መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም » የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም -4

የትምህርቱ ርዕስ | የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም -4

እመቤታችን ድንግል ማርያም በብዙ መከራና እንግልት ውስጥ አልፋለች ። የባለ መስቀሉ የኢየሱስ እናት ናትና መስቀል ተሸክማ ኖራለች ። በፅንሰትዋ ጊዜ በነበራት ስጋት ፣ በመውለጃዋ ወራት በገጠማት መገፋት ፣ በግብጽ በረሃ በደረሰባት መንከራተት ፣ በናዝሬት ኑሮዋ ባሳለፈችው አነስተኛ ኑሮ ምቾትን የሚጠይቅ ልመና አንድም ቀን ወደ ልጅዋ ስታቀርብ አናነብም ። የምስጋና እናት ናትና ምሬትም የለባትም ። በቃና ዘገሊላ ግን ስለ ሌሎች ማፈርና መጨነቅ ምልጃን አቀረበች ። እነዚያ ሰዎች ታላቅ ሐፍረት ፣ መሸማቀቅ ፣ አሁን ይህ ምን ይባላል  የሚል ግራ መጋባት ውስጥ ነበሩ ። ወደ ቤታቸው እንዳይሸሹ ችግሩ ያለው ቤታቸው ውስጥ ነው ። አንድን ሰው ስለ ችግሩ ነግረው እወቅልኝ ፣ ተረዳኝ እንዳይሉ የጠሩት የቃና ዘገሊላን ሕዝብ ነው ። ሕዝብን ማስረዳት ከባድ ነው ። በሰው መጨረሻ ላይ የሚጀምር እግዚአብሔር በዚያ ቤት ነበረ ። እመቤታችን ድንግል ማርያም የሰዎቹን ችግር አይታ ተረዳች ። መንፈሳዊ ሰው ሳይነገረው የሰዎችን ችግር የሚያውቅ ነው ። ካወቀ በኋላ እንዳይቀመጥ የሚያደርገው አዛኝ ልቡ ነው ። እመቤታችን ድንግል ማርያም በዚያ ሰርግ ላይ ብቻዋን አልሄደችም ፣ ሁልጊዜ ከሐፍረት የሚያድነውን ጌታ ይዞ መሄድ ያስፈልጋል ። ሁለተኛ በሰርግ ግርግር አልተወሰደችም ፣ የሙሽራውን ችግር ተረዳች ። መንፈሳዊ ሰው ከግርግር ወጥቶ የሰዎችን ችግር ይገነዘባል ። ያማረ ልብስ ቢለብሱ ፣ ጨዋታ ቢያበዙ እንኳ ሳቅ የሸፈነውን ብሶት ይረዳል ።

ለሰዎች መማለድ የሚያስፈልገው ሲነግሩን ሳይሆን ሳይነግሩንም ነው ። ምልጃ በሰዎቹ የመከራ ጫማ ውስጥ እግርን ማጥለቅና በፍቅር ወደ ጌታ መለመን ነው ። ምልጃ ሙሉ በሙሉ ፍቅር ነውና እግዚአብሔርን ያስደስተዋል ። ደግሞም ጸሎታችን ያለ ምልጃ ሙሉ እንደማይሆን የነገረን ራሱ ባለቤቱ ነው ። አባታችን ሆይ እንጂ አባቴ ሆይ አንልም ። የዕለት እንጀራችንን ስጠን ዛሬ እንጂ የዕለት እንጀራዬን አንልም ። ጸሎት ሌላውንም ወገን ማካተት አለበት ። ራስ ወዳድነት ያለበት ጸሎት አያርግም ። እመቤታችን ድንግል ማርያም የሰዎቹን ችግር ተረድታ ዝም አላለችም ፣ ለልጅዋ አቀረበች ። የራስን ችግር ማመቅ ፣ የሰዎችን ችግር አይቶ አዝኖ መቅረት ትክክል አይደለም ። እኛ አምላክ ያለብን ሕዝቦች ነን ። በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ይገባናል ። ልጅዋ ቻይ መሆኑን ታምን ነበር ። የእምነት እናቶች የሚባሉ በብሉይም በሐዲስም አሉ ። ያለ ወንድ ዘር እንደምትፀንስ ያመነች ግን እመቤታችን ብቻ ናት ። እንደ እርስዋ ያለ አማኒ አይገኝም ። እግዚአብሔር እንዲሁ መሥራት የሚችል መሆኑን ታምናለች ። በቃና ዘገሊላ ሰርግ ላይም ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንዲደግስ ፣ ወይን እንዲሰጥ ጠየቀች ። ወይን ተለቅሞ ፣ በመጭመቂያ ተጨምቆ ፣ ተብላልቶ ፣ ተቀምሞ የሚቀርብ ነው ። ይህ ሁሉ ሂደት ለሰው እንጂ ለእርሱ አስፈላጊ አይደለም ብላ አመነች ። እግዚአብሔር እንደሚሰጠን ካመንን በቂ ነው ፣ እንዴት እንደሚሰጠን መመራመር ግን አስፈላጊ አይደለም ። ቢሻ ካለው ዘግኖ ቢሻ ፈጥሮ መስጠት ይችላል ። እርሱ ከጊዜ ውጭ ነውና ሰዓቱ ሠርክ ነው ፣ ጊዜው ምሽት ነው አይባልለትም።

ሐምሌ 11 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ