መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የኃጢአት ስሞች » የኃጢአት ስሞች -6

የትምህርቱ ርዕስ | የኃጢአት ስሞች -6

“ከመድኃኒቱ አጣላው” ይባላል ። መካሪውን ሲሸሽ ፣ ከሚወደው ሰው ሲርቅ ከመድኃኒቱ አጣላው የሚባለው ነገር ይደርሳል ። ቤተ ክርስቲያን ማልቀሻ ቦታ ፣ መጽናኛ ስፍራ ናት ። ከእግዚአብሔር ቤት የራቀ ፣ ንስሐን የጠላ ፣ ቅዱስ ቍርባንን የሸሸ ከመድኃኒቱ የተጣላ ነው ። የሰው ልጅ ተፈጥሮ ከጠላቱ ጋር የሚወዳጅ ፣ የሚያርደውን የሚከተል ነው ። ለኃጢአት ሞኝ የሆነው ሰው ለንስሐ ግን ብልጥ ይሆናል ። ሰዎች የእግዚአብሔርን መኖር የሚጠራጠሩት ፣ የክርስቶስ ተቃዋሚ የሚሆኑት ከልባቸው አይደለም ፣ ክርስትና ንስሐን ወይም መመለስን የሚጠይቅ ሃይማኖት ነውና ከዚያ ለመሸሽ ብለው ነው ። በርግጥም ሰው ከመድኃኒቱ ይጣላል ፣ ከመድኃኒቱ ከተጣላ በምን ይድናል ( እግዚአብሔር አማራጭ የሚሰጥ አምላክ አይደለም ፣ ይህ ካልተስማማህ ያኛው ይቀየርልህ አይልም ። ወደ እግዚአብሔር የምንገባበት በሩ ንስሐ ነው ። ሰው ለመዳን በሽታውን ማመን አለበት ። ቤተ ክርስቲያን በጠባይዋ ቤተ ሕሙማን ናት ። መድኃኒትዋም ንስሐና ደመ ኢየሱስ ነው ።

እግዚአብሔር በአደባባይ ለልባችን ይናገራል ። ሰባኪው አፈ ክርስቶስ አፈ ንጉሥ እንደሆነ እናምናለን ። ለሚሊየኖች በሰባኪ አንደበት ሲናገር መልእክቱ የሚደርሰን ግን በግላችን ነው ። ከአንድ ሰዓት ስብከት አንድ ሺህ ሰው በቀጥታ ለእርሱ የተላከውን መልእክት ይወስዳል ። ሰባኪው በአደባባይ ሲናገር መልእክቱ ያንተ ነው ብሎ የሚያከፋፍለው ሁሉን ቻይ የሆነው ፣ ለልብ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ ነው ። አምላካችን የሚገልጥ እንጂ የሚያጋልጥ አይደለም ። ብዙ ምእመናን የንስሐን ትምህርት አይፈልጉም ፣ ብዙ ሰባኪዎችም የሰውን ስሜት እያዳመጡ የንስሐ ስብከት መስበክ አቁመዋል ። የንስሐ ስብከት ሲደረግም ትችት የሚያሰሙ ፣ አበዛችሁት ብለው የሚሳደቡ ምእመናንም ተፈጥረዋል ። የጉድ ዘመን ዕለቱ ዓመት ነውና ይኸው አላልቅ ብሎ እንደ ቆዳ ያለፋናል ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ስብከቱ ንስሐ ነው ። “ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ፦ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር።” ማቴ. 4 ፡ 17 ።

የመጥምቁ ዮሐንስም የስብከቱ መጀመሪያና መጨረሻ ንስሐ ግቡ የሚል ነበር ። ክርስቶስ አምላካችን ፣ ቤዛችንና አርአያችን ነው ። እርሱን ተከትለን ንስሐን መስበክ ይገባናል ። የንስሐ መንፈስ በሕዝብ ላይ ካልታየ በግል ማረፍ ፣ በአገር በሰላም መኖር አይቻልም ። ንስሐ ይቅር መባባልን ያመጣል ፣ ሰውን ከክፋት ወደ ደግነት ይለውጠዋል ። የእግዚአብሔርን ምሕረት የማያሳይ የንስሐ ስብከት በሽታውን አሳውቆ መድኃኒቱን መደበቅ ነው ። ኃጢአቱን አምኖ የእግዚአብሔርን ምሕረት ያልተቀበለ ሰው እንደ ይሁዳ ይሆናል ። ይሁዳ በደሉን አመነ ፣ ንስሐ ግን መግባት አልፈለገም ፣ በዚህ ምክንያት ራሱን አጠፋ ። ንስሐ የምንለው የሰው መመለስና የእግዚአብሔር ይቅርታ ማድረግ ድምር ነው ። ወፍ በአንድ ክንፍ አትበርም ፣ ንስሐና የእግዚአብሔር ምሕረት የተያያዙ ናቸው ። እምነት የምንለው ሁለት ነገሮችን ከልብ ማመን ነው ። ፍጹም ኃጢአተኛ መሆንን ማመንና ፍጹም መሐሪ መሆኑን አምኖ ወደ እግዚአብሔር መጠጋት ነው ።

ኃጢአት የተለያዩ ስሞች አሉት ። አንዱ ዓመፃ የሚል ነው ። ሐዋርያው፡- “እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤” ይላል ። ሮሜ. 1፡18 ። እግዚአብሔርን ለማወቅ አለመፈለግ ትልቅ ኃጢአት ነው ። ቃሉን ትቶ በሕሊና የሳሉትን አምላክ መከተልም ስህተት ነው ። እኔ አዋቂ ነኝ ስለ እግዚአብሔር መስማት አያሻኝም ማለት የበደል ከፍታ ነው ። እውቀት የሚጀመረው ከፈሪሀ እግዚአብሔር ፣ ጥበብም ሙሉ የሚሆነው በእምነት ነው ። ሰው እግዚአብሔርን ካላወቀ በራሱ ላይ የበላይ ሊሆን አይችልም ። ገበሬ የተወው ማሳ የማይበቅልበት አረም እንደሌለ እግዚአብሔርን ያልተጠጋ ሰውም የማይሰለጥንበት ነውር የለም ።

ለእግዚአብሔርና ለመንግሥቱ አልገዛም የሚል እምቢታ እርሱ ኃጢአት ወይም ዓመፃ ይባላል ።

ይቀጥላል

ሰኔ 19 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ