ያደገ ሰው መገለጫ
አይበሻሸቅም
ልጅ ፣ ልጅ ስለሆነ ብቻ አይወርስም ። ለመውረስ ማደግ ወይም መብሰል አለበት ። ልጅ ሳይበስል ንብረት ቢያስቀምጡለት ይባክናል ። የነገሥታት ልጆች ሳይበስሉ አልጋውን ከወረሱ ሞግዚት ይደረግላቸው ነበር ። ለዚህም በልጅ ኢያሱ ያየነው ነው ። የእግዘአብሔርንም መንግሥት የምንወርሰው በልጅነት ብቻ ሳይሆን በብስለትም ነው ። ያልበሰለ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ስም ያሰድባል ፣ ጸጋውን ያባክናል ። ከኃጢአትም ተድላን ይፈልጋል ። መብሰል ባለው ላይ ሲጨምር አለመብሰል ግን ያለውን ያሳጣናል ። ያደገ ሰው ሌላው መገለጫው አይበሻሸቅም ። ሕፃናት ከጨዋታ ክፍላቸው የሚበዛው መበሻሸቅ ነው ። ሲበሻሸቁም የሚመርጡት ነገር የለም ፣ የሚያውቁትንና የሚያዩትን ሁሉ ይናገራሉ ። ያኛው ልጅ አካሉ የተጎዳ ከሆነም ለብሽሽቁ ያውሉታል ፣ አባቱ የማያኮራና ሥነ ምግባር የሌለው ከሆነም ያንን ያነሣሉ ። በቤት ውስጥ የተወራና የሰሙት ነገር ካለም ያንን በማውጣት ያ ልጅ ወላጅ አልባ መሆኑን ወይም እገሌ አባቱ እገሊት እናቱ አለመሆናቸውን ይነግሩታል ። ያ ልጅም ከብሽሽቁ መሐል የማንነት ጥያቄ ፣ በራሱ መሸማቀቅ ፣ ለማን ላውራው የሚል ስሜት ያድርበታል ። አብዛኛው ስብራት የሚጀምረው ራስን ማበርታት በማይቻልበት በልጅነት ዕድሜ ነው ። የሚበዛው የሰው ልጅ እስከ ሽምግልናው የሚኖረው ልጅነቱን ነው ። የልጅነት ጊዜ ውብና አስደሳች መሆን ያለበት መሠረት የሚጣልበት ስለሆነ ነው ። የልጅነት ጉዳቶች ሊካሱ የሚችሉት በእግዚአብሔር አባትነት ብቻ ነው ።
መበሻሸቅ ያለ ማደግ ምልክት ነው ። መበሻሸቅ እየተከታተሉ ያንን ሰው መሳቂያ ማድረግ ፣ በአደባባይ ማራቆት ነው ። መበሻሸቅ በቃላት ፣ በድርጊት የሚገለጥ ነው ። መበሻሸቅ ሞትን ሊወልድ የሚችል ነው ። መቼም ሕሊና የሌለው ሰው የሌላውን ሕሊና ለመስበር ብቁ ነው ። ሕሊና ካለን ለሰው ሕሊና እንጠነቀቃለን ። በአባቱ ድካም ልጅን አንመዝነውም ፣ በእናቱ ጥፋትም ልጅን ዕዳ አናሸክመውም ። አባት እንደ ልጁ ፣ ልጅም እንደ አባቱ የሚሆንበት ዕድል ጠባብ ነው ። እግዚአብሔር እያንዳንዱን ሰው ሲፈጥረው ኦርጂናል አድርጎ እንጂ ኮፒ አድርጎ የፈጠረው ማንም የለም ። ስለዚህ እገሌ እንደ ራሱ እንጂ እንደ ወላጆቹ አይደለም ። የብዙ ጨካኝ ነገሥታት ልጆች በባዕድ አገር ያለ በደላቸው ይንከራተታሉ ። እንደ አባቶቻቸው አይደሉም ። መርጠው ከዚያ ቤተሰብ አልተወለዱምና መውቀስና መከሰስ አይገባንም ። የበደለኛው የአዳም ልጅ ጻድቁ አቤል ነው ፣ የጻድቁ የዳዊት ልጆች እነ አምኖን እነ አቤሴሎምን የመሳሰሉ ጨካኞች ናቸው ። ዛሬ ትልልቅ መንፈሳውያን አገልጋዮችን ካየን የካህን ልጅ አይደሉም ። እግዚአብሔር ከማይጠበቅ ስፍራ ለራሱ ሰው ያበቅላል ።
ብሽሽቅ ከተፈጠርንበት ዓላማ ያወጣናል ። የምንኖረውም ሌላውን ለማናደድ እንደሆነ እንድናስብ ያደርገናል ። ብሽሽቅ የሌላው ክፉ ነገር እንጂ ደግ ነገር እንዳይታየን ስለሚያደርግ አደጋው ከባድ ነው ። ብሽሽቅ ሰድቦ ለሰዳቢ መስጠት ፣ ያ ሰው ሰላምና ዕረፍት ሲያጣ መደሰት ነው ። የሚገርመው ለማብሸቅ ብለው ሰዎች የሚገቡበት ነገር ራሳቸውን የበለጠ ሊጎዳ ይችላል ። ለማብሸቅ ብለው ሌላ እጮኛ ፣ ሌላ ትዳር የሚጀምሩ ዕድሜአቸውን በከንቱ ነገር የሚፈጽሙ ሰዎች አሉ ። ለማብሸቅ ብለን የምንገባበት ነገር የበለጠ የምንጎዳበት ነው ። አብሻቂም አብሻቂ አለውና ። ብሽሽቅ ግለሰቦችን ፣ ትዳርን ፣ አገርን ፣ ቤተ ክርስቲያንን ይጎዳል ። ዛሬ በምን ላናደው በሚል መርሕ የክፋት ውድድር ውስጥ ገብተናል ። ሰዎች ሰዎችን ለማብሸቅ ሚዲያ ገዝተዋል ። አንድን ሰው ለመናገር ሚሊየኖችን ጆሮ ስጡኝ ይላሉ ። ያልተመጣጠነ ጠብ እየጎዳን ነው ። ብዙ የዋሃን እንዲሸማቀቁና እንዲፈሩ እያደረግን ነው ።
ትልልቅ ሥራ ለመሥራት ልቡም ጉልበቱም ያላቸው ሰዎች ነበሩ ፣ ነገር ግን ስሜ እንዳይጠፋ በማለት ተሸፍነው ለማለፍ ቆርጠዋል ። በዚህ ዓለም ላይ ራእይና ኃይል እየባከነ ነው ። ሁሉ አገር የራሱን አዋቂ ያከብራል ፣ የሌላ አገር አዋቂንም ያስመጣል ። በእኛ አገር የራሳችንን አዋቂዎች እንገፋለን ። የምንኖረው ኑሮ ደስታ የሚሰጠን ስለሚያስደስተን ሳይሆን እገሌን ስለሚያናድድ ነው ። እግዚአብሔር ለዚህ ርካሽ ፍላጎት ይህን ውድ ተፈጥሮ አልሰጠንምና ማሰብ ያስፈልገናል ። ብሽሽቅ መቀናናትን ይወልዳል ። መቀናናትም መጋደልን ይጋብዛል ። የማደርገው ነገር ትክክል ነው ወይ ? የሚል ሚዛን እንጂ እገሌን ያናድደዋል ወይ ? የሚል ጣዕመ ኃጢአትን ማራቅ ይገባናል ።
እግር እያላቸው እንዳይራመዱ ፣ እጅ እያላቸው እንዳይሠሩ ፣ አፍ እያላቸው እንዳይናገሩ ፣ አእምሮ እያላቸው እንዳያቅዱ ያደረግናቸው ሰዎች በተለያየ መንገድ ሥነ ልቡናቸውን የጎዳናቸው ምስኪኖች ናቸው ። መቼም አገርን መለወጥ ራስን ከመለወጥ ይጀምራልና በሌሎች ትችትና ስም ማጠልሸት እንዳንቆም መጠንቀቅ ያስፈልገናል ። ሁሉም ሰው በግሉ ስለ ራሱ መልስ በሚሰጥበት በእውነተኛው ዙፋን ፊት እንቆማለንና ሰዎች ስለሚሉን ነገር መጨነቅ አይገባንም ። ሰው ባደገ ጊዜ ፣ ሀብቱና ሥልጣኑ ሲደረጅ አብሮ አደጉን የሚሸሸው ብሽሽቅን በመፍራትና ክብሬን አጣለሁ ብሎ በመስጋት ነው ። አብሮ አደጋችን ትልቅ ቦታ ሲደርስ የአሁኑን ወንበር ማክበር ግዴታችን ነው ። አሊያ ምሥጢር ያወጣሉ ተብለን ሞት ሊታወጅብን ይችላል ። “በለፈለፉ ይጠፉ” ይባላል።
ያደገ ሰው አይበሻሸቅም። ከብሽሽቅ ኑሮ ካልወጣን ለአገራችን የምንመኘውን አናይም !
ይቀጥላል
ሚያዝያ 7 ቀን 2018 ዓ.ም.