መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም » የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም -2

የትምህርቱ ርዕስ | የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም -2

በአይሁድ ባሕል ሰርጉን የሚደግሰው ሙሽራው ራሱ ነው ። በአባቱ ቤት ስፍራ አዘጋጅቶ ሙሽራይቱን ይወስዳታል ። በቃና ዘገሊላ ሰርግ ላይ ወይን ጠጁ ባለቀ ጊዜ ደጋሹ ሙሽራ እጅግ ደንግጧል ። በሰርግ ቀን ድግሱ ካለቀበት ፣ መጥኖ መጥራትን ካልተረዳ ቤቱን እንዴት ይመራል ተብሎ ይናቃል ። ሙሽራው በታላቅ ሐፍረት ውስጥ ነበረ ። በክብር የበለጡ ሰዎች ሰው ሁሉ ገብቶ ካለቀ በኋላ ዘግየት ብለው ይመጣሉ ። ታላቁ የክብር ጌታ ግን ቀድሞ ደርሷል ። ክቡርነት ለካ ማክበር ነው ። ጠሪ አክባሪ እንዲሉ የጠራውን አከበረ ፣ ክቡር ያከብራል ። በዚያ ሰርግ ላይ የወደፊቱን የመንግሥተ ሰማያትን ሰርግ እያየልን ነበር ። በምድር የሚታየው ሁሉ ከሰማይ የተወሰደ ነው ። በላይ ያለው አያልፍም ። ትልቁን ሰርግ ቀራንዮ ላይ እንደሚሰርግ ይታየዋል ፣ እርሱ ሙሽራችን ነውና ለሙሽራይቱ ቤተ ክርስቲያን ራሱን ወይንና የሰባ ፍሪዳ አድርጎ ይደግሳል ። የአይሁድ ሙሽራ በአባቱ ቤት ስፍራ አዘጋጅቶ ሙሽራይቱን እንደሚወስድ ክርስቶስም በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ መጥቼ እወስዳችኋለሁ ብሎ ቃል ገብቷል (ዮሐ. 14 ፡ 2-3)። ከእድምተኛው በፊት ክርስቶስ ከእናቱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተገኘ ። አንዳንድ ሰዎች ቀድመው የሚገኙት ወደ ሌላ ቀጠሮ ለመሄድ ጊዜ ለማግኘት ነው ። ክርስቶስ ግን ለመሄድ አልመጣም ። በእናንተ ዘንድ መኖሪያ አደርጋለሁ ብሏልና (ዮሐ. 14 ፡ 23) ። ሁሉን በሚያውቅ እውቀቱ የወይን ጠጁ ማለቁን አውቋል ፣ ከእናቱ ልመና እስኪመጣ ድረስ ጠብቋል ። አንዳንድ ጉዳዮቻችን ካልጸለይን የሚፈጸሙ አይደሉም ።

የሰርጉ ደጋሽ ሙሽራ ሊጋብዝ የጠራቸው እየጋበዙት ነው ። የእግዚአብሔር ሰዎችን በቤታችን ስንቀበል የበለጠ ይሰጡናል ። ኤልያስ የሰራፕታዋ መበለት አንድ ምሳ ብትጋብዘው ሦስት ዓመት ከመንፈቅ በእግዚአብሔር በረከት ጋበዛት ፣ ልጅዋ ሲሞት በጸሎት አስነሣላት ። ኤልሳዕ የሱነም ሴት በቤትዋ ብትቀበለው ልጅ እንድትወልድ ጸለየላት ፣ ልጅዋ ካደገ በኋላ ቢሞት በተአምራት አስነሣላት ። የእግዚአብሔር ሰዎች በረከቶቻችን ናቸው ። እመቤታችን ድንግል ማርያም እጅግ አስተዋይ ናት ። በዚያ ግርግር ባለበት ፣ የሰርግ ዜማ በሚሰማበት ግብዣ ላይ የወይን ጠጅ ማለቁን ተረዳች ። ሙሽራው በታላቅ ሐፍረት ውስጥ መውደቁ አሳዘናት ። ከአርባ ቀን በፊት ሰማያዊ አባቱ ለዓለም እንዳስተዋወቀው ፣ እርስዋም ለዓለም ልታስተዋውቀው ነው ። ክርስቶስ በተገለጠ ቍጥር መስቀሉ እየተቃረበ ይመጣል ። ተሰውሮ ሠላሳ ዓመት የኖረው ሲገለጥ ሦስት ዓመት ብቻ ቆየ ። ሞትም ተፈረደበት ። የመሰወር ወራት ዕድሜን ያረዝማል ። ሰማያዊ አባቱ በዮርዳኖስ የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት እንዳለ እናቱም በቃና ዘገሊላ ሰርግ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለች ። ጸሎት የሚሰምረው ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ነውና ።

በዚያ ሰርግ ላይ የሚታዘብ ብዙ ሰው አለ ። የምትራራ እናት ፣ በተአምራቱ ከውርደት የሚያድን ጌታ አለ ። ያየነው ጉድለት ዘመቻ የሚቀሰቀስበት ፣ አሳልፈን የምንሰጥበት ፣ በሐሜት የምናራቁትበት ሳይሆን የጸሎት ርእስ ነው ። ያ ሙሽራ አቅሙን ማወቅ ነበረበት ፣ መጥኖ ሰው መጥራት ያስፈልገው ነበር ፣ የሰባት ቀን ግብዣ ሰባት ሰዓት መቆየት ሲያቅተው ሁሉ ቢታዘበው እንደ ሰው ትክክል ይመስላል ። መንፈሳዊ ሰው መሆን ግን ሌላ ዓይን ማበጀት ነው ።

የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም የሚለው ልመና የሚያራራ ነው ። ርኅርኂተ ሕሊና መሆንዋ ታወቀ ። እግዚአብሔርን የተሸከመና እግዚአብሔር የተሸከመው አማኝ አዛኝ መሆን አለበት ። በእስራኤል ምድር ላይ ወይን የሌለው ግብዣ አይታሰብም ። እንደ ማር ብርዝ ትኩስ ወይን ማቅረብ የተለመደ ነው ። ምነው ምን ገጠመህ ብላ ሙሽራውን መጠየቅ ፣ የተጨነቅህ ትመስላለህ ብላ ማጣራት አላስፈለጋትም ። ያንን ሁሉ ሰው የሚሸኝ አሁን የሚገኝ የግዥ ወይንም ሊኖር አይችልም ። የገንዘብ ጥያቄም አላነሣችም ። ይህን ጉዳይ ወደ ማን ማምጣት እንዳለባት አውቃለች ። ምንም እንኳ ሠላሳ ዓመት እርስዋን ታዝዞ አሁን የሰማያዊ አባቱን ፈቃድ የሚፈጽምበት ጊዜ ቢሆንም ዝም ማለት አልሆነላትም ። እርሱ በተአምራት በተገለጠ ቍጥር ሞቱ እንደሚፋጠን ብታውቅም የሰዎች ማፈር አሳዘናት ። አንገት ደፍተው ስለሚኖሩት የምንጸልየው ቃል ፣ የምንሠራው ተግባር ከሌለን ክርስትናችን እጅና እግር የለውም ማለት ነው ። ስላፈሩ ሰዎች ስትል ወደማያሳፍረው ልጅዋ መጣች ። ሊጋብዙህ ጠርተው ድግሱ አለቀባቸው ፣ የሰው ጥንስስ ሳይጀመር ያልቃል ፣ ልጄ እባክህ ድግስ ተጠርተህም መጋበዝ ልማድህ ነውና አስባቸው አለችው ።

የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም ። የወይን ጠጅ የተባለው ክብር አልቆብናል ። ኢካቦድ ሁኖ ክብር ከኢትዮጵያ ለቋል ፣ ስድብ ክረምት ከበጋ በታላላቆች ላይ ይዘንባል ። መንፈስ ቅዱስ የክብር መንፈስ ነው ። ክብር በሌለበት እግዚአብሔር አይገኝም ። ቅሌት ፣ መወራረድ የሰይጣን ግብሩ ነው ። ዛሬም የወይን ጠጅ ክብር የላቸውም እኮ የሚል ልመና ያስፈልገናል ። የወይን ጠጅ እውቀትን የሚወክል ነው ። እውቀት ሌላ ሰው ማድረግ ፣ ክፋትን አስጥሎ ደግ ነገርን ማስጨበጥ ይገባዋል ። ክፋትንና ዘረኝነትን የሚያጠነካክር እውቀት ድንቁርና ነው ። እውነተኛው እውቀት እየጠፋ ፣ የሃይማኖት ጥበብ እየራቀ ፣ የቦምብ እውቀት እያየለ መጥቷል ። ፈሪሀ እግዚአብሔር የጥበብ ጉልላት ፣ የማስተዋል ቁንጮ ናት ። እንዳሻው የሚበላ ፣ ሳይመጥን የሚናገር በዝቷል ። ሲበሉ ለውኃ ፣ ሲጣሉ ለእርቅ ቦታ ትቶ ይባላል ። እንደሚታረቅ ሁኖ የሚጣላም እየጠፋ ነው ። የወይን ጠጅ ማስተዋል እየጠፋ ነው ። ዓይቶ የሚረግጥ እየታጣ ፣ ረግጦ የሚያይ እየበዛ ነው ። ከሊቅ እስከ ደቂቅ ፣ ከኩተት/ከሕፃንነት ዳዴ/ እስከ ሽበት ያለው ወደ አንድ መልክ እየመጣ ነው ። አለማስተዋል እየበዛ ፣ ካርታውን እንደ ጣለ መንገደኛ እየሳትን ነው። ከባለ ቅኔው ጋር እንዲህ እንላለን፡-

እመቤቴ ማርያም ጠጅ እያማረሽ ፣
ማር አትይውም ወይ ሲቆርጥ ልጅሽ ።

ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ