ጌታዬ ሆይ እምነቴ እየጎደለ ይንቦጫቦጫል ፣ ወደ ኋላ እየጎተተ ሊጥለኝ ይፈልጋል ። አንዳንዴም እምነቴ እያነሰ ላሸንፈው የሚገባኝ ነገር ያሸንፈኛል ። ሌላ ጊዜም እምነት አልባ እየሆንሁኝ ሁሉም ነገር ድግግሞሽ ይሆንብኛል ። የጎደለውን እምነቴን ሙላበትና ማዕበሉን ገሥጸው ። ያነሰውን እምነቴን ጨምርበትና የታመመውን ነገሬን ፈውሰው ። እምነት አልባ ስሜትን ውሰድና ሠርክ አዲስ እንደሆንህ አሳየኝ ። የአገሬ ፣ የቤተሰቤ ፣ የቤተ ክርስቲያኔ ነገር ተራራ ሁኖ ሲታየኝ የጎደለኝ ትንሽ እምነት ነውና እባክህ እምነት ጨምርልኝ። እምነቴን በጾም በጸሎት የምገልጥበትን ፣ ተራራውን ከኋላዬ አድርጌ የምተርክበትን አቅም አድለኝ ። ከፊት የቆመውን ከኋላ የሚያደርግ ፣ አላሳልፍ ያለኝን የሚያሳልፍ ፣ የበረታብኝን የእግር መጫሚያ የሚያደርግ ያንን እምነት እባክህ ጨምርልኝ ። አላምንም እንዳልልህ በቤትህ እመላለሳለሁ ፣ አምናለሁ እንዳልል ተራራውን እሰጋለሁ ። እባክህን ጌታዬ እንዳምንህ እርዳኝ ። ስለ ሌሎች መጎዳት ጾምና ጸሎትን እንድይዝ በፍቅር የሚሠራ እምነትን አድለኝ ። እኔ ቅርንጫፍ ነኝ ፣ አንተ የተሸከምከኝ ግንድ ነህ ። እስከ ዛሬ ለወደፊትም አልከብድህምና ደስ ይለኛል ። ለዘላለሙ አሜን ።
እምነት ጨምርልኝ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ