የትምህርቱ ርዕስ | ዕድገት -4

ያደገ ሰው መገለጫ

2- ምሥጢር ይጠብቃል

አንድ ሰው ጠንካራ ማንነት አለው የሚባለው ምሥጢር መጠበቅ ሲችል ነው ። ቀላል ሰው ምሥጢርን ለመያዝ አቅም የለውም ። ሕይወት የጓዳና የአደባባይ መልክ እንዳላት ስለማይረዳ ሁሉን አደባባይ ፣ ሁሉን ዋዛ ያደርገዋል ። ምሥጢር ለመያዝ የማይችሉ ሰዎች “የማይነገር ከሆነ አትንገሩኝ ፣ እኔ አልችልም” ብለው ይናገራሉ ። አቅምንም ማወቅ መልካም ነው ። ምሥጢርን መጠበቅ ትልቅ የዕድገት መገለጫ ነው ። ያላደገ ልጅ የወላጆቹን ምሥጢር ፣ የቤቱን ገመና ያወጣል ። የሚነገርና የማይነገር ምን እንደሆነ ልጆችን እያስተማሩ ማሳደግ በጣም አስፈላጊ ነው ። ልጆች ያዩትን ሁሉ ይናገራሉ ። ያዩትን ሁሉ የሚናገሩ ልጆች ሕይወታቸውም አደጋ ላይ ይወድቃል ። ልጆች የሰሙትን ሁሉ ያስተላልፋሉ ። የሰጡአቸውን ሁሉ ያደርሳሉ ። ብዙ ክፉ ሰዎች ፣ ሰላዮችና አሸባሪዎች ልጆችን መሣሪያ ያደርጋሉ ። ምሥጢርን ለመጠበቅ ገና ከጠዋቱ ጠንካራ ምክር ይፈልጋል ። የመልካም ሰው መስፈርት ይውጣ ከተባለ ቀና ሰው ፣ ወዳጅነትን የሚያከብርና ምሥጢርን የሚጠብቅ ሰው በመላው ዓለም ተፈላጊ ነው ። ምሥጢርን መጠበቅ የተሟላ ሰውነት ፣ የተገነባ ሥነ አእምሮ ፣ የሙያ ቃል ኪዳን ፣ ትምህርተ ኖሎት ወይም የእረኝነት ብቃት ፣ የመንፈሳዊነት ጌጥም ነው ።

ሁሉም ሰው ለማንም የማይነግረው የራሱ ምሥጢር አለው ። ሰው ማኅበራዊ ፍጡር ነው የምንለው በግሉም ስለሚኖር ነው ። ከራሱ ጋር መኖር ያልቻለ ሰው ከሌሎች ጋርም መኖር አይችልም ። ከራሱ ጋር የሚኖር ሰው የራሱ ምሥጢር አለው ። ሌላውም ሰው የግል ምሥጢር ስላለው ልናከብርለት ይገባል ። የሌላውን ሰው ገመና ለመስማት ፣ ስልኩን ለመበርበር ፣ የሚውልበትን ለመከታተል ማንም ሥልጣን አልሰጠንም ። ይህ ዘመን የነጻነት ዘመን ይመስለናል ፣ የምድር ገዥዎች ፣ የዲሞክራሲ አቀንቃኞች ሳይቀር የሰውን ንግግር እየጠለፉ የሚሰሙበት ፣ በውድቀቱ እያስፈራሩ የሚገዙበት የዝቅታ ዘመን ነው ። ባልና ሚስትም አንድ ቢሆኑም አልተጨፈለቁም፣ ወንዱ ወደ ሴቷ ፣ ሴቷ ወደ ወንዱ ታጥፈው ሳይሆን አንድነታቸው በመጠባበቅ ነው ። አንድነት የግል ምሥጢርን የሚያስቀር አይደለም ። ባልና ሚስትን በአንድነት የሚያናዝዝ አዋቂ ካህን የለም ። ሁሉም በግሉ ሊናዘዝ ፣ ሊማከር ይገባዋል ። አንድ ሰው ምሥጢሩን ከነገረን ንስሐ አባቴ ነህ ፣ ሐኪሜ ነህ ፣ ስለ እግዚአብሔር ሆነህ የምትሰማኝ አንተ ብቻ ነህ እያለን ነው ። የዓለም ሕዝብ ቍጠር 8 ቢሊየን ከደረሰ ከዚህ ሁሉ ሕዝብ የእኔ ምርጥ አንተ ነህ እያለን ነው ። ከዚህ ክብር ወርደን ምሥጢርን ማውጣት ተገቢ አይደለም ። የሌላውን ምሥጢር ስናወጣ የወሬ ጥማት ያለው ደስ ይለዋል ፣ ነገር ግን በጣም እየፈራንና እየተጠነቀቀን ይመጣል ። ክፉው ዓለም ክፉዎችን ይፈራል ።

ተመራጭና ተወዳጅ ሰው መሆን ሁሉም ሰው ይፈልጋል ። በቁመናቸው የሚወደዱ መልካቸው ጠውልጎ ፣ ቁመናቸው በበሽታ ታጥፎ ይታያሉ ። ታዲያ የማይረግፍ ውበት ፣ የማይዘነብል ቁመና ምሥጢር ጠባቂነት ነው ። ምሥጢር ጠባቂዎች የሚፈለጉት በትልልቅ ቦታ ላይ ነው ። ነገሥታት ሳይቀር ምሥጢር ጠባቂ ሰው ይፈልጋሉ ። ይልቁንም የነገሥታትን ምሥጢር በቅርበት ማወቅ ሰይፍ በአንገት ላይ አንጠልጥሎ መኖር ነው ። ምሥጢር ከጠበቁት ይጠብቃል ። ውለታውንም ይመልሳል ። በምንም መንገድ የግለሰቦችንም ፣ የነገሥታትንም ምሥጢር ላውጣ ብለን መነሣት የለብንም ። አምነውን የነገሩንን ነገር እስከ መቃብራችን ልንይዘው ይገባል ። ሆድ እንኳን ምሥጢርን ስንት ቆሻሻ ነገር ተሸክሞ ይኖር የለም ወይ ( ዓለም ወደ ሕፃናት ባሕል እየተመለሰች በመሆኑ ሁሉም ነገር ሲወራ እየሰማን ነው ። ያደገ ሰው የሚወራና የማይወራ የሚለይ ነው ። በሰለጠነው ዓለም ልጆች ወንፊት ሆነው እንዲያድጉ ገና በጠዋቱ በሰለጠኑ አማካሪዎች እንዲያወሩ ይደረጋሉ ፣ የወላጆቻቸውን ምሥጢር ትምህርት ቤት ሳይቀር ያወራሉ ። ወንፊት የሆነ ትውልድን መምራት ቀላል ስለሆነ የምድር ነገሥታት ልጆችን በጠዋቱ ምሥጢር የለሽ አድርገው ይሠሩአቸዋል።

ሔዋን በሰይጣን ፈተና የወደቀችው ምሥጢርን ለጠላት በማውጣት ነው ። ዛሬም የአገርን ምሥጢር የሚያወጡ በሞት ይቀጣሉ ። ሞት የመጣው ምሥጢርን በማውጣት ነው ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተመረጠችው ምሥጢር ጠባቂ በመሆንዋ ነው ። ምሥጢርን መጠበቅ ለአማካሪና ለሐኪም ቃል ኪዳን ነው ። ዛሬ ቃል ኪዳኑ እየጸና አይመስልም ። የት ላውራ የሚል ምጥ የያዘው ትውልድ እየመጣ ነው ። አንዳንድ አማካሪዎች ስም መጥራት እስኪቀራቸው ያማከርኩት እንዲህ ያለ ሰው… እያሉ ያወራሉ ። ምሥጢር የሕግ ከለላ እንዳለው ይዘነጋሉ ። መምህረ ንስሐን አባት የሚያሰኘው ምሥጢር መጠበቁ ነው ። የአገር ደኅንነት የቆመው በምሥጢር ላይ ነው ። የአገራት ምሥጢር ሲወጣ ፣ የታላላቅ ሰዎች ገመና ሲዘረገፍ መፍራት ያስፈልጋል ። አንዳንድ ጦርነቶች የሚፈበረኩት እንዳይወጣ የሚፈለግ ምሥጢር ሲገጥም ሊሆን ይችላል ። የምድር ታላላቅ ሰዎች ምሥጢራቸው አደጋ ላይ ከደረሰ የሚሊየኖችን እልቂት ሊሠሩበት ይችላሉ ። ሁሉም ሰው ለምሥጢሩ የሚከፍለው ዋጋ አለ ። ምሥጢር ጠባቂ መሆን ሕይወትን ከአደጋ መጠበቅም ነው ። ያደገ ሰው ምሥጢር ይጠብቃል ።

ይቀጥላል
መጋቢት 30 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ