልህ ፣ ያስታመምካቸው ያሳመሙህ ፣ ያስተማርካቸው ስሑት ያሉህ ፣ ለንስሐ የበቁት ንስሐን ያበዙት ፣ ያጎረስካቸው የነከሱህ ፣ ያለበስካቸው ያራቆቱህ ፣ በዚህም መድኃኔ ዓለምን መስለሃልና አንተ ልጅ እንደምን አለህ ?
እየበላህ የሚርብህ ፣ እየጠጣህ የሚጠማህ ፣ የምትፈልገውን አላውቅ ብለህ ውሎህን ያበላሸኸው ፣ ቶሎ ቀርበህ ቶሎ እየራቅህ የማታውቀውን ሥዕል ለማግኘት የምትቅበዘበዘው አንተ ልጅ እንደምን አለህ ? ሁሉም ከሥርህ ሊነቅልህ የወጣ ባላጋራ የመሰለህ ፣ የጥንቃቄ ዓይን ወዳጆችህን የጋረደብህ ፣ እንኳን ሰዉ የገዛ ልብህ የከዳህ ፣ ሰላም በሚመስለው ከተማ በጦርነት ያለኸው ፣ የወንድም ባላንጣ ፣ የእኅት አገርጋሪ ፣ የጎረቤት ምቀኛ ፣ የመንደር ነፋስ ፣ የአገር አድማ ፣ የአማኞች የሰላ ምላስ አላኖር ያለህ አንተ ልጅ ሰማይ እያየህ ነውና ኧረ እንደምን አለህ ?
ምሽቱ የሚያስፈራህ ፣ ንጋቱም የሚያሰጋህ ፣ ብቸኝነቱ ብርድ ብርድ የሚልህ ፣ ገና ሳትዋደድ መጣላቱ የሚያሰጋህ ፣ ስትፋቀር ወረቱ ገና ለገና የሚያባንንህ ፣ የወደደህን የምትርቅ ፣ የሚጠላህን የምትጣበቅ ፣ ሚዛን አጥተህ ሁሉ ወዳጅ ሁሉ ጠላት ሁኖ የሚታይህ ፣ የአንድ ቀን ትውውቅ ለዘላለም የሚሆን የሚመስልህ ፣ ሰውን በቁመና ፣ ፍቅርን በጥርስ የምትለካ ፣ ስምህን ሲያቆላምጡት ምን ልሁን የምትል ፣ የሰላምታ ውለታ አለብኝ ብለህ የምትጨነቅ ፣ በማመስገኛ ዘመንህ ራስህን የምትረግም ፣ ውዳሴ አምላክን የምታስቀር አንተ ብኩን ፣ አንተ ልጅ እንደምን አለህ ? እንደ ምን አለህ ብሎ አምላክህ በርህን ዛሬ እንኳኳ ነው ፣ እንደ አንተም እንደ ሰዉም ጨርሰህ እንደ ጌታ ያለኸው አንተ ልጅ እንደምን አለህ !
ሆድህ የሚባባው ፣ ሰው ለመኖር ሲያቅድ አንተ ግን ለሞትህ የምትሰናዳው ፣ ሞተህ ያለውን ትርኢት እያሰብህ ቀድመህ ለራስህ የምታለቅሰው ፣ ብሞት እንኳ እንዲያነሡኝ ብለህ በርህን ክፍት አድርገህ የምትተኛው ፣ ራስህን መቅጣት የዘወትር ሥራህ ያደረከው ፣ ቀኑን ከነፋስ ፣ ምሽቱን ከጨረቃ ጋር የምታወራው ፣ ከሰው ተፈጥረህ ሰው የራበህ ፣ ከአገር በልተህ ብቻህን የቀረህ አንተ ልጅ እንደም አለህ ? በቀልህን ሊበቀል እግዚአብሔር በደጅ ቆሟና ደስ ይበልህ !
አንተ ልጅ እስቲ እኔ ልምከርህ፡-
ማን ይደርስልኛል ? ምን አገኛለሁ ? ማለት የእምነት መንገድ አይደለምና አቁመው ። ሰዎችን ቅዱስም ኃጥእም ናቸው ብለህ አትበይን ። ሊረዱኝ ይችላሉ ብለህ አትርዳ ፣ ለደግ የሚጠብቁት ያጠቃልና ። እንዳለህ ለማሳየት ጌጥ አታብዛ ። ለእግዚአብሔር ክብር እንጂ ሌሎችን ለማናደድ አልተፈጠርህምና ዓላማህን አትርሳ ። ኑሮን ውጣ ውረድ ፣ ሰውነትን ሸለቆ የሚያደርገው ብሽሽቅ መሆኑን አትዘንጋ ። ምድር ቋሚ ቤት መስላህ ጨርሰህ አትዘን ። የተደሰቱ ካሉ ቀጥሎ ማዘናቸው ፣ ያዘኑ ካሉ ቀጥሎ መደሰታቸው የዓለም ወግ ነው ። የመጣው ሲሄድ ደስ ይበልህ ፣ የሚያስጨንቅ ፍቅር ነው ፣ ክዳት የሚያስተዛዝብ ነው ። የሄደውም አንድ ቀን ይመጣል ። ሳታውቅ ተደስተህ እውነቱን ስታውቅ ከተከፋህ ለእውቀት ክብር የለህም ። የማሸነፊያ መንገድ ጌታህን ክርስቶስን ማየት ብቻ ነው ። እኔም ከበረታሁ በጸሎት እነግርልሃለሁ ። ዘላለም የሚኖር ወዳጅ ፣ አጠገብ ሳይሆን በውስጥ የሚገኝ አጽናኝ አለ ። ጠባቂ መላእክቶችህ ብቸኝነትና ፍርሃት እንዳይሰማህ ተሰጥተውሃልና ደስ ይበልህ ። ልብህ መሰበሩ ልብ እንዳለህ ምልክቱ ነውና በመሰበርህ እንኳን ደስ አለህ ። ልብ የተሠራው ለመሰበር ነው ብለዋል አዋቂዎቹ ።
አንተ ልጅ እንደምን አለህ ?
ሚያዝያ 29 ቀን 2018 ዓ.ም.