የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ /15

/አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ ኧረ እባካችሁ አንብቡ !!!/
ክርስቲያኖች በድምጥያኖስ ዘመን /81-96 ዓ.ም./
ከሮማ ቄሣሮች በክርስቲያች ላይ ስደት በማስነሣት የሚታወቀው ኔሮን ቄሣር መሆኑን አይተናል ። ኔሮን ቄሣር ሙዚቀኛና ዘፈን ወዳድ ነበር ። ከእርሱ በፊት የነበረውን ቀላውዴዎስ ቄሣርን እናቱ በመርዝ ገድላለት ሥልጣን ስለያዘ ሁሉን ተጠራጣሪ መሆን ጀመረ ። በክርስቲያኖች ላይ ብዙ እንከን ቢፈልግም ምንም ሊያገኝ አልቻለም ። ቤተ መንግሥቱን ለማስፋትና ለእብደቱ እፎይታን ለማግኘት በ64 ዓ.ም የሮምን ከተማ በእሳት አጋይቷታል ። ይህን ያደረጉት ክርስቲያኖች ናቸው በማለት ሕዝቡን ተበቀሉ ብዙ አዋጅ ነገረ ። በእርሱ ዘመን ክርስቲያን የሆኑ ሮማውያን ዜግነታቸውን ተነጠቁ ። ክርስቲያኖች ሰም እንዲጠጡና ሰም ተነክረው እንደ መብራት እንዲያበሩ ተደረገ ። ከአንበሳ ጅራት ጋር ክርስቲያኖች ታሰሩ ። ብዙ እብድ ውሾች ተዘጋጅተው ክርስቲያኖች እንዲለከፉ አደረገ ። አብደው ቅስማቸው ተሰብሮ እንዲሞቱ ይህን ክፋት ቀየሰ ። በኔሮን ቄሣር ዘመን በእሳት መቃጠል ቀላሉ የመግደያ ዘዴ በመሆኑ በዚህ የሞተ እንደ ዕድለኛ ይቆጠር ነበር ።

ከኔሮን በኋላ አንድ አንድ ዓመት ሁለት ቄሣሮች ቢነግሡም በመጨረሻ ቬስፓስያን ነገሠ ። እርሱም በልጁ በቲቶ አማካይነት ኢየሩሳሌምንና መቅደሱን አፈረሰ ። ከዚያ በኋላ በተነሡት በአምስት ቄሣሮች ዘመን የጎላ መከራ በክርስቲያኖች ላይ አልታየም ነበር ። የቬስፓስያን ልጅ ፣ ኢየሩሳሌምን ያፈረሰው የቲቶ ወንድም ድምጥያኖስ ከ81-96 ዓ.ም ቄሣር ሁኖ ነገሠ ።
ሮማውያን፡- “አዲስ ኅብረትና ክብ ሲያዩ ይፈራሉ ፣ ቀነናውያንንም ያስባሉ” ይባላል ። በዚህ ምክንያት የክርስቲያኖችን ስብስብ አልወደዱትም ። ክርስቲያኖችም የአይሁድ እምነት ሌላኛው ክፍል እንደሆኑ ያስቡ ነበር ። ክርስትና ራሱን ችሎ የሚቆም በብሉይ ተስፋና በአዲስ ኪዳን ፍጻሜ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያወቁት ዘግይቶ ነው ። ክርስቲያኖች የሮማን ግዛት ለማወክ በአይሁድ ተልእኮ ተሰጥቷቸው ወደ ዓለም እንደ ወጡ ቄሣሮች ያስቡ ነበር ። ይህን ከሚያስቡ አንዱ ድምጥያኖስ ነበር ።

ሮማውያን በሰሜን እስከ ጀርመን ሸለቆ ፣ በምዕራብ እስከ ፈረንሳይ ፣ በሰሜን ምሥራቅ ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ ፣ በደቡብ ሜዲትራንያን የሚያዋስናቸው አገሮችን ሰሜን አፍሪካን ጨምሮ አምስት የሰሜን አፍሪካ አገሮችን ይገዙ ነበር ። እንግሊዝ ግሪክም የግዛታቸው አካል ነበሩ ። ታዲያ የዚህ ሁሉ ገዥ አምላክ መባል ይገባዋል ። ቄሣሩ ከአማልክት አንዱ ነው ፣ ስግደት ይገባዋል የሚል አዋጅ ማስነገር ጀመሩ ። ጢባርዮስ ቄሣር ራሱን “የአምላክ ልጅ ነኝ” እያለ ይጠራ ነበር ። “የአምላክ ልጅ አምላክ ነው” በማለትም መናገር ጀመረ ። ይህን ተከትሎ ድምጥያኖስ “ጌታና አምላክ – Lord and God” እያለ ራሱን መጥራት ጀመረ ። ክርስቲያኖች፡- “ኢየሱስ ጌታ ነው” ይሉ ስለ ነበር ከቄሣሮች ጋር በቀጥታ መጋጨት ውስጥ ገቡ ።
ከቬስፓስያን እስከ ድምጥያኖስ የመጨረሻ የሥልጣን ዓመታት ድረስ በነበሩት 27 የዕረፍት ዓመታት ክርስትና በቤተ መንግሥት ውስጥ ገብቶ ነበር ። ከተራው ሕዝብ ባሻገር ልዑላኑና ልዕልቶች ወደ ክርስትና እየመጡ ነበር ።ድምጥያኖስም ፍላብየስ ክሌመንተስ የሚባለውን ዘመዱን ክርስቲያን ነህ ብሎ አስገድሎታል ። ሚስቱ ፍላብያ ወደ ግዞት ተልካለች ። ለክርስቲያኖች የሰጠችው ርስቷም ለግባ መሬት ክርስቲያኖች ይጠቀሙበት ነበር ።
ድምጥያኖስ የራሱን ምስል አሠርቶ እንዲሰገድለትና እንዲመለክ ወደ ኤፌሶን ልኮ ነበር ። ይህንን የግብዝነት ተግባር ወንጌላዊው ዮሐንስና ክርስቲያኖች በግልጽ ተቃወሙ ። ዮሐንስም ተከስሶ ወደ ደሴተ ፍጥሞ እንዲጋዝ ተወሰነበት ። የአዲስ ኪዳን የመጨረሻ መጽሐፍና ብቸኛ የአዲስ ኪዳን የትንቢት መጽሐፍ የሚባለውን “ራእየ ዮሐንስ”ን የጻፈው በዚህ በፍጥሞ ደሴት ነው ። ድምጥያኖስ ከአባቱና ከወንድሙ በወረሰው የአይሁድ ጥላቻ ምክንያት ክርስትና በአይሁዶች የተመሠረተና የሮማን ግዛት ለማፍረስ የተሰባሰበ የፖለቲካ ስልት እንደሆነ ያስባል ። ግምጃ ቤቱም ተሟጦ ስለነበር አይሁዳውያን በኢየሩሳሌም ላለው መቅደስ ባሉበት አገር ሁነው ሁለት ዲናር የመገበር ልማድ ነበራቸውና ይህ ስጦታ ለእርሱ እንዲደረግ ማስገደድ ተያያዘው ። ክርስቲያኖችንም አማልክትን ስለማይቀበሉ “ሃይማኖት የለሽ” እያለ ይጠራቸው ነበር ። የክርስቲያኖችንም ንብረት እንዲወረስ ፣ ወደ ግዞት እንዲላኩም አዝዞ ነበር ። ክርስትና ባሪያና ጨዋ የሚል ልዩነት አልነበረውምና ከባሮች ብዙዎች ጳጳስ ሆኑ ። በሮም ውስጥ ከሚኖሩት ሰዎች ከግማሽ በላይ ባሮች ነበሩና ይህ ተግባር የሮም ቄሣሮችን ማወክ ጀመረ ። በ96 ዓ.ም በተነሣው የፖለቲካ ጠብ ድምጥያኖስ ተገደለና በምትኩ ለክርስቲያኖች ነጻነትን ያወጀው ፣ ወንጌላዊ ዮሐንስን ከግዞት የፈታው ፣ ለሁለት ዓመታት የነገሠው ኔርቫ ነገሠ ።
አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መምህራን ዘመነ ሐዋርያት የሚሉት ከ33-70 ዓ.ም ያለውን ነው ። የመጨረሻው ሐዋርያ ወንጌላዊ ዮሐንስ የመጀመሪያውን ምእተ ዓመት ስለፈጸመና እስከ 98 ዓ.ም በሕይወት ስለነበረ ዘመነ ሐዋርያት እስከ 100 ዓ.ም ነው የሚሉም አሉ ። ዘመነ ሰማዕታት ተብሎ የሚጠራው 160-312 ዓ.ም. ያለው ጊዜ ነው ። የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ግን ዘመነ ሰማዕታት የምትለው 284-313 ዓ.ም. ነው ። ምዕራባውያን ደግሞ ከ96-113 ዓ.ም ያለውን ዘመነ ሰማዕታት ይሉታል ። ከድምጥያኖስ እስከ ዶቅልጥያኖስ ዘመን ማለት ነው ። የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ከዶቅልጥያኖስ ዘመን ጀምራ ዘመነ ሰማዕታት ትላለች ። ዶቅልጥያኖስ 284-305 ዓ.ም. በሥልጣን የቆየ ቄሣር ነው ። ክርስትናን ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ ብሎ የፎከረ ሲሆን ማጥፋት አቅቶት ክርስትና ወደ ቤቱ ስለገባ ተጨንቆ ሥልጣን ለቀቀ ። ታዲያ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ የመከራ ዘመን የነበረውን ዘመነ ዶቅልጥያኖስን ዘመነ ሰማዕታት በማለት እንደ ዘመን መጀመሪያ አድርጋ ወስዳው ነበር ። ኋላ ላይ ግን፡- “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ቸርነት አድርጎልናል ፣ ከቸርነቱ አንጻር መከራው ትንሽ ነው ፤ መከራን ሁልጊዜ ለምን እናስታውሳለን ? ወደ ተደረገልን ቸርነት እንመለስ” ብለዋል ። ዘመነ ሰማዕታትን ግን ያስቡታል ።
ኔሮን ቄሣር በሮም ላይ ክርስቲያኖችን ሲያሳድድ ድምጥያኖስ ግን በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖችን ያሳድድ ነበር ።
ይቀጥላል
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ