የትምህርቱ ርዕስ | ዕድገት -18

የመጨረሻው ክፍል

ብቻውን መቆም አይፈራም

ልጆች እጃቸውን ተይዘው ሲሄዱ ፣ በወላጆቻቸው ጥብቅ ቁጥጥር ውስጥ ሲሆኑ ደስተኛ አይደሉም ። እንኳን ልጅ ውሻም ሲታሰር ደስተኛ አይደለም ። ነጻነት የፍጥረተ ዓለም ጥማት ነው ። ታዲያ ልጆች የሚመኙት ነገር ብቻቸውን መሄድ ፣ ያለ እርዳታ መሻገር መቻል ነው ። አንድ ሕፃን ልጅ “ስታድግ ምን ታደርጋለህ ?” ስለው “ብቻዬን እሄዳለሁ” አለኝ ። በወላጆቹ እጅ ተይዞ ፣ ክንዱ እስኪገነጠል ተንጠልጥሎ መሄድ ያስመርረው ነበር ማለት ነው ። ያደገ ሰው ብቻውን መቆም አይፈራም ። ልጆችን የምንወዳቸው ከሆነ ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ ማገዝ አለብን ። አጉል ተስፋ በመስጠት ፣ እኔ እያለሁ ምን አትሆንም በማለት ሙት ትውልድ እንዳናፈራ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። ሁልጊዜ ቋሚ አይደለንምና ፣ ዛሬ በእጃችን ያለው ነገ አይኖርምና መተማመኛ መስጠት አንችልም ። ልጆች ጥገኝነትን ከለመዱ ፣ ሳይሠሩ ገንዘብን ከወሰዱ የራሳቸውን የግል የሌላውን የጋራ አድርገው ማሰብ ይጀምራሉ ። ከመሥራት ይልቅ ማታለልን ፣ ከጽድቅ ይልቅ በኃጢአት የሚገኝ ትርፍን ይናፍቃሉ ። ይሉኝታ እያጡ እኔ የለኝም ሌላው ግን አለው የሚል ስሜትን ያዳብራሉ ። የሌላውን ንብረት በቀጥታ መስመር የራሳቸው ማድረግ ስለማይችሉ የወንጀል ተባባሪ ይሆናሉ ። የሰውን ገንዘብ የሚመኝ ጨካኝ ይሆናል ። ያ ሰው በሕይወት እያለ መንጠቅ ስለማይችል የዚያን ሰው ሞት እየተመኘ ይመጣል ።

“ዓሣ የሚወድ ወዳጅህን ዓሣ ማጥመድ አለማምደው” ይባላል ። እኛ በሌለን ጊዜ እንዳይራብ ፣ ደግሞም የሚፈልገውን ያህል ማጥመድ እንዲችል ማስተማር ተገቢ ነው ። ድንበር አቋርጠው የተጓዙ ሰዎች ሁለት ነገር ይረዳል ይላሉ ። የመጀመሪያው ውኃ ዋና ሲሆን ፤ ሁለተኛው ቋንቋ ማወቅ ነው ። ሁልጊዜ የወላጆች ቤት መኖር አይቻልም ። በዚህ ዓለም ላይ በወታደር ቅርጽ እንጂ በቱሪስት መልክ ራስን ማዘጋጀት አደጋው ከፍ ያለ ነው ። ዓለም የተድላ ስፍራ ሳትሆን የትግል ቦታ ናት ። ይልቁንም የመቆያ ዓለም ሆና እንዲህ ያስጨነቀች የመኖሪያ ብትሆን ምን ያህል ታስጨንቀን ነበር ( ብለን ስናስብ ሞት መድኃኒት ሁኖ እንደ ተሰጠ ይገባናል ። እግዚአብሔር ጦርነቱ ሲፋፋም ፣ ቀጣዩ ሁኔታ አስጊ ሲሆን አምባሳደሩን ወደ አገሩ የሚጠራበት መንገድ ሞት ይባላል ። በርግጥ ራሱን ጠርቶ ወደ አገሩ የሚሄድ አምባሳደር የለም ። አምባሳደር ከሆንን ከአገራችን ርቀን እንደምንኖር እርግጥ ነው ። በገዛ አገሩ አምባሳደር የሚሆን የለምና ። ይህችን አጭር ዘመን በቆራጥነት ፣ በጥብዐት/በቅዱስ ጭካኔ ፣ በእምነት መሻገር አለብን ።

ይህ ዓለም የስደት ቤታችን ነው ። ስደተኛ በሌላ አገር ፣ በሌላ ባሕልና ቋንቋ ውስጥ የሚኖር ነው ። ስደተኛ ቢንቁት ቢጠሉት ብዙም አይገርመውም ። ምክንያቱም የገዛ አገሩ እንዳልደላው ያውቃልና ። የስደት ቤት ቢያመሻሹበት እንጂ አያድሩበትም ። እኛ የገዛ አገራችንን ብንረሳም ሁለተኛ ዜጋ የሰጡን ግን አይረሱትም ። በሰው አገር የሚኮሩ ተቀባይነታቸው ሊነጠቅ የሚችል መሆኑን ይረሳሉ ። በዚህ የስደት ዓለም ላይም ክብሩም ፣ ሙገሳውም ውሸት ነው ። ከብዙ ድካም በኋላ ስደተኛው ለአገሬ የምሠራው መቼ ነው ( ይላል ። በዚህ ዓለምም ካለው እንግልት ቀጥሎ ለሰማይ አገሬ መቼ ነው የምሠራው? እንላለን ። የሮጥንላቸው ሰዎችና ዓለም አላረካ ይሉናል ። ለሰዎች ያለን ደግነት የጨው ውኃ እንደ መስጠት ነው ። መልሰው ይጠማሉ ። ባደረግንላቸው ነገር ከማመስገን ሌላ ተጨማሪ ይፈልጋሉ ። ወደን ፈቅደን የሰጠነውን ረስተው ተምነውና ጨምረው ፣ አስፈራርተው ለመውሰድ ይከጅላሉ ። ደግነት በእግዘአብሔር ዘንድ እንጂ በሰው ዘንድ ሞገስ እያጣ ነው ።

ያደገ ሰው ራሱን ችሎ ይቆማል ። እግዚአብሔር የማንኖረው ሕይወት ፣ የማይዋል ቀን ፣ የማይሸነፍ ጦርነት አልሰጠንም ። ያደገ ሰው ይህችን ዓለም በውክልና አይገናኛትም ። በቀጥታ ስለ ራሱ መልስ ይሰጣል ። ሥራዬን ሰው ይሥራልኝ ከሚል አስተሳሰብ ይወጣል ። ለሰዎች ማስፈራራት እጅ አይሰጥም ። ትግልን የመጨረሻዬ ነው ብሎ ይሰጋውም ። መገለልን በጽናት ያስተናግዳል ። እንዳያሙኝ ብሎም በድብቅ አይኖርም ። ድፍረት ለማግኘት ብሎ ዝምተኛ ከሆነ ለፍላፊ ፣ ፈሪ ከሆነ ደፋርን አይቀልብም ። የመኖር መብት እንዳለው ያውቃል ። ሰዎች መስመራቸውን ሲያልፉም ያሳውቃል ። ለፍቅር እንጂ ለፉከራ አይሸነፍም ። ማስፈራራት ሁሉም ይወዳል ። የሚፈራ ካገኘ ሕፃንም ፣ ውሻም ያሳድዳል ። ቆመን ስንጠብቅ ፣ ደፍረን መልስ ስንሰጥ ግን ሁሉም ነገር መቆም ይጀምራል ።

ከሥራው ሐሜቱ ፣ ከራእዩ ተቃዋሚው በሚበዛበት በእኛ ምድር እግዚአብሔርን ብቻ እየሰሙ መጓዝ ተገቢ ነው ። አሳድደን ማግኘት ያለብንም የተገፉ ሰዎችን ነው ። እውነተኛው የሕይወት ምሥጢር እነዚህ ሰዎች ጋ አለ ። እነዚህ ሰዎች ማስመሰል ስላልቻሉ ሁሉም አግሏቸው ይሆናል ። ቀልድና ተረብ የያዙ ሰዎች ሙያቸው ቀላል ነውና ሁሉ ያውቃቸዋል ። የከበረ ነገር የያዙ ሰዎች ግን ብዙ ሰው አያውቃቸውም ። የሽንኩርት ገበያ ግርግሩ ብዙ ነው ። የአልማዝ ፣ የዳይመንድ ሱቅ ግን በወር አንድ ጊዜ ጠያቂ ቢገባበት ነው ። ውድ ነገሮች ብዙ ፈላጊ የላቸውም ። ብቻ ያደገ ሰው ብቻውን መቆም አይፈራም ። ላመነበት ነገርም ዋጋ ይከፍላል ። ከአገር ብንርቅ ከዘመድ እንጂ ከእግዚአብሔር አልራቅንም ። ሰው ቢጠላን ዘላለማዊ ፍቅር ተገልጦልናል ። ወደን መጣላት አይገባንም ፣ ሰዎች ግን እኛን እንዲወዱ ማስገደድ አንችልም ። ተው እንጂ ወዳጄ ዘንድሮም ትፈራለህ? ብዙ አይተሃልና ጸንተህ ቁም !

ዕድገት የሚለውን ርእስ ፈጸምን ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ።

ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ