የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንደ እኔ ከተሰማችሁ ክፍል 2

    ተቀጣጥሮ መገናኘት፣ ተገናኝቶ መግባባት፣ ተግባብቶ ሥራ መጀመር ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ተቀጣጥረው የማይገናኙ ለዝንተ ዓለም ተለያይተው የሚቀሩ፣ ተገናኝተው የማይግባቡ ተጣልተው ተዳምተው የሚለያዩ፣ ጀምረው የማይጨርሱ ብዙዎች ናቸው፡፡ እኔና እናንተን ግን ይኸው አድሎን አድሮ የመገናኘትን ጸጋ ሰጠን፡፡ ያላመጥነውን የምንውጠው፣ የከደነውን ዓይናችንን የምንገልጠው፣ ያስገባነውን አየር የምናወጣው እግዚአብሔር ዕድሜ ሲሰጥ ነው፡፡ ያላመጡትን ለመዋጥ፣ የከደኑትን ለመግለጥ፣ ያስገቡትን አየር ለማስወጣት ጥቂት ጊዜ ብትሆንም ያችንም ዕድሜ የሚሰጥ እርሱ ነው፡፡ እናንተ ግን ዓመት እየቆጠራችሁ ኖርን ትላላችሁ፡፡ በእኛ በእስራኤል ልማድ ግን አንድ ቀን ኖረ፣ ሁለት ቀን ኖረ እንላለን፡፡ እናንተ ግን ቆየ ትላላችሁ፡፡ አንድ ሰዓትም መኖር ነው፡፡ በችሎታችን የሆነ፣ የሚሆንም ምንም ነገር የለም፡፡ ሁሉ በእርሱ ነው፡፡ ትላንት “አይዞሽ” ብላችሁኛል፡፡ ትልቅ ድምፅ ነው፡፡ እንጀራን የሚመጸውት እንጂ ተስፋን የሚሰጥ የለም፡፡ “እግዚአብሔር አይተውሽም” አላችሁኝ፡፡ ይህም ትልቅ የመጽናናት ቃል ነው፡፡ አዎ እስከ ዛሬ እግዚአብሔር ማንንም ተወ ተብሎ አልተጻፈም፡፡ መተውንም በእኔ አይጀምርም፡፡
ትላንት ካቆምኩበት ልቀጥልላችሁ፡– ማኅበረሰቡ ሴትን እንደ ተንቀሳቃሽ ዕቃ የሚያይ ነው፡፡ ሴትና ወንድ መሆን የጾታ ልዩነት መሆኑ ቀርቶ የሰብእና ልዩነት መስሎ ይታያቸዋል፡፡ የሴት ልጅ እናትነቷ ክቡር፣ ጾታዋ ትንሽ ለምን ሆነ? የእናትነት መነሻው ሴትነት አይደለም ወይ? ሴት ከባናለች፡፡ ከኋላችን እናት፣ ከፊታችን ሚስት፣ ከጎናችን እህት ሆና በዙሪያችን አለች፡፡ የመከራው ዓለም ያለ ሴት አይገፋም፣ እያለቀሰች ቊስል የምታጥብ፣ እያዘነች ወኅኒ ቤት ሄዳ የምትጎበኝ፣ በብርቱ ጦርነት ውስጥ ልጄን ብላ በእሳት ውስጥ የምታልፍ ያች ሴት አይደለችምን? ለነገሩ እኔም ሴት አልወድም እላለሁ፡፡ ራሴ የጠላኹትን ማንነት ማነው የሚቀበለው? ሃይማኖትም ቢሆን የሴትን የሥራ ድርሻ ገለጠ እንጂ ጾታዋን አላወገዘም፡፡ የአማኝ፣ የዜጋ መገኛ ያች ሴት ናትና፡፡ በዓለም ላይ ሁለት ገዢዎች አሉ፡፡ አንደኛው በገሀድ፣ ሌላው በስውር የሚገዛ፡፡ ሴት የማትታይ ገዢ፣ የነገሥታት ምክር አቅራቢ፣ የፈሪዎች ልብ አበዳሪ ናት፡፡ ከታላላቅ ጦርነቶች በፊት ከሴት የተማከሩ ብልሃት ያገኛሉ፡፡ ሴትነቴን ባላመልከውም አከብረዋለሁ፣ ከእግዚአብሔር የተቀበልኩት ምን ክፉ አለ!
ባለጌ ወንዶች ሴትን በአካል ይደፍራሉ፣ ባለጌ ሴቶች ወንድን በኅሊና ይደፍራሉ፡፡ ሁለቱም መድፈር መሆኑን ቃለ እግዚአብሔር ይነግረናል፡፡ አንዱን ልጄን የወለድኩት በትዳር አይደለም፣ ከደብረ ታቦር ግርጌ ከሚገኘው ምንጭ ውሃ ልቀዳ በተላክሁበት ጊዜ መደፈሬም መጽነሴም አንድ ሆነ፡፡ ከማያውቁትና ከማይወዱት ሰው ጋር መውደቅ፣ ያለ ሕሊናና ያለ ኑሮ ዝግጅት ልጅን
ወደ ዓለም መጋበዝ ምንኛ ከባድ መሆኑን እኔ አውቃለሁ፡፡ “ወንድ ልጅ ፊት ካልሰጡት…” በማለት ሁሉም በእኔ ፈረደ፡፡ በቊስሌ ላይ ጥዝጣዜ የሆነብኝ የሰዎች ትንታኔና ፍርድ ነበር፡፡ ሃይማኖቱም ሊያወግዘኝ ይሰናዳል፡፡ በዚህ ጊዜ ወላጆቼ በሳንሄድሪ ሸንጎ ጉዳዬን አቀረቡት፡፡ “ልጃችን የብልግና ባሕርይ እንደሌለባት ከልጅነቷ ጀምሮ በፈሪሃ እግዚአብሔር እንዳደገች፣ በያህዌና ያህዌ በሠራው ፍጥረት በመደነቅ እንደ ተመሠጠች፣ ይህችን ዓለም በሚበልጠው ሰማያዊ ፍቅር እንደለወጠች እናውቃለን፡፡ በዕለቱ ብንነቅፋት ንዴታችን ነው፡፡ እውነተኛ ማንነቷን ስናይ ግን ልጃችን ጨዋ ናት” አሉ፡፡ ምስክሮች መጡ፡፡ “እውነትን መናገር ለሰው አይደለም፣ እውነትን መናገር ለእግዚአብሔር ነው፤ በደብረ ታቦር ጫካ ውስጥ እንክልካይ ስንለቅም የሆነውን ሁሉ ዓይተናል፡፡ ወንዱ ጥፋተኛ ነው፡፡ በሽማግሌዎች ፍርድ፣ በካህናት ውግዘት ይገባዋል” አሉ፡፡
የግራና የቀኙን የሰማው የሳንሄድሪ ሸንጎ፡– “ይህ ሸንጎ የመጀመሪያ አማራጩ ሰላም ነው፣ የእርሱ ወደ ወኅኒ መጣል፣ እርሱን ለሮማ ወታደሮች አሳልፎ መስጠት የእርሷን ጉዳት አይለውጠውም፣ እንደ ሰማነው ፀንሳለች፤ ጠቅልሎ እንዲይዛት፣ እኛንም የዕወቁልኝ ድግሱ ላይ እንዲጠራን ፈርደናል” በማለት ወሰነ፡፡
የሕይወት ምርጫዬ ካልሆነው፣ ከዚህ በፊት ከማላውቀው፣ ቢያንስ ቤተሰቦቼ ካላጩልኝ ችግርና ፍርድ ቤት ካጨልኝ ባሌ ጋር መኖር ጀመርን፡፡ ጣፋጩን እያጣጣሙ ብቻ ሳይሆን መራራንም እያጣጣሙ መኖር ግድ መሆኑን ያኔ አየሁት፡፡ ሲላመዱ መዋደድ ይመጣልና ከትዳር በኋላ እጮኝነትን ጀመርን፡፡ በዓመቱ ዮሴፍ ተወለደ፡፡ እግዚአብሔር የዲቃላን ምስክር የሚቆጥረው በልጁ መልክ ላይ ነውና ልጁ ፍጹም አባቱን መሰለ፡፡ ከዚያ ጭንቀት፣ ከዚያ ክፉ ገጠመኝ ውስጥ ይህን የመሰለ፣ በየዕለቱ የሚለመልም ዮሴፍ በመውጣቱ ደነቀኝ፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን ለበጎ ማድረግ ይችልበታል፡፡ የእኔ ጌታ እንዴት ታደርገዋለህ አይባልም ለሰው የሚቀርቡ መጠይቆች እርሱ ጋ አቅም የላቸውም፡–
–      ለምን? አይባልም፣ ይግባኝ የማይጠየቅበት ንጉሠ ነገሥት ነውና፡፡
–      እንዴት? አይባልም፡– ካለ መኖር ወደ መኖር ማምጣት ይችላልና፡፡
–      መቼ? አይባልም፡– ከጊዜ በፊት የነበረ ከጊዜ በኋላ የሚኖር ነውና፡፡
–      የት? አይባልም፡– ባሕር ጎዳናው፣ ደመና መረማመጃው ነውና፡፡
ሁሉ በሁሉ የሆነው የእኔ አምላክ፣ ሁሉም የእኔ ሲለው ለሁሉ የሚበቃ ነው፡፡ የዓለም ነገር የእኔ ሲሉት ያጣላል፤ አይበቃምና፡፡ እግዚአብሔርን ሁሉ የእኔ ሲለው ይፋቀርበታል፣ ሞልቶ ይተርፋልና፡፡ የማይበቃን የዓለም ነገር የእኔ ማለት ሞኝነት ነው፡፡ የእኛ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ “ቅድመ ዓለም የነበርህ ጥንታዊ፣ ዛሬም ያለህ ማዕከላዊ፣ ወደፊትም የምትኖር ዘላለማዊ አንተ ነህ፡፡ የማይለምዱህ አዲስ፣ ሳታረጅ ሁሉን የምታስረጅ፣ ዘበናይ ሳይሆን ቋሚ እውነት አንተ ነህ፡፡”
“መንግሥት ሲጠሉት ኖሮ ሊወዱት ሲሉ ይሞታል” ይሉኝ ነበር ጎረቤቴ የነበሩት የፋኑኤል ልጅ ሃና፡፡ ባሌንም ስጠላው ኖሮ መውደድ ስጀምር ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡
እርሱን ለመውደድ ውስጤ ሲፈተን ኖሯል፡፡ በአንድ ቀን ስህተቱ ግን ሰው አይመዘንም፡፡ ቢያንስ በሸንጎ ሳይክደኝ ተቀብሎኛል ብዬ ፍቅሩን ማጣጣም ስጀምር እርሱ ማለቅ ጀመረ፡፡ ባሌ ከዚህ ዓለም በሞት ተሻገረ፡፡ ልጄን ያለ አቅሙ አባቴ፣ ብርሃኔ እያልኩ መጥራት ጀመርኩኝ፡፡ በግራም በቀኝም ያለኝ፣ ሮቤልም ብንያምም ያው አንዱ ልጄ ነው፡፡
የእናት የአባት ቤት ኮንትራት እንጂ ዘላቂ አይደለም፡፡ ካገቡ በኋላ አባት ባል እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ከደግ ልጅም ያው ክፉ ባል ይሻላል፡፡ አምጣ ሲሉት የማያሳቅቅ ባል ብቻ ነው፡፡ ቤተሰቦቼ ወደ እነርሱ የምመለስ እየመሰላቸው ሁሉም ፊት ይነሡኛል፡፡ የተወለደ በጭንቅም ቢሆን ያድጋል፡፡ ያ ልጅ አደገ፡፡ ቀድሞም ጋብቻን አልፈልግም ብዬ ኖርኩ፡፡ ልጄን የወለድኩት 31ኛውን ዕድሜን ስይዝ ነው፡፡ ዛሬ ልጄ 27ኛ ዓመት ዕድሜውን ይዟል፡፡ ባልንጀሮቼ ያገቡበትን ዕድሜ ይቆጥሩና በልጅነታቸው ይደሰታሉ፡፡ ያገባሁበትን ዕድሜ ብቆጥር ዛሬ የ27 ዓመት ሴት ነኝ፡፡ እውነቱ ግን 58 ዓመቴ ነው፡፡ ይህ ዕድሜ ወንድ ልጅ እዳራለሁ ብሎ የሚያስብበት ሊሆን ይችላል፡፡ ወንድ ልጅ ጊዜ አያውቅምና፡፡ ያለፈብንን ነገር ማወቅ ክብር ነው፡፡ ያለፈባቸውን ነገር ቢያውቁ ብዙ ሽማግሌዎች ዘማዊ ባልሆኑ ነበር፡፡ ለእኔ ግን ትዳሬ የእስራኤል አምላክ ነው፡፡ በዚህ ዓለም ያለው ፍቅሩ፣ ትዳሩ፣ ልጁ ለሰማያዊው ነገር ምሳሌ ነው፡፡ እውነቱና ሙላቱ ግን ከላይ ነው፡፡ እውነተኛው ፍቅር፣ እውነተኛው ትዳር፣ እውነተኛው ልጅ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡
አንዱ ልጄ ብዙ ወዳጅ አፈራልኝ፡፡ የሮማ ወታደሮች በደጃፌ ባለፉ ቊጥር በልጄ ተዛመዱኝ፡፡ ስንቃቸውን ሁሉ እቤቴ ማራገፍ ጀመሩ፡፡ አንዳንዶቹም ዮሴፍ ለእኔም ልጄ ነው እያሉ ደመወዝ መቊረጥ ጀመሩ፡፡ የቅርቡ እየከፋ፣ የሩቅ መወዳጀቱ የአምላክ ሥራ ነው አልኩኝ፡፡ ጎረቤቴ እሜት ሶስና አንድ ልጅ ወልደው እርሱም ዱርዬ ሆነባቸው፡፡ ታዲያ ከሌላኛዋ ጎረቤቴ ጋር አንድ ቀን በመንገድ ስናልፍ ክፉ ሥራ ሲሠራ አየነው፡፡ እኛ እህቴም፡– “አንድ ሰጥቷት አንዱም ከፋባት” አሉኝ፡፡ እኔ ግን እስካሁን ባርኮልኛል፡፡ ስለ ሰው መናገር የምንችለው እስካሁን ያለውን ነው፡፡ ከአሁን ቀጥሎ ያለው እንኳን ለእኛ ለባለቤቱም ከባድ ነው፡፡ በማንኖርበትም ዘመን የታመነ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እርሱ ሲወዱት መጥላት፣ ሲያምኑት መክዳት የለበትም፡፡
እኛ ደግ እህቴ፡– “አንድ ሰጥቷት እርሱም ከፋባት” ያሉት አሁንም የማለምደው ቁምነገር ነው፡፡ አዎ የአንድ ብልሹ ክፉ ነው፡፡ ልብን የሚሰብር ነው፡፡ አንዱ ሲባረክም እንደ ይስሐቅ ነው፡፡ ብዙም ቢወልዱ ጠቃሚው አንድ ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚሠራው በአንድ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንዱን ሺህ፣ አንዱን ለሺህ ደራሽ ያደርገዋል፡፡ ወንድ በሆነልኝ ሴት በሆነልኝ ይላል የሰው ሞኝ፡፡ እግዚአብሔር ሲባርከው ግን ወንዱም ሴት፣ ሴቱም ወንድ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ያንን አንድ ልጄን ዮሴፍን ባረከው፡፡ ሳይናገር የሚረታ፣ ሳይታገል የሚጥል ባለ ሞገስ ሆነ፡፡ የእኔ ብቻ ሳይሆን የአገሩ ልጅ ሆነ፡፡ የጀመረውን ለመጨረስ እልኸኛ፣ ለእኔ ሳይሆን ለእገሌ ይሁንለት የሚል የፍቅር ሰው ሆነልኝ፡፡ እንደ ልጅ የምደሰትበት፣ እንደ ትዳር የምጠቀምበት፣ እንደ መምህር የምመከርበት ልጅ ሆነልኝ፡፡ ደግ ልጅ የባልን ሀዘን ያስረሳል፡፡ ከዚህ በኋላ ረክቻለሁ፡፡ የእርሱን አበባ ዓይቶ በሰላም መሰብሰብ ነው፡፡ የረካ በሰላም ማረፍን ይመኛል፡፡ ያልረካ ግን አፈር ላፈር ገና  መጫወት ይፈልጋል፡፡
 ሰው ለሠርጉ፣ ሰው ለምርቃቱ ቀጠሮ ይይዛል፡፡ መከራ ግን በሰው ላይ ይቀጥራል፡፡ ሲገሰግስ ያደረው መከራ ዓርብ ከሰዓት በፊት ደረሰብኝ፡፡ የካቲት 29 ቀን 31 ዓ.ም
. ነው፡፡ ዮሴፍ ሥራ ሄደ ብዬ እንደገና ለመጸለይና የነቢያትን መጻሕፍት ትርጓሜ ለመስማት ወደ ምኩራብ ልወጣ ስል ዮሴፍ መጣ፡፡ መልኩ ጠቁሯል፡፡ ሰው ለደቂቃ ብልሽት የተዘጋጀ መሆኑን ባውቀውም በራሴ ላይ ይመጣል ብዬ ግን አስቤ አላውቅም፡፡ በሩቁ የምንቀበለውን በቅርብ መቀበል አለመቻል ራስ ወዳድነት ነው፡፡ በመከሩበት መመከር መታደል ነው፡፡ በመከሩበት መመከር ተራ ነው፡፡ “ልጄ ምነው አመመህ እንዴ?” አልኩት “ትንሽ ሕመም ይሰማኛል፣ ለክፉ ግን አይሰጠኝም፤ የእስራኤል አምላክ በፈዋሽ እጁ ይፈውሰኛል፡፡ እርሱ እንኳን በበሽታ ላይ በሞት ላይም ሥልጣን አለው” ብሎ ተናግሮ ሳይጨርስ አልጋው ላይ ወደቅ አለ፡፡ እኔም ቤቱን እንደገና ከፋፈትኩና ከሰሉን አቀጣጥዬ የሚወደውን ምግብ ልሠራለት ደፋ ቀና ማለት ጀመርኩኝ፡፡ 27 ዓመት ሙሉ ትኩስ እንግዳዬ ልጄ ነው፡፡ “ምን በልተሃል?” አልኩት በቀዘቀዘ ድምፅ “አንቺ ጋ የበላሁት ነው” “ከማን ጋር ተጣልተሃል?” አልኩት፡፡ “ቢጣሉኝም አልጣላም፣ ናይን ቤቴ እንጂ አገሬ አይደለም፣ ከማንም ጋር ከፍቅር ውጭ ጉዳይ የለኝም” አለ፡፡ ቂጣውን በስሱ ጋገርኩ፣ ያማረውን የእስራኤል የዓሣ ወጥ አዘጋጀሁ፡፡ የጥብርያዶስ ዓሣ ጣፋጭ ነው፡፡ ሴት ካገኘ ደግሞ ልዩ ነው፡፡ የሚሰማኝ መስሎኝ እለፈልፋለሁ፡፡ እናት ባይመልስላትም ለልጇ መናገሯን አታቆምም፡፡
“ዮሴፍ እስቲ ቀና በል” ብዬ ብወዘውዘው ድምፅም ትንፋሽም የለውም፡፡ … ከዚያ በኋላ የሆነውን አላውቅም፡፡ መላው ናይን ተላቀሰ፡፡ ዮሴፍ ስሙ የእኔ ልጅ እንጂ የሁሉም ልጅ ነው፡፡ ወዳቂና አንሺው’ አልቃሽና አባሹ መለየት እስኪያዳግት ሁሉም ዋይ አለ፡፡ የሞት ሌባ የአገር አውጫጪኝ አያወጣው፣ ጎበዝ ሯጭም አይዘውም፡፡ አሳዳጊው እኔ ተቀምጬ ሳያስፈቅደኝ ልጄን ወሰደ፡፡ በልጄ ላይ እኔ ፍቅር አለኝ፣ ያህዌ ግን ሥልጣን አለው፡፡ ሬሣ ይሰንብት አይባልም፡፡ አይጠቅመንም አንጠቅመውም፡፡ የእስራኤል አልቃሾች፣ ሙሾ አውራጆች ሬሣው ባረፈበት ሁሉ ቅኔውን መፍሰስ ጀመሩ፡፡ እኒያ እሜት ሶስና ልጃቸው በመንፈስ የሞተባቸው በአካል ለሞተው ልጄ ልጃቸውን ጨምረው አለቀሱ፡–
አብ እሳት ወልድ እሳት መንፈስ ቅዱስ እሳት
ቀድሞም ልማድሁ ነው አሳይቶ መንሣት
እያሉ መግጠም፣ ከፈጠረ ጌታ ጋር መሟገት ጀመሩ፡፡ ባገሩ ሁሉ ሞት በርክቶ የሁሉም በር በሞት ተደፍሮ ነበርና እሜት ልያም እንዲህ ብለው አለቀሱ፡–
ምን ያለው ዘመን ነው እሳትና ገለባ
የታመመው አይድን የወጣው አይገባ
በማለት ሀዘናቸውን ሲገልጡ ሕዝቡ ሁሉ ተባላ፡፡ ሬሣው እንደ ገና ተንቀሳቅሶ ወደ መቃብሩ ተጓዘ፡፡ ሲያልፍ አወራዋለሁ፣ ዛሬስ አላደክመውም ያልኩት ያ ወዳጄን ከነተከታዮቹ ሲመጣ ሳየው ከልቅሶዬ በላይ ሐፍረት ተናነቀኝ፡፡ በራሱ የሚያልፍ መከራ የለም፡፡ የመከራ አሳላፊው አንድ ነው!  እንደ እኔ ከተሰማችሁ ከሞት የጨከነ ፍቅር አለ!
                                                          ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ