መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም » የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም -3

የትምህርቱ ርዕስ | የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም -3

የቃና ዘገሊላ ሰርግ ብዙ ነገሮችን ያስታውሳል ። የመጀመሪያው ጋብቻ የተከናወነው በገነት ነው ። ድግስ ፣ ሚዜ አልነበረም ። ግን ያ ጋብቻ ጸንቷል ። አዳም ሞት ያመጣችበትን ሚስቱን ስምዋን ሔዋን ብሎ የሰየመበት ነው ። ያ ጋብቻ ይቅርታ ነበረው ። እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ፣ ገነትን ታህል ቦታ ያሳጣችውን ፣ ድርብ ሞት ያመጣችበትን አንቺ የሕያዋን እናት ነሽ ስምሽ ሔዋን ይባል ማለቱ ይቅርታን ያስተምረናል ። ትዳር የሚቀጥለው በይቅርታ ነው ። ልጅ ቢሆን የአካል ክፋይ ነው ። ትዳር ግን አካልነት ነው ። ቀኝ እጅ ግራ እጁን ቢመታ ቅያሜ እንደሌለ ፣ ይቆረጥ እንደማይባል ባለ ትዳርም አካል ናቸውና ይቅር ሊባባሉ ይገባል ። በገነት ሰርግ ፣ በቃና ዘገሊላም ሰርግ የነበረው አንዱ ጌታ ክርስቶስ ነው ። ተዋሕዶ የሚለው ቃል ለምሥጢረ ሥላሴም ለምሥጢረ ሥጋዌም ይነገራል ። ተዋሕዶ ለጋብቻም ይነገራል ። ለሥላሴ ተዋሕዶ ሲነገር አካላት በየራሳቸው ጽኑዓን ሁነው በአንድ መለኮት ያብባሉ ፣ ይሠራሉ ፣ ይፈርዳሉ ። ተዋሕዶ ለሥጋዌ ሲነገር ሁለትነት ጠፍቶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ይባላል ። ተዋሕዶ ለጋብቻ ሲነገር ሁለት አካል ፣ ሁለት ጠባይያት ሳሉ የመንፈስ አንድነት ይኖራቸዋል ፣ የአሳብ ትብብርም ለአንድ ቤት እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል ። ተዋሕዶ ሥላሴ ላይ ሲነገር አካልን ሳይጨፈልቅ ፣ መለኮትን ሳይበትን ነው ። ለሥጋዌ ሲነገር የአካልና የባሕርይ ምንታዌን/ሁለትነትን አርቆ ነው ። ለጋብቻ ሲነገር አካልም ጠባይያትም ለየራስ ሁነው በመስማማት አንድ ይሆናሉ ።

በቃና ዘገሊላ ሰርግ የተጠራው መለኮቱ ነው ወይስ ሰውነቱ ብንል መለኮት ሰርግ አይጠራም ፣ ሥጋም ውኃን ወይን ጠጅ ማድረግ አይችልም ። አንዱ ክርስቶስ ወደ ሰርግ ተጠራ ፣ አንዱ ክርስቶስ ውኃን ወደ ወይን ለወጠ ። ከተዋሕዶ በፊት ሁለት አካልና ባሕርይ የነበረው ከተዋሕዶ በኋላ ግን አንድ አካል አንድ ባሕርይ ሁኖ ለዘላለም ይኖራል ። በሥጋ የተሰወረው መለኮትነቱ በቃና ዘገሊላ ሰርግ በተአምራት ተገለጠ ። ቃና ዘገሊላ ገነትን ብቻ የሚያስታውስ አይደለም ፣ የመጨረሻውን ሰርግ የሚገልጥም ነው ። በቃና ዘገሊላ ሰርግ ሁለት ሰዎች ብቻ ሙሽሮች ነበሩ ። በመጨረሻው ቀን ግን እኛ ሁላችን ሙሽራይት እንሆናለን ፣ ክርስቶስ የሁላችን አንድ ሙሽራ ይሆናል ። አንድ ሙሽራ አንዲት ሙሽራይት እንዳለችው ሁሉ አንድ ካልሆንን ከበጉ ሰርግ አንሳተፍም ። አንድ ራስ አንድ አካል አለው ፣ አንድ አካልም አንድ ራስ አለው ። አካል የተባለች ቤተ ክርስቲያን አንድ ስትሆን ራስዋ ክርስቶስ እየከበረ ይመጣል ። አንድነት በማጣት በአደባባይ አንዱ ያንዱን ልብስ እየገለጠ ፣ ክርስቶስን በአደባባይ ዛሬም እየሰቀለ ነው ። ዛሬም ክርስቶስ ከመስቀል አልወረደም ።

ቃና ዘገሊላ ቀራንዮን ይመስላል ። ሰርግ ላይ መስቀሉን ያልረሳ ጌታ ምስጉን ነው ። ለእናቱ ልመና የሰጠው መልስ ይህን ይገልጣል፡- “ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት ፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት።” (ዮሐ. 2፡4)። በመስቀል ላይም ሳለ “አንቺ ሴት” የሚለው ድምፅ ተሰምቷል ። “ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን፡- አንቺ ሴት ፥ እነሆ ልጅሽ አላት።” (ዮሐ. 19 ፡ 26)። አንቺ ሴት ማለት በአራማይክ ቋንቋ ክብርን የሚያመለክት ነው ። ደግሞም “የሴቲቱ ዘር ራስህን ይቀጠቅጣል” የሚል ትንቢት ነበርና ያ ትንቢት መፈጸሙን የሚገልጥ ነው (ዘፍ. 3፡15 ፤ ገላ. 4፡4) ። ክርስቶስ እንበለ ዘርአ ብእሲ (ያለ ወንድ ዘር) የተወለደ ነውና የሴት ዘር ነው ። ያቺ ሴት ተብላ ትንቢት የተነገረላት ድንግል ማርያም ናት ። በቃና ዘገሊላ የነበረውን ችግር ከክርስቶስ በቀር የሚፈታው ማንም አልነበረም ፣ የአዳምም ውድቀት ያለ ክርስቶስ የሚፈታ አልነበረም ። ቀራንዮ ማንም ሊፈታው ያልቻለውን ማኅተም ክርስቶስ የፈታበት ቁልፍ ነው ። ቤዛነት አምላክነት ያሻዋል ። በመስቀል ላይ የፈሰሰው የፍጡር ደም ቢሆን ኖሮ ፍጡር ፍጡርን ማዳን አይቻለውም ነበር ። መለኮት ደም የለውም ፣ ፍጡር አዳኝነት የለውም ። ሥጋ የተዋሐደው ቃል በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ ድነናል ። በቃና ዘገሊላ ወይን በተአምራት ተሰጠ ፣ በቀራንዮ ወይነ ደሙ በቤዛነት ፈሰሰ ፣ ወይን በቃና የሰጠ በቀራንዮ ወይን ሆነ ። በቃና ዘገሊላ ከፊተኛው ወይን የኋለኛው በለጠ ፣ በሥላሴ አምሳል ከመፈጠራችን በላይ በተዋሕዶ ያገኘነው ክብር አምላክ ሰው ፣ ሰውም አምላክ የሆነበት ነውና እጅግ ልዑል ሆነ ።

ጌታችን በሠላሳ ዓመቱ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ ዓለም ሁሉ አወቀው ። በእናቱ ቤት ተሰውሮ የነበረው አሁን የዓለም ቤዛ የሚሆንበትን ሥራ ጀመረ ። የሰርጉ ባለቤት ጌታችንን የጋበዘው ከዮርዳኖስ በፊት ነው ። በሰርጉ ላይ አምላክን የሚጋብዝ እድለኛ ነው ። በደስታቸው ዓለምን እንጂ እግዚአብሔርን መጋበዝ የማይችሉ ብዙዎች ናቸው ። ሰርጉ ላይ ጌታ ስለ ተገኘ ወይኑ አያልቅም ማለት አይደለም ፣ ቢያልቅም ይበረክታል ። በጀልባዋ ላይ ጌታ ስለ ተሳፈረ ማዕበል አይመጣም ማለት አይደለም ፣ ቢመጣም በጌታ ቃል ይገሠጻል ። ሁልጊዜ በደስታችንም በውጥናችንም ጌታን መጋበዛችንን እርግጠኛ መሆን አለብን ። በሔዋን ያፈረ ዓለም በድንግል ማርያም ከብሯል ። ዘመዳችን ናትና ። የእኛ ልጆች በሰው አገር በትምህርት ፣ በስፖርት ውጤት ሲያመጡ እንኮራለን ። ድንግል ማርያም ዘመዳችን ፣ መኩሪያችን ፣ የተዋሕዶ ድልድይ ናት ። አምላክ ከእርስዋ የነሣውን ሥጋ ተዋሐደ ፣ ድንግል ማርያምን ተዋሐደ ብንል ድንግል ማርያም አምላክ ሆነች ማለታችን ነው ፣ የአምላክ እናት መሆንዋን እንመሰክራለን ። የአምላክን ክብር ፣ የቅዱሳንን ክብር እናውቃለን ። አምላክ ያለ አክባሪ በራሱ የከበረ ሲሆን ቅዱሳን ግን በእርሱ ከብረዋል ።

ሐምሌ 10 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ