የትምህርቱ ርዕስ | ዕድገት -3

ያደገ ሰው መገለጫ

ገመናውን ይሸፍናል

ያላደገ ገመናውን መሸፈን አይችልም ፣ ወላጆቹ ወይም ተንከባካቢዎቹ ይሸፍኑለታል ። እርሱ አያፍርም ፣ አጠገቡ ያሉ ግን ያፍሩለታል ። ሁሉም ነገሩ አደባባይ ነው ፣ የሚታዘበው እስኪያጣ የተረሳ ሰው ይሆናል ። የሚናደድበትም ፣ የሚስቅለትም አያገኝም ። ማደግ ገመናን መሸፈን ነው ። እግዚአብሔር የደበቀልንን ገመና መሸፈን ተገቢ ነው ። ከእኛ የኃጢአት ልምምድ ሰው ሊማር ይችላል ብለን ከመጠን በላይ ግልጽ መሆን ኃጢአት እንዲስፋፋ ማስታወቂያ መሥራት ነው ። አንዳንድ ግልጽነቶች ከሰይጣን ናቸው ። የሰው ልጅ የሚነገርና የማይነገርን ለይቶ ማወቅ አለበት ። በቤቱ ውስጥ ሊራቆት ፣ በአደባባይ ሊሸፈን ይገባዋል ። በቤቱ ውስጥ ለብሶ ፣ በአደባባይ ቢራቆት ይህ የአእምሮ መዛባት ነው ። ሁለት ሰዎች ያሳለፉትን ነገር ለሦስተኛ ሰው ባያወሩ መልካም ነው ። ምክንያቱም ወዳጅነት ጽኑ የሚሆነው ሲሸሽጉት ነውና ። ውድ ወርቁንና ዳይመንዱን ፊት ለፊት የሚያስቀምጥ ማንም የለም ። ሁለት ሰዎች አብረው የሠሩት ስህተት ለሦስተኛ ሰው በምንም መንገድ አይወራም ፣ ይህ ራስን ማዋረድ ነው ። ከተወራበት ይልቅ ያወራው ይናቃል ። በደልን በንስሐ ፣ በእግዚአብሔር ፊት ማስወገድ እንጂ ሕዝብ ማጫወቻ ማድረግ ድፍረትን በምድር ላይ ያበዛል ። እስከ ዛሬ ጨዋ መስለን ኖረናል ። ማኅበራዊ መገናኛዎች ግን የተደበቀውን ማንነታችንን አውጥተውታል ። በምድር ላይ ሕግ ፣ ሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ፣ የሃይማኖት ተቋማት የተዘጋጁት ገመናችንን እንድንሸፍን ፣ በቦታው እርዳታ እንድናገኝ ነው ። ከቦታው ውጭ የሆኑ ነገሮች አደጋ አላቸው ።

የከተማው የጽዳት ማስታወቂያ ቆሻሻን በቦታው መጣል ፣ ቆሻሻን በመልክ በመልኩ መለየትና በአግባቡ ከተወገደ ቆሻሻ ሀብት መሆኑን የሚናገር ነው ። ቆሻሻ በቦታው መጣል አለበት ፣ ያለ ቦታው ከሆነ ይበክላል ፣ ምሥጢርም ከቦታው ውጭ ከሆነ ራስንም ሌሎችንም ማጥፊያ ይሆናል ። ቆሻሻን በመልኩ መለየት አስፈላጊ ነው ። ያ ሥራን ያቀላል ፣ ብክነትን ይከላከላል ። እንዲሁም ለማን ምን መንገር አለብኝ የሚለውን መለየት አስፈላጊ ነው ። ለሐኪሙ በሽታን ፣ ለካህኑ ኃጢአትን ማውራት ይገባል ። እንኳን ከእርዳታ ሰጪነት ርቆ ላለው ሕዝብ ይቅርና ለባለሙያቹም ቢሆን በእውቀታቸውና በጸጋቸው መጠን መናገር ይገባል ።

የሰው ልጅ ገመና ያለው ፍጡር ነው ። ደጅ ቢያድርም ላስኪት መከለል ይፈልጋል ። ሰውን ከእንስሳ ልዩ የሚያደርገው ገመና ያለው መሆኑ ነው ። ያማረ ቤት የሠሩ ሰዎች ለቅርብ ሰው የማይነገርን ነገር ለሕዝብ ሲያወሩ እናያለን ። ዓላማው አዋቂ ነኝ ፣ ተጠቂ ነኝ ፣ ተፈላጊ ነኝ ማለት እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም ። የተጎዳ አገር ይዘን በሥራ ሳይሆን በነውር መወዳደራችን ተገቢ አይደለም ። አሁን የምናገረው ለራሴ እፎይታ ስለሚሰጠኝ ነው ወይስ የኔ ጉዳይ የዓለም ሁሉ ጉዳይ ነው ብዬ ስለማስብ ነው ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። ደስታችንን ደብቀን ችግራችንን መዝራት ራስ ወዳድነት ነው ። እኔ ከፍቶኛል ሁሉም ይክፋው ማለት ነው ። ችግራችንን ለሚመለከተውና ሊረዳን ለሚችለው ባለሙያና ባለ ስጦታ መንገር አስፈላጊ ነው ። የትም የገለጥነው ገመና ዘመናችንን በሙሉ እስረኛና አንገት ደፊ ያደርገናል ። ሰዎች ባለፈ ታሪካችን እንዲገመግሙን ያደርጋል ። “አንዴ ዘማ ካሏት ብትቆርብም አያምኗት” ይባላል ። የሰው ልጅ ይቅር ማለትና ክፉ ነገርን መርሳት ትልቅ ፈተናው ነው ።

ገመናችንን ስንገልጥ ምሥጢር የሌለን ፣ ነጻ ሰው የሆንን መስሎ ይሰማን ይሆናል ። ነገር ግን ክብር አይኖረንም ። በዙሪያችን ያሉ ቤተሰቦቻችን ፣ የገዛ ልጆቻችን አንገት እንዲደፉ ምክንያት እንሆናለን ። የሰዎችን ኀዘኔታ መፈለግ ራሱን የቻለ መቃወስ ነው ። እግዚአብሔር ሲያዝን እንጂ የሰዎች ኀዘኔታ የትም አያደርስም ። የሞተውን ሰው ሺህዎች ከበው ያለቅሱለታል ፣ እንባ እንደ ክረምት ውኃ ይፈስለታል ። በእንባ ብዛት የተነሣ ሟች ግን የለም ። የእኔ ጉዳይ በእግዚአብሔር ኃይል እኔን የሚመለከት ነው ብሎ ማሰብ ዕድገት ነው ። ሰዎች ሁሉ የራሳቸው ችግር አለባቸው ፣ የማያውቀኝ ሰው በገመናዬ ሊያውቀኝ አይገባም የሚል ሰብአዊ ክብር ሊኖረን ያስፈልጋል ። ይልቁንም የትዳር ጉዳይ የሁለት ሰዎች ብቻ ሳይሆን የሁለት ቤተሰብ ፣ የልጆችም ጉዳይ ነውና በር ተዘግቶ የሚወራ እንጂ አደባባይ ላይ የሕዝብ ማጫወቻ የሚሆን አይደለም ። “ሞኝ ባያፍር የሞኝ ዘመድ ያፍር” ይባላል ። ለራሳችን ገመና እኛው ማፈር ሲገባን ሰዎች ካፈሩልን አደጋ አለው ።

ይቀጥላል

መጋቢት 29 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ