መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ኧረ ተወኝ ጌታዬ ! » ኧረ ተወኝ ጌታዬ ! -2

የትምህርቱ ርዕስ | ኧረ ተወኝ ጌታዬ ! -2

ሁልጊዜ አመመኝ ስል ልማዱ ነው ብለው ሞቴ ቀባሪ እንዳያጣ ፣ ሁልጊዜ ሳማርር ጨለምተኛ ነው ብለው ወዳጆች እንዳይርቁኝ ፣ ሁልጊዜ ስገሥጽ ተመጻዳቂ ነው ብለው ተዳጊዎች እንዳይጠሉኝ ኧረ ተውኝ ጌታዬ በሕይወቴ ጣልቃ እየገባህ ምራኝ ። ከሚለበልብ ጸጸት ፣ ምነው ባላደረግሁት ከሚል ቁጭት አድነኝ ። እሳቱን አጥፋው አልልህም ፣ እሳቱ እያለም ማዳን ትችላለህ ። ኧረ ተው ጌታዬ ለልቤ ልብ ፣ ለእምነቴ እምነት ሁነው ።

ሲሰጡኝ የበለጠ እየከጀልሁ ቸርን ቢስ እንዳላደርግ ፣ ሲችሉኝ እየበደልሁ ትዕግሥተኛን ቀስቅሼ አውሬ እንዳላደርግ ፣ ሲወዱኝ እየራቅሁ ሰው አልባ እንዳልሆን ኧረ ተወኝ ጌታዬ ከልጅነት አስተሳሰብ አውጣኝ ። ራሴን አንቱ ካልኩበት ግብዝነት ዛሬ አድነኝ ። የራሴን ቅንጣት ደግነት ተራራ ፣ የሌሎችን ብዙ ቸርነት ትቢያ አድርጌ ከማየት እባክህ ሰውረኝ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ካያያዝ እንዳላበላሽ በቸርነትህ አግዘኝ ።

ይሻላል ሲሉት ይብሳል ፣ ያማረሩት ሲሄድ የበለጠ አማራሪ ይመጣል ። በአለንጋ የሚገርፈው ሲሞት በጊንጥ የሚገርፈው ይተካል ። ከክፉም ክፉ ይመረጣል ፣ የትላንቱን የሚያስንቅ ከምድር አይገኝም ። ሳላመሰግን ዘመኔ እንዳያልቅ ኧረ ተወኝ ጌታዬ ለአሳቤ ድንበር ስጠው ። ዙፋን የማይለቅ ንጉሥ ፣ ጥምጥም የማይፈታ ቄስ ፣ ትጥቅ የማይፈታ ወታደር ፣ ጠመኔ የማይጥል መምህር የለምና ሰው ሆኜ በሰው ከመገረም እባክህ አድነኝ ። ሥራውን የፈጸመ ፣ ታሪኩን የጻፈ ያስደስተኛል ፤ ሥራዬን ለመፈጸም ግን ዳተኛነት ያጠቃኛል ፣ ተግባርን ሳልገድል ሽልማት ፣ ሳልዋጋ ጎፈር ያምረኛል ። የሚያቀሉ ወዳጆችን እየፈለግሁ እኔ ግን የማከብድ ጓደኛቸው ነኝ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ጭንቀቴን እንደ ገለባ አቅልለው ፣ ከደረሰብኝ ነገር የደረስክልኝ አንተ ትበልጣለህና አፌን በምስጋና ሙላው ።

የሰው ፊት እንደ እሳት እንደሚፋጅ ይታወቀኛል ። ስሰጥ ግን እሳደባለሁ ፣ ማንነቱን ገፍፌ ሣንቲም እጥላለሁ ። ቀዳዳ ለለበሰ ስቄ ፣ ለለማኝ ሰላምታ ሰጥቼ አላውቅም ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ያንን ክፉ ቀን ያየ ሰው እንዴት በከፋው ሰው ላይ ይጨክናል ! ያልተመለሰ ፍቅር ዕዳ ነው ። ሰዎች እንዲያምኑኝ እንጂ እንዲተማመኑብኝ አልፈልግም ። ለወዳጆቼ አንተን ተክቶ ከመቆም እባክህ አድነኝ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ውደዱኝ አምልኩኝ ከሚል ከንቱነት በቸርነትህ አውጣኝ ።

ነገር ሁሉ በጌታ ይከናወናል እላለሁ ፣ በነገር ሁሉ ግን መጸለይን እረሳለሁ ። ሁሉም በጎ ነገር የመለኮት ግብር ነው እላለሁ ፣ ያገኘሁትን ግን በጥበቤ ያገኘሁ መስሎኝ እኮራለሁ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ትዕቢት የዲያብሎስ የበኵር ልጅ እንዳያደርገኝ እለምንሃለሁ ። ቁመናዬንና ውበቴን ከመሸጥ እባክህ አድነኝ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ደካማ መሆኔን አውቃለሁ ፣ ባንተ ብርታት ግን አልደገፍም ። ጠላት እንዳለብኝ እቀበላለሁ ፣ የማይዘናጋውን ጥበቃህን ግን እረሳለሁ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ የሚያረገርገውን የቤቴን መሠረት አንተ አጽናው ።

ብዙ ሲወቅሱኝ ይከፋኛል ። ይቅር እንዳላሉኝ ይሰማኛል ፣ ጉድለቴን እንዳጎሉት ይታወቀኛል ። እኔ ግን ሰዎችን መውቀስ ይቀናኛል ። የራሱን ሬሳ አስቀምጦ የእኔ ሬሳ ለመቅበር የመጣ ብዙ ነውና አመስጋኝነትን አለማምደኝ ። ሰዎችን ስወቅስ ለራሳቸው ያላቸውን ግምት ገድዬ እንዳይሆን እሰጋለሁ ። ኧረ ተወኝ ጌታዬ ያልተሠራ ሠሪ ቤቱን አይጨርስምና ይኸው እዋልላለሁ ። ዓለም ቢያገለኝ ካንተ ጋር አንድ አድርገኝ ። እርሱ እኮ ብለው ሲጠቁሙብኝ “ና ወደ እኔ” የሚለው ድምፅህ ይሳበኝ ። የምነግርህ ብዙ አለኝ ፣ በአደባባይ የማይወራ ብዙ እንፋሎት አርግዣለሁ ። በትዳር መከዳት ፣ በልጅ መታመም እንደምን ኃያል ነው ! ኧረ ተወኝ ጌታዬ ቶሎ ናልኝ እልሃለሁ ።

ግንቦት 7 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ