መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የሕይወት ራስ » የሕይወት ራስ -1

የትምህርቱ ርዕስ | የሕይወት ራስ -1

“የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት”

የሐዋ. 3 ፡ 15 ።

ቅዱስ ጴጥሮስ የሕይወት ራስ ብሎ የገለጠውን ግሪኩ አርኬጎስ ይለዋል ። አርኬጎስ የሁለት ቃላት ጥምር ነው ። አርኬ ማለት መጀመሪያ ፣ መነሻ ፣ ዋና መሠረት ፣ ባለቤት ፣ አመንጪ ፣ ዋና መሪ ፣ ካፒቴን ማለት ነው ። በዮሐ. 1 ፡ 1 ላይ “በመጀመሪያ” የሚለው ቃል አርኬ ተብሎ ተጠርቷል ። ጎስ ማለት መሪ ፣ አስተባባሪ ፣ የሚነዳ ፣ ወደፊት የሚያደርስ ፣ ከፋች ማለት ነው ። አርኬጎስ ማለት በአማርኛው እንደ ተገለጠው የሕይወት ራስ ማለት ሲሆን ጀማሪ ፣ መሪ ፣ አለቃ ፣ አዛዥ ማለት ነው ። አርኬጎስ መጀመሪያ የሚመሠርት ፣ መንገድ አይቶ የሚመራ ፣ በርን ከፍቶ የሚያስገባ ማለት ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርኬጎስ ተብሏል ። እርሱ የሁሉም ፍጥረት መገኛ ነው ። በእርሱ መሠረትነት ላይ ሕይወት ያለው ፍጥረት ተደግፏል ። ወደ ሕይወት ግብ ለመድረስ እርሱ አማራጭ ሳይሆን ብቸኛ ምርጫ ነው ። ሰው ሆነን እንድንፈጠር ፣ ከውድቀት እንድንነሣ ፣ የተውነውን የጽድቅ ጉዞ እንደገና እንድንጀምር መሠረት ሆኖናል ። የሚታየውንና የማይታየውን ዓለም ፈጥሯል ። ባለቤት ያለው ቤት አይደፈርም ፣ እርሱን መካድ ባለቤት የሌለው ዓለም መፍጠር ነው ። የሚታየው የዓለም ዝርዝርክ ፣ የሰው ልጅ መንገድ ጠፍቶት መንከራተት ከተባረከው አርኬጎስ የመለየት ውጤት ነው ። የተዘጋውን የገነት በር በደሙ የከፈተ ፣ ወንበዴን ይቅር ብሎ የመጀመሪያ ተጋባዥ ያደረገ ፣ ለምሕረቱ ልክ ፣ ለይቅርታው ወሰን የሌለው ዛሬ የምንሰብከው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ።

የጥንት ግሪኮች አርኬጎስ ብለው የሚሰይሙት ጀግኖቻቸውን ነው ። እነዚህ ጀግኖች እነማን ናቸው ብለን መጠየቅ አለብን፡-

የከተማ መሥራች

ዱር መንጥሮ ፣ መንገድ ቀይሶ ፣ ንድፍ አውጥቶ የሚጀምር ፣ ሕዝብንም የሚያሰፍር የከተማ መሥራች አርኬጎስ ተብሎ ይጠራል ። ቅዱስ ጴጥሮስ አርኬጎስ ብሎ ሲጠራው የአዲሲቷ ኢየሩሳሌም መሥራች መሆኑን እየገለጠ ነው ። ከሁሉ በላይ የሕይወታችንን ከተማ ዱሩን አስተሳሰብ በመመንጠር ፣ ድንግዝግዝ የሞላበትን ጫካ መንገድ በመስጠት ፣ መልክ ያልነበረውን ማንነት ባለመልክ በማድረግ ያስተካከለ አለቃ ነው ። እርሱ ጀማሪና ፈጻሚ ነው ። በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ ብሎ የነገረን ውብ ከተማን የሠራልን ነው ። እውነተኛውን ኑሮ እንድንጀምር ያደረገን ፣ ከመመሳሰል ሕይወት ያወጣን ፣ በስሙ የተጠራነውን አንድ ያደረገን ፣ የሕዝቦች ጠበቃ ፣ የአእላፋት አሳዳሪ ነው ። በርግጥም አርኬጎስ ነው ።

ይቀጥላል

ሰኔ 20 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ