የትምህርቱ ርዕስ | ዕድገት -5

ያደገ ሰው መገለጫ

ሌሎችን አያደክምም

ያላደገ ልጅ ፍላጎቱን መግለጽ አይችልም ፣ ለፍላጎቱ ሁሉ መግለጫ ቋንቋው ልቅሶ ነው ። ያላደገ ልጅ ከእቅፍ አይወርድም ፣ አልጋ ሜዳው ነው ። ያላደገ ልጅ በራሱ መቀመጥ ፣ መቆም ፣ መራመድ ይቸገራል ። ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ በድጋፍ ወይም በመታዘል ነው ። ሁሉን ሥራውን ሌላው የሚሠራለት ነው ። ይህ ሂደት እስከ ወዲያኛው የሚቀጥል ቢሆን ኖሮ ወላጆች ለመውለድ አያስቡም ነበር ። ይህ ግን ወደ ዕድገት የሚደረግ ጉዞ በመሆኑ ለጊዜው ዋጋ ይከፍላሉ ። የሚድኸው ልጅ ደስ ይላል ፣ ሁልጊዜ የሚድህ ሆኖ ቢቀር ያሳስባል ፣ የሚኮላተፍ ልጅ ይጣፍጣል ፣ ሁልጊዜ አፍ ባይፈታ ግን ያስጨንቃል ። ልጄ አልራመድ አለኝ ፣ ልጄ እስካሁን አፍ አልፈታም ጸልዩልኝ የሚል ድምፅ ይሰማል ። አለማደግ ያሳስባል ። በዕድገት መንገድ ላይ ያለ ግን በየዕለቱ ለውጡ ስለሚታይ ያስደስታል ። ያደገ ልጅ ከወላጆቹ እቅፍና ጀርባ ላይ የወረደ ነውና አያደክምም ። የሚፈልገውን ራሱ ያደርጋል ። ወላጆቹንም ያግዛል ። ታናሽ ወንድሙን ይሸከማል ። መልእክት ተልኮ ጎረቤት ጋ ያደርሳል ፣ እገሌን ጥራልኝ ቢሉት ሄዶ ይጠራል ። የሚያዩት እየረኩበት “አህያ በወለደች ታርፋለች” እያሉ ይጠቅሱበታል ። ያደገ ልጅ ወላጁን ያሳርፋል ።

በአካልም በአእምሮም ያደገ ሰው ፍቅሩንም ቅሬታውንም መግለጥ ይችላል ። ግንኙነቱን የሚያከብር ፣ የፍቅር ዕዳ የሌለበት ነው ። ዝም ብሎ መወደድ ሕፃንነት ነው ፣ የሚወዱንን መውደድ ያስፈልጋል ። ለፍቅር ምላሽ ካልሰጠን ነፍሳችን ትጨነቃለች ። ያንን ሰው የጎዳነው ያህል ይሰማናል ። አንድ ዝነኛ ሰው ሚሊየኖችን እወዳችኋለሁ ብሎ ሲናገር ሁሉም ያጨበጭባል ። መውደድ ግን በውስጡ መታዘዝ አለው ። መውደድ በውስጡ ለሌላው ማሰብና መኖር አለው ። ሚሊየኖችን መውደድ ቀላል ነው ፣ አንድን ሰው መውደድ ግን ከባድ ነው ። እርሱን መንከባከብ፣ ይቅር ማለት ፣ መድኃኒቱን በሰዓቱ እንዲወስድ ማስታወስ ይፈልጋል ። በጅምላ የሚወዱ ብዙ ናቸው ፣ አንድን ሰው ወደውት ለዚያ ሰው ዋጋ የሚከፍሉ ግን ጥቂት ናቸው ። ያደገ ሰው ይህን እፈልጋለሁ ይህን አልፈልግም ይላል ። መርዝ ሲግቱት እንዳይቀየሙ ብሎ አይጨልጠውም ። በአርባም ፣ በስድሳም ዓመቱ በይሉኝታ ተሸብቦ ፣ ባለጌዎችን ስፖንሰር እያደረገ ፣ እሺ እሺ በማለት ላላመነበት ነገር እየኖረ ዘመኑን የሚያባክን አለ ። ሰዎች የማይገባ ነገር ሲያደርጉብን መታገሥ መልካም ነው ፣ ስህተታቸው ትክክል እስኪመስላቸው ዝም ማለት ግን ሰዎቹን መጉዳት ነው ። ለሰዎች ብለው አገር ፣ ሃይማኖት የሚለውጡ ፣ ለሌላው ፈገግ ለማለት ብቻ የተፈጠሩ የሚመስላቸው ምስኪኖች አሉ ። ዓላማ የላቸውምና ቀኑ ይመራቸዋል ፣ ጨዋታ ባለበት ሁሉ ይመቻቸዋል ። እምቢ ማለት ስለማይችሉ አንድ ቀን ወንጀል ሠርተው ራሳቸው ወኅኒ ያገኙታል።

ሰው የሚፈልውን ነገር ቁጭ ብሎ በማልቀስ አያገኝም ፣ የሚፈልገውን ለማግኘት በጥቂቱም ቢሆን መንቀሳቀስ አለበት ። እግዚአብሔር ጥረትን ይባርካል ። ጨለማ ላይ በማፍጠጥ ጨለማ አይወገድም ፣ አንድ ክብሪት መጫር ግን ጨለማውን ይገዳደራል ። ሁልጊዜ ሌላው የሠራውን ገንዘብ መካፈል ፣ ሌላው የሠራውን ምግብ ማጣጣም ፣ ሌላው ያጠበውን ልብስ መልበስ ፣ ሌላው ባነጠፈው አልጋ መተኛት ሊከብደን ይገባል ። ወላጆቻችንና ወዳጆቻችን ልብሳቸው ቆሽሾ ያመጡትን ነገር እኛ ነጭ ለብሰን ከተማ መዞር ተገቢ አይደለም ። ማደግ ብቻ መጓዝም ነው ። ሰው የሚያሻግረው ሕፃን ደስተኛ አይደለም ፣ ብቻውን ለመሻገር ይመኛል ። ያደገ ሰው ሌላው ይናገርልኝ ፣ እገሌ ካልጀመረ አልጀምርም አይልም ። ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ አያረፍድም ። ወንድሜ እስኪልክ እያሉ ለእናታቸው የማይልኩ ያላደጉ ሰዎች ዛሬም አሉ ። የራስን ብቻ ማድረግ ሌላውን አለመጠበቅ ፣ ስንት አደረግህ ብሎ አለመጠየቅ ብስለት ነው ።

ብዙ ያላደገ ትውልድን እያየን ነው ። እንደ አራስ ቤታቸው አሁንም ከአልጋ ያልወረዱ ፣ ከቤት መውጣት የማይፈልጉ ፣ አካል እያላቸው ስንኩላን የሆኑ አሳዛኝ ትውልዶች እየመጡ ነው ። ምናልባት ወላጆቻቸው የእነርሱንም ሥራ እየሠሩላቸው ልጆቹን ዓላማ የለሽ አድርገው ሊሆን ይችላል ። ሰውን ከቤቱ የሚያስወጣው ምቾት ማጣት ነው ። ምቾትን መንሣት የወላጅ ግዴታ ነው ። በራሴ መቆም እችላለሁ የሚል የዕድገት ሥነ ልቡና ያስፈልገናል ። ሠራተኛም እኛ ካልበረታን ይንቀናል ። ወደ ዓላማችን ለመጓዝ የማንንም ይሁንታ መጠበቅ የለብንም ። በዓላማችን ትክክለኛነት ላይ ብቻ እርግጠኛ ከሆንን ዛሬ ጉዞ መጀመር ያስፈልጋል ። ሁሉን ነገራችንን የሚፈጽሙልን ሰዎች እኛን ሲያስቡ ስጋት ይሰማቸዋል ። በድፍረት ለመሞት እንኳ አቅም ያጣሉ ። እኔ የሌለው ቀን ይህ ልጅ እንዴት ይሆናል ? ይላሉ ። ማደግ ወጥቶ ገንዘብ ማምጣት አይደለም ፣ ራስን ችሎ መቆም ነው ። ያን ጊዜ የምናሳስብ ሳይሆን የምናሳርፍ ሰዎች እንሆናለን ። ያደገ ሰው የእኔ የብቻዬ ፣ የእገሌ የጋራዬ አይልም ። የኅብረት ዓለም መሆኑን ይረዳል ። ደስታ ያለው ከመቀበል ይልቅ በመስጠት ውስጥ መሆኑን ያምናል ።

ያደገ ሰው ሌላውን አያደክምም ። እንኳን ሰውን እግዚአብሔርንም የሚያደክሙ ብዙ ሰነፎችና የመለወጥ አሳብ የሌላቸው ሰዎች አሉ ። ነቢዩ እነዚህን እንዲህ ይላቸዋል፡- “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፥ ስሙ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን ? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ።” ኢሳ. 7፡13። እያንዳንዱ ቀን ላይመለስ እየሄደ ነውና እባካችሁ ንቁ ፣ ትዳራችሁን ወላጆቻችሁን አታድክሙ ። ቅን መሆን እየቻላችሁ ቅንቅን አትሁኑ ። ቀኑ ዛሬ ነው ። የሚቆጨው ዓለም ማለፉ ሳይሆን እኛ ሳንለወጥ ቀኑ ማለቁ ነው ።

ይቀጥላል

ሚያዝያ 1 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ