“እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው ።” (ዮሐ. 15 ፡ 1)
የዘር ግንዳችን ከዚህ ይመዘዛል እያሉ ሰዎች ሲተርኩ ደስ ይላል ። በታሪክ መጻሕፍት ላይ የእርሱ ቤተሰቦች ተጠቅሰው ሲያገኝ ኩራት የሚሰማው ጥቂት አይደለም። የሚበዛው የዓለም ሕዝብ ግን የዘር ግንዱን በትክክል መናገር የሚችል አይደለም ። እስራኤላውያን በዚህ የተካኑ ናቸው ። እያንዳንዱ እስራኤላዊ ከየትኛው ነገድ መሆኑን መናገርና ወደ ኋላ መቍጠር ይችላል ። አንድን መምህር ለመቀበል የዘር ግንዱን ማወቅ ይፈልጋሉ ። አባቱንና አያቱን መናገር የማይችል በእነርሱ ዘንድ ክብር የለውም ። ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌሉን ለአይሁዳውያን እንደ ጻፈው ይታወቃል ። ክርስቶስ የዳዊት ዘርና የዳዊት ልጅ ለመሆኑ ከዳዊትና ከአብርሃም ጀምሮ የሁለት ሺህ ዓመታት የዘር ቆጠራ አድርጓል ። ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ ክርስቶስ የአዳም ልጅ መሆኑን ለመናገር የአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት የዘር ሐረግ ቆጠራ አካሂዷል (ማቴ. 1፡1-17፤ ሉቃ. 3፡23-38)።
ብዙ ልጆች በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸውን አያውቁም ። የልጅነት ጊዜያቸውን በሰላም አሳልፈው ሲያድጉ እኔ ከማን ነው የተወለድሁት ? የሚል ጥያቄ ያቀርባሉ ። በርግጥ ወላጆቻቸውን ያጡ እንጂ አሳዳጊ ያጡ አይደሉም ። ከወለደ ያሳደገ ክብሩ ትልቅ ነው ። የወለደ የእኔ የሚለውን ሲጥል ፣ ያሳደገ ግን የእኔ የማይለውን የእኔ ብሎ አሳድጓል ። እነዚህ ልጆች ወላጅ አልባ እንጂ ፈጣሪ አልባ አይደሉም ። ቢሆንም የእነዚህን ልጆች ሥነ ልቡና መጠበቅ ፣ ፍቅርን መስጠት ይገባል ። አንድ ልጅ ወላጅ ካለው የወላጁ ዕዳ ነው ፣ ከሌለው ግን የመላው ዓለም ስጦታ ነው ። የእኔ ነው የሚለው ከሌለ የእኛ ነው ማለት ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ወላጅን ካለማወቅ በላይ እግዚአብሔርን አለማወቅ ለታላቅ ድባቴ አሳልፎ ይሰጣል ። ወላጅ ያጡ ልጆችን ማሳደግ ትልቁ አምልኮ ነው ። አምልኮ አቤት አቤት ማለት ብቻ አይደለም ። የተበተነውን መሰብሰብ ትልቅ አምልኮ ነው ። የእግዚአብሔር የአፍ ብቻ ወዳጅ ላለመሆን በጎ መሥራት ይገባል ። እንኳን እግዚአብሔር እኛም የአፍ ወዳጅ እየጠላን ነው ። በአፋቸው የሚያስተዛዝኑ ፣ በእጃቸው ምንም የማይሰጡ ባለ ዱሽ እጆች መንፈሳዊ ትዝብት ላይ የወደቁ ናቸው ። ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ፡- “ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ይህ ነው ፤ ወላጆች የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ ሰውነቱን መጠበቅ ነው።” (ያዕ. 1፡ 27) ። አባት ለሌለው አባት ፣ እናት ለሌለው እናት መሆን ትልቅ አምልኮ ፣ የእግዚአብሔር ወኪል/ምስለኔ መሆን ነው ። ቆመው የሚዘምሩና የሚያዘምሩ ትልቅ አምልኮ ይህ መሆኑን ማወቅ አለባቸው ። እግዚአብሔር እጅ እግር የሌለውን ክርስትና አይወድም ። ወላጅ አልባም ፣ ሽማግሌም ብድር መመለስ የሚችሉ አይደሉም ። እውነተኛ አምልኮ ብድር መመለስ ለማይችል ቸርነት ማድረግ ነው ። ከእኩያ ጋር መገባበዝ ሳይሆን ከመከረኞች ጋር አብሮ መቍረስ እርሱ በእግዚአብሔር ፊት ንጹሕ መሥዋዕት ነው ።
ቅዱስ ዮሐንስ የንስሐ ጥምቀት ያጠምቅ ነበር ። በእርሱ ዘመንም አገሩን እንደ ወረርሽኝ የበከለው በሽታ ትዕቢት ነበር ። “በልባችሁም፡- አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ ፤ እላችኋለሁና፡- ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል” ይላቸው ነበር ። (ማቴ. 3 ፡ 9) ። የእኛ ዘመን ትምክሕት አድጓል ። ለእግዚአብሔር ከእኛ ውጭ ማን አለው ? የሚልና ሌላውን የሚንቅ የልብ ትዕቢት ውስጥ ነን ። እግዚአብሔር የሰው ድሀ የሆነ እየመሰለን ከእኛ ውጭ አማራጭ የለውም እያልን ነው ። አይሁዳውያን በልባቸው አብርሃም አባት አለን ይሉ ነበር ። የአብርሃም እውነተኛ ልጆች በሥጋ ከእርሱ የተወለዱት ሳይሆኑ በሃይማኖት የሚመስሉት ናቸው ። ሃይማኖት በዘመናት ፣ በሰማይና በምድር አንዲት ናት ። የምናምነው አብርሃም ራሱ ያመነውን ነው ፣ የምናምነው ቅዱሳን መላእክት የሚያምኑትን ነው ። በሃይማኖት አንድ ነን ። እግዚአብሔር የወደደው የአብርሃምን ሥጋዊ የዘር ሐረግ አይደለም ፣ የባረከውም እምነቱን ነው ። በአብርሃም እምነት የጸኑም የአብርሃምን በረከትይወርሳሉ ።
በጥንቱ እኔ እኮ የእገሌ ተማሪ ነኝ እያለ ተማሪው ይኮራል ። በዚህ ዘመንም ከዚህ ዩንቨርስቲ ተመርቄአለሁ ማለት ትልቅ የኩራት ምንጭ ነው ። መማር እጅግ ደስ ይላል ። አእምሮ ለማወቂያ የተሰጠን መሣሪያ ነው ። አእምሮ እውቀትን ካልሰበሰብንበት ይጎዳል ፣ ይጎዳናል ። ባዶ የሆኑ አእምሮዎች ባዶ ዓለምን ይፈጥራሉ ። ባዶነት የተጠላ ነው ። እግዚአብሔር የፈጠራት ዓለም በአእምሮ የምትመራ ናት ። አሊያ በሕገ አራዊት የበለጠ ገዳይ የበላይ ይሆንባታል ። እውቀት ግን ያልተማሩትን ለማገዝ ፣ ለምድር አስተዋጽኦ ለማድረግ እንጂ ለትምክሕት የሚሆን አይደለም ። ሁሉም አስፈላጊ ነውና ማን በማን ላይ ይኮራል ?
እነዚህ ሁሉ ትምክሕቶች እውነትነት የላቸውም ። እውነት በምድርም በሰማይም የጸናች ናት ። በእግዚአብሔር ፊት የማይቀርብን ነገር ገንዘቤ ማለት ማፈርን ያስከትላል ። በዘር ሐረጋችን ፣ በቋንቋ ጥራታችን ፣ በወላጆቻችን ትልቅነት ፣ ከፍ ባለው አስተዳደጋችን ፣ በታወቁት መምህራኖቻችን ፣ በከበረው የትምህርት ተቋማችን መመካት እውነትነት የለውም ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- “እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ ፤ ገበሬውም አባቴ ነው” አለ (ዮሐ. 15 ፡ 1) ። የዘር ሐረጋችሁን መናገር ቢያቅታችሁ ፣ ወላጆቻችሁ እነማን መሆናቸውን እንኳ በቅጡ ባታውቁ ፣ ከእገሌ መምህር የተማርኩ ነኝ ለማለት ባትበቁ አትጨነቁ ። እውነተኛው የወይን ሐረግ ክርስቶስ ነው ። ከእርሱ ጋር ለመግጠም ፣ ቅርንጫፍ ለመሆን ዛሬ ወስኑ ። በንስሐ ፣ በቅዱስ ቍርባን ከክርስቶስ ጋር ወገን ሁኑ ። የሚያኮራው ግንድ እርሱ ብቻ ነው ። አባቱን ለማያውቅ ፣ አያቱንም ለናፈቀ ክርስቶስ ትልቅ እርካታ ነው !
አንተ የአብ ልጅ ማንም የለኝም ለሚለው ሁሉን ትሆናለህ ፣ ብዙ አለኝ ለሚለው ያለኸው አንተ ብቻ ነህ ። ስመ መልካሙ ኢየሱስ ለስንቱ መልስ ነህ ! እኔም ብቸኛ ምርጫ አንተን አድርጌአለሁ ። ሲመሽ ሲነጋ የማገኝህ አንተን ብቻ ነው ። ከፍታ ዝቅታም የማያርቅህ ወዳጄ አንተ ነህ ። እስከ አዳም መቍጠር ባልችል ዘላለምን ባንተ እቆጥራለሁ ። ከሚቆጠረውና ከሚያልቀው ወደማይቆጠረው ባንተ ተሻግሬአለሁ ። አዳም ሆይ አልወቅስህም ፣ በዳግማዊ አዳም ተክሻሁ !
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም.