መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » እግዚአብሔር ያልመለሰው ጸሎት » እግዚአብሔር ያልመለሰው ጸሎት -1

የትምህርቱ ርዕስ | እግዚአብሔር ያልመለሰው ጸሎት -1

የእግዚአብሔር ርኅራኄ የጀመረው ሰዎች ስለ ጸሎት ምንነት አውቀው መጸለይ ከጀመሩ በኋላ አይደለም ። ቸርነቱ ከፍጹማን አካላቱና ከዘላለማዊው ባሕርዩ ጋር ጸንቶ የኖረ ነው ። ጸሎታችን የእግዚአብሔር ቸርነት መገለጫ እንጂ እርሱን ቸር ማድረጊያ አይደለም ። አንዳንዶች የአባት ፍቅር የመጣላቸው ከወለዱ በኋላ ነው ። መውለድ የለወጠላቸው ጭካኔና ግዴለሽነት ፣ ራስ ወዳድነትና ሞልቃቃነት አለ ። እግዚአብሔር ከዘላለም እስከ ዘላለም ቸር ነው ። ጸሎት በእኛ ፍላጎትና በጌታ ቸርነት የሚፈጸም ነው ። ጸሎት በአብዛኛው የነፍሳችንን ጉዳይ የሚመለከት ነው ። ፀሐይ ባናምንም ባንጸልይም ትወጣለች ። ሥጋዊ ነገሮች ላላመኑና ላልተመለሱ ሰዎች ሲደረጉ እናያለን ። ጸሎት በዋናነት የነፍሳችንን ጥያቄ የሚፈጽም ነው ። እውነተኛውን ጸሎት መጸለይ የሚችሉት ከእግዚአብሔር የተወለዱ ናቸውና ። አባት ብሎ እግዚአብሔርን ለመጥራት መወለድ ያስፈልጋል ። እግዚአብሔር ሁሉንም ጸሎታችንን ይሰማል ፣ ሁሉንም ግን አይሰጠንም ። አልተሰጠንም ማለት አልሰማንም ማለት አይደለም ። ባለመስጠት የሚሰማቸው ሰዎች አሉ ።

እግዚአብሔር ጸሎትን በተለያየ መንገድ ይመልሳል ። እነዚህም መንገዶች አራት ናቸው ።

1- እሺ እሰጥሃለሁ ፤
2- ጠብቅ ታገኛለህ ፤
3- አይሆንም አይሰጥህም ፤
4- በሌላ መንገድ እከፍልሃለሁ ።

ጸሎታችን በእነዚህ አራት መንገዶች ተመልሰዋል ። እኛ አንድ ነገርን ብቻ ስለምንጠብቅ ያልተመለሰ ይመስለናል እንጂ እርሱ ልመናን የሚመልሰው በተለያየ መንገድ ነው ።

እሺ እሰጥሃለሁ

እግዚአብሔር የብዙ ሰዎችን ጸሎት መልሶአል ። የጸሎት ደብተር ስለሌለንና ስለምንረሳ ያልተመለሰ ይመስለናል እንጂ ከለመነው ውስጥ የሚበዛው መልስ አግኝቷል ። እግዚአብሔር ጸሎታችንን የሚመልሰው ራሱ ጸልዩ ብሎ ስላዘዘና አዛኝ ስለሆነ ነው ። ሰዎች ለሰዎች ደግ ነገርን ለማድረግ ፈቃድና አቅም አንድ ጊዜ አይሟሉላቸውም ። ፈቃዱ ሲኖራቸው አቅም የላቸውም ፣ አቅሙ ሲኖራቸው ፈቃዱ የላቸውም ። በዕለታዊ ኑሮአችን የምንሰቃየው በዚህ ምክንያት ነው ። ምንም ባልነበረን ጊዜ ለሰዎች ቤት ሠርተን ለመስጠት ፣ ድሆችን ከገበታችን ለማብላት ፣ አሥራት በኵራታችንን በእጥፍ ለማውጣት እንመኝ ነበር ። አቅሙ ሲመጣ ግን ዳተኛ ሆነናል ። በብር አሥራት ያወጡ የነበሩ በዶላር ማግኘት ሲጀምሩ ለማውጣት ይሰስታሉ ። አቅሙ ሲኖር ፈቃድ ይከዳል ፣ ፈቃዱ ባለበት ዘመን ደግሞ አቅም ዘግይቷል ። እግዚአብሔር ግን የልጆቹን ልመና ለመስማት ፈቃድም አቅምም አለው ። ሰው ሊከውን የማይችለውን ለብዙዎች በማድረግ ታላቅነቱን ገልጧል ። እግዚአብሔር መኖሩን ከሚያስመሰክርበት ነገር አንዱ ሳንለምነው በሚሰጠን ሌሊትና ቀን ክረምትና በጋ እንዲሁም ለምነነው በሚቸረን ብዙ ጸጋ ነው ።

ጠብቅ ታገኛለህ

እግዚአብሔር በትዕግሥት ውስጥ እየተዘጋጀ ሳይሆን እኛን እያዘጋጀ ነው ። ለሚሰጠን በረከት ብቁና ስምም እንድንሆን የትዕግሥትን ዋጋ ያስከፍላል ። የሰው ልጆች በቀላሉ ያገኙትን ነገር በቀላሉ ሊጥሉት ይችላሉ ። እግዚአብሔር እንድናከብረው የሚፈልገውን ጸጋ የትዕግሥት ደጅ ጥናትን ያውጅበታል ። ጻድቁ አብርሃም ዕለቱን ለምኖ ያገኘ አይደለም ። 25 ዓመታት እግዚአብሔርን በትዕግሥት ጠብቋል ። በዚህ መሐል ብዙ መውደቅና መነሣት አለ ። እርሱም የትምህርቱ አካል ነው ። ጉዳዩ ከመለወጡ በፊት እኛ ብንለወጥ ይሻላል ። የምንመኘው ነገር አንድ ክፍተታችንን የሚሞላ ነው ፣ ትዕግሥት ግን ለሕይወት ዘመናችን ስንቅ ፣ የተዘጉ በሮችን መክፈቻ ቁልፍ ነው ። አብርሃም ስለ ልጅ ልቡ ሞቶ ነበር ፣ በ75 ዓመቱ የተኛውን ልቡን ቀስቅሶ ልጅ እሰጥሃለሁ ያለው ራሱ እግዚአብሔር ነው ። ለአብርሃም ጸሎቱንም መልሱንም የሰጠ እግዚአብሔር ነው ። የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ሕልሙ እስኪፈጸም ብዙ መከራ ተቀብሏል ፣ 13 ዓመታት በስደትና በእስር ተጎድቷል ። ነገሥታትና ካህናት የሚለብሱትን ወጥ ቀሚስ አስቀድሞ በአባቱ ተሸለመ ፣ የአለቅነት ልብስ ከለበሰ በኋላ ዮሴፍ በወንድሞቹ ተቀጥቅጦ ጉድጓድ ተጣለ ፣ በሃያ ብር ተሽጦ ግብጽ ወረደ ። እግዚአብሔር ያለውን ይፈጽማል ፣ የትኛውም የጠላት መንጋ ሊያስቆመው አይችልም ።

ነቢዩ ዳዊት የ15 ዓመት ብላቴና ሳለ ተቀባ ። ከተቀባ በኋላ ግን የንጉሥ ጠላት መጣበት ፣ በሕመሙ ያጽናናውና የፈወሰው ሳኦል ጠላት ሁኖ ተነሣበት ። 15 ዓመታት ተንገላቶ የተቀባበትን መንበር ጨበጠ ። እግዚአብሔር በበጎች ጥበቃ መሪነትን አሰለጠነው ፣ ለሳኦል በገና በመደርደር ደግሞ የቤተ መንግሥቱን መግቢያና መውጫ አስለመደው ። በ15 ዓመታት ስደት የዓለምን መልክ አሳየው ። በይሁዳ አንግሦ ሰባት ዓመት አሰለጠነው ። ከሰባት ዓመት በኋላ በመላው እስራኤል ላይ አንግሦ ታላቅ ንጉሥ አደረገው ። በትዕግሥት ውስጥ መሠራት አለ ። በእነዚህ ዓመታት በመታገሡ ዳዊት እስካሁን ወደር ያልተገኘለት ንጉሥ ሆነ ። ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ አይሁድ የሚጠቀሙት የተደራረበ ሦስት ማዕዘን ያለው ባለ ስድስት ጫፍ ምልክት “የዳዊት ኮከብ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል ። በግምት ከ15 ሚሊየን ሕዝብ በላይ “ዳዊት” በሚል ስም አሁን እየተጠራ ነው ። የእስራኤል የመከላከያ ሥርዓት “የዳዊት ወንጭፍ- David`s Sling” በመባል የሚጠራ ነው ። እስራኤል ሦስት ዋና ዋና የመከላከያ ሥርቶች አሏት ። የዳዊት ወንጭፍ የሚባለው ግን ከባድ ሮኬቶችን የአጭርና የመካከለኛ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችንና ክሩዝ ሚሳኤሎችን እንዲሁም የአየር ስጋቶችን ለመጥለፍ የሚያስችል ነው ። የዳዊት ወንጭፍ ጎልያድን እንደ ጣለች እንዲሁም ይህ የመከላከያ ሥርዓት በእስራኤል ሰማይ ላይ የሚታዩ አጥቂዎችን የሚጥል ነው ። ዳዊት መዝሙሩ በመላው ቤተ አይሁድና ቤተ ክርስቲያን ቀንና ሌሊት ላለፉት 3 ሺህ ዓመታት ይዘመራል ። የመጠበቅ ዋጋ ከሞት በኋላም ደማቅ ኮከብ ያደርጋል ። ከሁሉ በላይ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር መወለዱ አምላክ በትዕግሥተኞች ቤት ለማደሩ ምልክት ነው ።

ይቀጥላል

ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ