ያደገ ሰው መገለጫ
አሳቡን መግለጥ ይችላል
ያደገ ሰው አሳቡን ለመግለጥ አይቸገርም ። አሳብ የሰው ውስጣዊ ማንነት ነው ። ሰው በመልኩ አይዳኝም ፣ በአሳቡ ግን ይመዘናል ። እንዴት እንዲህ ያለ አፍንጫ ኖረው ( አይባልም ፣ እንዴት እንዲህ ያስባል ? ይባላል ። አሳቡ የፍርድ መነሻ ነው ። ይልቁንም እግዚአብሔር ከምንሠራው ተነሥቶ ብቻ ሳይሆን ከምናስበው ተነሥቶ ይፈርዳል ። ንጹሕ አሳብ እግዚአብሔርን ማየት ይችላል ። እግዚአብሔር በጎላ ዓይን ፣ በጥሩ መነጽር ሳይሆን በንጹሕ ልብ የሚታይ አምላክ ነው ። በዘመናት ሁሉ ድንቅ ጸሎት “አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ” የሚል ነው ። የሰው ልጅ እግዚአብሔርንም ሕይወትንም ፣ ራሱንም ሰዎችንም የሚያየው በልቡ መስተዋት ነውና ንጹሕ አስተሳሰብ ሲኖረው ሁሉ ንጹሕ ሁኖ ይታየዋል ። የብዙ ግጭቶች መሠረት ውስጣዊ ግጭት ነው ። በልብ ላይ ጦርነት ካለ በአገር ላይም ጦርነት ይኖራል ። የሚታየው ነገር ሁሉ የማይታየው አስተሳሰብ ውጤት ነው ። ልብ ብለን ስንጠቅስ ከሕይወት ጋር የተያያዘች ናት ። በመንፈሳዊ ቋንቋ ልብ የሚባለው ግን አስተሳሰብ ነው ። የሰው ሕይወቱ የተመሠረተው አስተሳሰቡ ላይ ነው ። ሰው ሊጠነቀቅ የሚገባው ለአስተሳሰቡ ነው ። በአሳብ የደፈረውን ነገር ለማድረግ ቀላል ነው ። ከአሳብ ቀጥሎ ያሉት ሎሌዎች ቃልና ተግባር ናቸው ።
አሳብን መግለጥ መቻል መታደል ነው ። ይህ ግን ለአንዱ የተሰጠ ለሌላው ያልተሰጠ አይደለም ። ሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ በሁሉም ሰው ላይ አሉ ። ማሰብ ፣ መናገርና ሕያው ሁኖ መኖር/በሕይወት የመኖር መብት የሰው ልጆች ተሰጥተዋል ። አሳብን ከመግለጥ በፊት ማሰብ አስፈላጊ ነው ። ማሰብ ጊዜ የሚወስድ ፣ ራስን መግዛት የሚጠይቅ ፣ ባልንጀራዬ ማነው ( ብሎ የሚመርጥ ነው ። ማሰብ ምድራዊ ተድላን መናቅ ፣ ምናኔን የሚከጅል ነው ። የሚያስብ ሰው የዛሬ ችግሩ ላይ አይቆይም ፣ ይህን ችግር ለሌሎች መሰላል ለማድረግ ይፈልጋል ። ካሰብን ሩቅ የሚባሉ ነገሮች የሉም ። ካሰብን ጨረቃም ቅርብ ናት ። ካሰብን ጥልቁ ውስጥ እንደ ዓሣ መጓዝ ይቻላል ። ማሰብ እንደ ስንዴ መለየት ፣ ማጥራትና መፈተግ ይፈልጋል ። ላስበው የሚገባው የቱን አሳብ ነው ? ማለት ያስፈልጋል ። ይቅርታ መርሳት ፣ መተው ነው ። ሁሉን ማሰብ ውጤታማ አያደርግም ። ሰዎች ካደረሱብን ጉዳት ካላገገምን ፣ የተናገሩንን ክፉ ቃል ካልረሳን ሕይወታችን በየዕለቱ እየተቀጣች ትመጣለች ። ስለዚህ በማሰብ ውስጥ አለማሰብ አለ ። ማሰብ የሚገባንን መለየት ይገባል ። ስንዴን ከእንክርዳድ የምንለየው የተውነው እንደሆነ ምግቡ ሊያሰክረን ስለሚችል ነው ። እንክርዳድ አስተሳሰቦች ያሰክሩናል ። ያን ጊዜ የምንሠራውንና የምንናገረውን አናውቅም ። የለየነውን ማጥራት ያስፈልጋል ። ወርቁን ከአፈር እንደሚለዩት ፣ እድፉን ከልብስ እንደሚያጥቡት ማጥራት ግድ ይላል ። የታየኝ ነገር ትክክለኛ ነገር ነው ወይ ? ብሎ ማጥራት ግድ ነው ። ለማጥራት እውቀት ፣ ጸሎትና ምክር ይፈልጋል ። እንዲህ አስባለሁ ትክክል ነኝ ወይ ( ብሎ ማስገምገም ተገቢ ነው ።
መፈተግ አድካሚ ሥራ ነው ። ዛሬ ጉልበት የሚያስወጣ ነገር እየተፈለገ አይደለምና በርበሬው ሳይታጠብ ፣ ስንዴው ሳይፈተግ ይበላል ። ለዚህ ስንፍና እንዲረዳ ደግሞ ጥቅም አለው የሚል ጥናት ይካሄዳል ። አሳብን መፈተግ ያስፈልጋል ። በደንብ እስኪታየን ድረስ ላልተማሩት ሰዎች ማቅረብ አይገባንም ። ከእኛ የወጣውን ነገር መመለስ አንችልምና ። ስህተት የሆኑ ነገሮችን ከአየር ላይ የሚቀልቡ ብዙ ዝግጁ ነፍሶች አሉ ። ስህተት የሰይጣን ፈተናም ስላለበት ብዙ ተከታይ ይኖረዋል ። መፈተግ እህሉን እያጠራ ፣ ኅብስቱን እያስዋበ የሚመጣ ነው ። አሳባችንን ማስጌጥ ፣ ደስ በሚል መንገድ ማቅረብ አስፈላጊ ነው ።
አንዳንድ ሰው በተፈጥሮው የመናገር ችሎታ አለው ። በልምምድም የመናገር ችሎታ ይመጣል ። ሰዎች አሳቤን መግለጥ አልችልም ብለው የሚለፈልፉ ሰዎችን ያቀርባሉ ። አንደበት እንዲሆነኝ ብለው አስተርጓሚ ይዘው ይዞራሉ ። አሳባችንን የገዛ አፋችን ሲገልጠው ደስ ያሰኛል ። አሳቡን መግለጥ የማይችል ሰው በውስጡ ሲያወራ የሚኖር ነው ። በትንሹም በትልቁም የሚከፍለው ዋጋ ከፍ ያለ ነው ። ሰው ካልተናገረ ብልሃትን ማግኘት አይችልም ። ለመታረምም መናገር አለበት ። አሳቡን የማይገልጥ ሰው ማኅበራዊ ኑሮ የለውም ። አሳብን መግለጥ አለመቻል ሱሰኛ ያደርጋል ። በመጠጥ ቤት ጫጫታ የሚደሰቱት እነዚህ ሰዎች ናቸው ። ሁከት ባለበት ዝም ብለው በደስታ ይቀመጣሉ ። አለመናገራቸውን እየተበቀሉት ነው ። አሳብን መግለጥ አለመቻል ብስጩ ያደርጋል ። ታማሚ የሆኑ ሕፃናት ራሳቸውን የሚጎዱት አሳባቸውን መግለጥ ስለማይችሉ ነው ። አጣጥበን እንቅልፍ የሚተኛ ልጅን እንወዳለን ፣ ከዚያ ይልቅ የሚያለቅስ ልጅ ጤነኛ ፣ ንቁና አሳቡን መግለጥ የሚችል ነው ። የእኔ ባል ምንም አያውቅም ማለት ተገቢ አይደለም ። የእኔ ሚስት ምንም አታውቅም ማለት አደንቍሮ መግዛት ነው ። ብዙ ሰዎች እነርሱ የሌላቸውን ጠባይ ያለውን ሰው ሲያገቡ አንዳንዴም የሚያንሳቸውን ሰው ይመርጣሉ ። ዓለም አቀፍ ለፍላፊዎች የትዳር ጓዶቻቸው ዱዳ ናቸው ።
አሳብን መግለጥ የዕድገት ምልክት ነው ። መደሰታችንን ፣ ማዘናችንን መግለጥ ያስፈልገናል ። ሌላው ሲናገር እንዳደመጥን ሁሉ እኛም መደመጥ አለብን ። ቃላትን ማስዋብ አይጠበቅብንም ፣ ሁሉም ሰው ደራሲ አይደለምና ። አሳብን በጨዋነት ፣ የሌላውን ስሜት በመጠበቅ መግለጥ ፣ ከቀጠሉም በፍቅር ፣ ከተለያዩም በስምምነት እንዲሆን አሳብን መግለጥ ይገባል ። ሰው በሕሊናው ላይ ማጥለያ ፣ ወንፊትና ማጣሪያ የሚያገኘው በዲሲፕሊን በመንፈሳዊነት ነውና ያሰብነውን ሁሉ መናገር አይገባም ። መናገር የሚገባንን ነገር አለመናገር ግን ቁጭት ሊፈጥር ይችላል ። ይልቁንም ፍቅሩን መግለጥ የማይችል ሰው ተጎድቷል ። ላሳደጉት አድናቆቱን ያልገለጠ ዕዳ ተሸክሞ ይኖራል ። በርቱ እናንተ የትንሣኤ ሕዝቦች ሞት የተሸነፈላችሁ ስለሆናችሁ ይህ ቀላል ነውና ዛሬ ጀምሩት ።
ይቀጥላል
ሚያዝያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም.