መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የሕይወት ራስ » የሕይወት ራስ -2

የትምህርቱ ርዕስ | የሕይወት ራስ -2

“የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት”

የሐዋ. 3 ፡ 15 ።

በጀግንነት እየመራ የሚሄድ

አርኬጎስ የሚል ስያሜ የሚያገኘው ከተማን የሚቀይስ ፣ ሕዝብን የሚያሰፍር ንጉሥ ነው ብለናል። ግሩምና ድንቅ አድርጎ የፈጠረን ክርስቶስ የሕይወታችን መሐንዲስ ነው ። አንድን ቤት የሚቀይስ ለራሱና ለጥቂት ቤተሰቡ ብቻ ያስባል ፣ ከተማን የሚቀይስ ግን ለአእላፋትና ለመጪው ዘመን ያስባል ፣ ክርስቶስም ስለ ሁላችን ያስባል ፤ የእርሱ ያልሆነ ማንም የለም ። ለሺህ ትውልድ ምሕረቱን ፣ የአባትን በረከት ለልጅ ልጁ የሚሰጥ አምላክ ነው ። ብቻውን የሚባረክ ፣ ብቻውን የሚረገም የለም ፣ ጽድቅን መምረጥ ያለብን ዘራችንም እንዲባረክና እንዲያርፍ ነው ። አንድን ከተማ የሚቀይስ ዱሩን ይመነጥራል ፣ ከአራዊት ጋር ይጋፋል ፣ እባብና ጊንጡን ያጠፋል ፣ ረግረጉን የሚረገጥ ያደርገዋል ፣ ተራራውን ሜዳ ፣ ሸለቆውንም ጉብታ ያደርገዋል ። ክርስቶስም እንደገና የመፍጠር ያህል ሕይወታችንን ሠርቶታል ። “አገር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል” እንዲሉ የበቀለብንን አሮጌ ማንነት አስወግዶታል ፣ አስፈሪውን ሞትና መቃብር ድል ነሥቶታል ። ተለሳልሶ የሚወጋውን ሰይጣንንና ሚስቱ የሆነችውን ዓለም አሸንፎአል ። የሚያስፈሩ ቀኖችን ያስደፈረን ፣ የሚያጠራጥሩ መጻኢ ዘመኖችን በእምነት እንድንጠብቅ ያደረገን እርሱ ነው ። መከራን ምክር ፣ ጉድለትን ትምህርት ቤት አድርጎልናል ። አዎ የሕይወታችን መሐንዲስ ፣ አቅኚው ፣ ከተማን ቆርቋሪው ፣ የጽዮን ሙሽራ እርሱ ክርስቶስ ነው !

የተያዘን ከተማ ፣ ቦታና ምሽግ ሰብሮ ፣ ቀድሞ ፣ ተዋግቶ ፣ በሩን ከፍቶ ለሕዝቡ የሚያስረክብ ጀግና እርሱ አርኬጎስ ይባላል ። ጀግና ሺህዎች የሚሞቱለት ሳይሆን ለሺህዎች የሚሞት ነው ። የእኛ አርኬጎስ ክርስቶስ ነጻ ፈቃዳችንን ሰጥተነው የምድር ገዥ ያደረግነውን ሰይጣን ያባረረ ፣ የተወሰደብንን ገነት ያስመለሰ ፣ በመብል ያጣነውን ክብር መብል ሁኖን እንደገና ያደለን ፣ ተዋግቶ ሞትን የሻረ ፣ ሲኦልን በኃይል የሰበረ ፣ በሩን ከፍቶ አዳምን ከነልጆቹ ያወጣ ጀግናችን እርሱ ነው ። ሺህ ገዳይ ጀግና ከሚባል ለሺህ የሞተው ክርስቶስ ጀግና ቢባል ስም ቦታውን ያገኝ ነበር ። ዛሬም ሞት ፣ መቃብርና ሲኦል እንዳያስፈራን እርሱ ሕይወታችን ፣ ትንሣኤያችንና ገነታችን ሆኗል ። በአማን አርኬጎስ !

ብዙ ምሽግ አስተሳሰብ ነበረን ። አስተሳሰባችን ፣ ፍልስፍናችን ፣ ልማዳችን ፣ ፍቅረ ኃጢአታችን ምሽጋችን ነበር ። ይህን ምሽግ በመስቀሉ ሰብሮ ያወጣን ፣ ከገዛ ምኞታችን ያዳነን እርሱ ክርስቶስ ነው ። ፊታውራሪያችን ሁኖ የቀደመልን ፣ በምስጋና ያስከተለን ፣ ውጊያውን ለራሱ ድሉን ለእኛ የቆረሰ ፣ ይኸው አገራችሁ ብሎ ገነትን ያወረሰን እርሱ የእኛ አርኬጎስ ነው ። ብዙዎች ከሚሞቱ እኔ ልሙት ብሎ የመጣ ፣ መሥዋዕት ያቀረበ ሊቀ ካህን ሳይሆን መሥዋዕት የሆነልን ሊቀ ካህን እርሱ ክርስቶስ ፣ የአንደበታችን ጣዕም ፣ የድንግል ልጅ ነው ። ካህኑም እርሱ ፣ መሥዋዕቱም እርሱ ፣ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመለኮቱ ተወካፌ መሥዋዕት/መሥዋዕት ተቀባዩም እርሱ ሁኖ አድኖናል ። “ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና ፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን ፤ አሜን ።” ይላል ። ሮሜ. 11 ፡ 36 ። ከእርሱ ሲል የአሳብ መነሻ የምክር ጀማሪው እርሱ ነው ። በእርሱ ሲል አድራጊው ፈጻሚው እርሱ ነው ። ለእርሱ ሲልም የሥራውን ምስጋና ፣ የበጎነቱን ክብር ተቀባይ እርሱ ብቻ ነው ማለት ነው ። ሰውን ቢያመሰግኑት ለጊዜው ነው ። “የፊት ምስጋና ለኋላ ሐሜት ያስቸግራል” እንዲሉ ያመሰገኑት ሳይረግሙት አይቀርም ። ለእርሱ ግን ለዘላለም ክብር ይሁን ተብሎአል ። አሜን ይሁን ።

 

ሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ