ወሬው ሲፋፋም ፣ መርዶም ሲበዛ ፣ የትላንቱ ሳይፈታ ሌላ ቋጠሮ ሲመጣ ፣ ችግር ሲነባበር ፣ መከራ ሲቆለል ፣ ለደስታ ያቀዱት ቀን ለኀዘን ሲውል ፣ የቅጽበት ሐሤት የዘመናት ልቅሶ ሲሆን ፣ የተባበረ ሲለያይ ፣ የሚያስታርቅ ሲጠፋ ፣ አራዊት ተንከባካቢ ሲያገኙ ፣ የሰው ልጅ ደጋፊ ሲያጣ አንተ ታውቃለህ ፣ ሙሉ ጥያቄም ሙሉ መልስም የለኝምና ቀንህን እጠብቃለሁ ። የሁሉንም ነገር ምሥጢሩን የምታውቅ ፣ መልስ ያለህ ፣ ሥልጣንህ ሁሉን የሚከውን አንተ እግዚአብሔር ነህ ።
አንተ ታውቃለህ !
መረንነት እንደ ጨዋነት ሲታይ ፣ ትውልድን ለማምከን ደፋ ቀና ሲባል ፣ የፊቱ እንደ ጠላት የዛሬው እንደ ወዳጅ ሲታይ ፣ ትዝታ ሲሻር ፣ ተስፋም ጥቁር ጨርቅ ሲለብስ ፣ ሊሰብክ የወጣው አምልኩኝ ፣ ሊያገለግል የተሾመው አገልግሉኝ ሲል አንተ ታውቃለህ ሊሆን ያለውንም ትቆጣጠራለህ ። ስጋት ቤቱን ሲሠራብኝ ፣ ፎካሪ ሲያስጨንቀኝ እንኳን ከተዛተ ከተወረወረም አንተ ታድናለህ ። ሞት የፈረደውን ሹም ቀድመህ ትወስዳለህ ። አንተ ታውቃለህ የውስጥን የልብን ትረዳለህ ፣ ያለ ነጋሪ የጓዳዬን ጉድለት ትሞላለህ ። ለመሸፈን ታያለህ ፣ ለመሙላት ትጠይቃለህ ፣ እያወቅህ ለምነኝ ትላለህ ።
አንተ ታውቃለህ !
ዛሬ እወድሃለሁ ብል መውደዴ አልተፈተነም ፣ አላምንም እንዳልል መሄጃ የለኝም ። እንደምወድህም አንተ ታውቃለህ ። የካድኩህን ሕዝብ አሳምን ብለህ ስትልከኝ ራሴን እጠራጠራለሁ ፣ ችኵሉን እረኛ ስታደርግ በራሴ እስቃለሁ ። የማልፈልገው በዝቶ የምፈልገው ሲጠፋኝ አንተ ታውቃለህ በፍቅርህ እየኝ ፣ በታማኝነትህ በቤትህ አኑረኝ ። ዛሬ ነጭ ለብሰው ባይ ጥቁሩን አውልቀው እንደሆነ አልገባኝም ። የሚስቁት ብዙ ቀብረው እንደሆነ አልተረዳኝም ። ምንም ያለባቸው የማይመስሉ ብዙ ሸክም ተሸክመዋል ፣ ፈገግታቸውን ሳይ እንዲህ የኖሩ ይመስለኛል ፣ ከታላቅ እሳት እንደ ወጡ መቼ አውቃለሁ ? አንተ ታውቃለህ ሬሳ አስቀምጠው “ደኅና ነው” እንደሚሉ ፣ አንተ ታውቃለህ ከመራራው ኑሮ ጣፋጩን ጌታ እንደ ቀመሱ ።
አንተ ታውቃለህ !
ከሞተ የቆየ ፣ ከፈረሰም የዘመነ ብዙ ደረቅ አጥንት ይታየኛል ። ለዚህም ሕይወት መስጠት ፣ ከዚህም ታላቅ ሠራዊት ማስነሣት ይቻልሃል ። አንተ ታውቃለህ ፣ ሁሉን በዕለት መከወን ስትችል በምዕራፍ ትሠራዋለህ ። ዘጠኝ ወር ተረግዞ አንድ ቀን አምጦ ልጅን ይወልዱታል ። የመከራ ትርፎቼን ላልጠላ እንድወዳቸው ፣ በክፉ ቀን የደረሱልኝን ላልርቅ እንድቀርባቸው ፣ የእንባዬ አባሾችን ላልቀየም እንድጠጋቸው እባክህ እርዳኝ ። አንተ ታውቃለህ አካባቢው ያሰጋል ፣ ዘመኑ ዳምኗል ። ለሚያምኑ ግን ፀሐይ ይወጣል ፣ ቅዱስነትህን ለሚጠባበቁ ፈውስ ይዘንባል ። ነጻነት ውድ ነው ፣ ሕይወት የሚከፈለው ለአርነት ነውና ። እውነተኛ ነጻነት ግን ከክፉ ገዥዎች ሳይሆን ከክፉ ልብ መላቀቅ ነው ። ልቡ የበደለውን ቸር አይክሰውም ። አንተ ታውቃለህ ድሀ ተቀምጦ ሀብታም ይሞታል ፣ ጥሪት መቆያ እንጂ መኖሪያ መቼ ይሆናል ? ማረፍ ሁሉ በተስፋና በትዕግሥት ውስጥ ተደብቋል ። ሕሊና ካልሠራ ሥጋ የሕሊና መቃብር ይሆናል ። አንተ ታውቃለህ የሕይወቴ መስፍን ነህ ። ከልቤ አባርሬህ በአገሬ ንገሥ እልሃለሁ ። ግለሰብ ሲበዛ ሕዝብ ፣ ቤቶች ሲበዙ አገር እንደሚሆን ዘንግቻለሁ ።
አንተ ታውቃለህ !
የሠራሁት ቢበላሽ የሠራህልኝ ፀንቷል ፣ ያልኩት ባይሆን ያልከው ተፈጽሟል ፣ አምጬ የወለድኳቸው ቢከፉብኝ የማላውቀው ዘመድ ሆኖኛል ። ሁሉም ነገር “ነበር” ለመባል ቢቸኩልም የሁልጊዜ ነዋሪ በሆንከው የልቤን መልሕቅ ባንተ ላይ እጥላለሁ ። ልቤ ሲጎድል ፍርሃት ሲከበኝ ፣ መንቦጫቦጩ ወደ ኋላ ሲስበኝ ፣ ነፍሴ ኀዘን አርግዛ ቀኑን ማየት ሲሳነኝ አንተ ታውቃለህ ። ደግሰህ ትጠብቀኛለህ ። እንኳን በሰው ርግማን በሰው ምርቃትም አንተ ካልሞላህበት መቼ ይሞላል( አንተ ታውቃለህ ሥራህን በውበት ትሠራለህ ፣ የማይኮረጅ የማይተች ግብርህን ትፈጽማለህ ። አምናለሁ ግን አላምንም ፣ እንዳምንህ እርዳኝ ። እንደ ልቤ ከሀዲ የለም ፣ አሁንም ግን አብሬው እኖራለሁ ፣ እያፈቀረ የተበደለውን አይረሳም ። እያስታወሰም አብሮ ይኖራል ። ልቤ ከዓለም ይሰፋል ። አንዴ አንተን ትልቅ ያደርጋል ፣ ቆይቶ ችግሩን ያገናል ። አንተ ታውቃለህ ፣ ቸሩ መድኃኔ ዓለም አዎ አንተ ታውቃለህ ። እንደምታድነኝ እንጂ እንዴት እንደምታድነኝ ማወቅ የእኔ ፈንታ አይደለም ፣ ብቻ አንተ ታውቃለህ !
በል አንተ ታውቃለህ የምንከርምበቱን ፣
ሰው ኑሮውን እንጂ አያስብም ሞቱን ።
ግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም.