የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ /16

/አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ ኧረ እባካችሁ አንብቡ !!!/
የትራጃን ዘመን ስደት
ኔርቫ የክርስቲያኖችን ስደት ያስቆመ ፣ በፍጥሞ ደሴት ታስሮ የነበረውን ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስን ያስፈታ ቢሆንም የሥልጣን ዘመኑ ግን ከ96-98 ዓ.ም ብቻ የዘለቀ የሁለት ዓመት ንግሥና ነበር ። ከእርሱ በኋላ የነገሠው ትራጃን የተባለው ቄሣር ነው ። ትራጃን የነገሠው ከ98-117 ዓ.ም ድረስ ነበር ። ትራጃን ሁለት ዓይነት መልክ የነበረው በስልትና በጭካኔ ክርስቲያኖችን ያሳደደ ንጉሥ ነው ። ትራጃን በሮማውያን ዘንድ የተወደደ ቢሆንም የክርስቲያኖችን ስደት ግን ያፋፋመ ነበር ። በግዛቱ ውስጥ ማንኛውም የሃይማኖትና የሌላም ስብስብ ስለተከለከለ በግዛቱ ውስጥ ክርስቲያኖች በግልጽ ሆነ በስውር ማምለክ አልቻሉም ። ሕዝቡም በክርስቲያኖች ላይ ነጻ እርምጃ እንዲወስድ መንገድ ከፈተ ። ይህ ስደትም በፍልስጤም ፣ በአንጾኪያ፣ በቢታንያና በጳንጦስ ፣ በፊልጵስዩስ በርትቶ ነበር ። ቢታንያና ጳንጦስ በቀጥታ በቄሣር ሥር የሚተዳደሩ ነበሩና የቄሣሩ እንደራሴ የነበረው ወጣቱ ፕሊኒ በክርስቲያኖች ምክንያት እየመጣ ያለውን ችግር ዘርዝሮ ለትራጃን ጽፎለት ነበር ። ፕሊኒ የክርስትና ሃይማኖት አማልክት የለሽ በመሆኑ አምላክ የለሾች ናቸው ፣ የጣዖታት ቤቶች መመናመናቸውም ፣ ሃይማኖቱ በቀላሉ እየተስፋፋ መምጣቱን ፣ ገልጾ በዚህ ምክንያት በሞት እንዲቀጡ የሚገልጥ ደብዳቤ ጻፈለት ።  ትራጃን ግን የሰጠው ምላሽ ክርስቲያኖች ነጻ እርምጃ እንዳይወሰድባቸው ፣ ተይዘው ክርስቲያን መሆናቸው ከተጣራ ግን እንዲቀጡ ፣ ለአማልክትም ሰግደው ይቅርታ ከጠየቁ እንዲለቀቁ የሚል ማርና እሬት የቀላቀለ መልስ ሰጥቶታል ። ይልቁንም ክርስቲያን የሚለውን ስማቸውን ትተው ለአማልክት ከሰገዱ ያለፈው ስህተታቸው ሁሉ በይቅርታ እንደሚታለፍላቸው ገልጾ በዘዴ እምነቱን ማስጣል እንችላለን የሚል መልእክት አስተላልፏል ። ትራጃን ክርስቲያኖችን የአማልክትና የቄሣር ጠላቶች በማለት ይጠራቸው ነበር ።

በትራጃን ዘመን በሰማዕትነት ያለፉት የኢየሩሳሌሙ ቅዱስ ስምዖን ፣ የአንጾኪያው አግናጥዮስና የሮሙ ቀለሜንጦስ ናቸው ።
የሀድርያን ዘመን
117-138 ዓ.ም. የነገሠ ሲሆን ከትራጃን ለየት ያለ ጠባይ ታይቶበታል ። ሕዝቡ እንግዳ ሃይማኖት በማለት ክርስቲያኖች እንዲጠፉ ሲጠይቅ ሐድርያን የሰጠው ትእዛዝ ግን ያለ በቂ ምክንያት ክርስቲያን በመሆናቸው አይቀጡም ፣ ተከሰው ሲቀርቡ ራሳቸውን የመከላከል መብት አላቸው ፣ ክርስቲያኖች ላይ ሐሰተኛ ክስ የመሠረቱ በሕግ ይቀጣሉ ፣ የክርስቲኖች ምላሽ የአገሪቱን ሕግ ከተቃረነ ይቀጣሉ የሚል ነበር ። ቢሆንም ነጻ እርምጃዎች ቢቀሩላቸውም ለቄሣሩ የማይሰግዱና አምልኮ የማያቀርቡ ከሆነ ይቀጣቸው ነበር ።
ከ138-161 ዓ.ም የነገሠው አንቶንዮስ ፒዩስ የሐድርያን የጡት ልጅ የነበረ ሲሆን እንደ ቀደሙት ቄሣሮች ክርስቲያኖችን ላይ እርምጃ ባይወስድም ሕዝቡ ግን መናፍቃን የሚላቸውን ክርስቲያኖች ላይ በግብታዊነት እርምጃ ሲወስድ በዝምታ የተመለከተ ነው ። አንቶንዮስ ፒዩስ ለሮም አማልክት ቀናተኛ ከመሆኑም በላይ ራሱን እንደ ሊቀ ካህናት በመቊጠር መሥዋዕት የሚያቀርበው ራሱ ነበር ። ሮማውያንም ጻድቅ ንጉሥ ብለው ሰይመውት ነበር ። በ155 ዓ.ም. ፖሊካርፕ በሰማዕትነት የሞተው በእርሱ ዘመን ነው ። 12 ክርስቲያኖች ሕዝብ በተሰበሰበበት የትርኢት ሥፍራ ክርስቲያኖች ለአንበሶች ተጥለው ሳለ አንዱ ክርስቲያን እምነቱን ክዶ ለአማልክት ስለሰገደ ሰማዕትነት አምልጦታል ። በዚሁ በአንቶንዮስ ዘመን የኢየሩሳሌሙ ኤጲስ ቆጶስ አባ ማርቆስና የሮሙ ፖፕ ሃይጂኑስ ተገድለዋል ፤ የፖፑ ምትክ ሁነው የተሾሙ ፖፕ ፓይያስ ቀዳማዊ በሰማዕትነት አርፈዋል ።
ማርቆስ አውሬልዮስ ከ168-180 የነገሠ ቄሣር ነው ። ይህ ሰው ክርስቲያኖችን “ሞገደኞችና ወፈፌዎች ናቸው” በማለት ይጠራቸው ነበር ። ይህ ንጉሥ እጅግ የተማረ ስለነበር ፈላስፋው እየተባለ ይጠራል ። የክርስቲያኖችን ትምህርት የሚጠላ ሲሆን የሮም አማልክትንም አይቀበልም ነበር ። የአይሁድን ሃይማኖት ግን አንድ አምላክን ስለሚያመልኩ እቀበለዋለሁ ይላል ። የአይሁድ ሃይማኖት ከአይሁዳውያን ውጭ ስለማይወጣ አሕዛብም አይሰጉትም ነበር ፤ ክርስትና ግን አሕዛብንም የራሱ ስለሚያደርግ ጥላቻ አትርፎአል ። በእርሱ ዘመንም ታላቅ ስደትና መከራ ተነሥቷል ። ወደ ሥልጣን የወጣው ፋርስ በሮም ላይ ጦርነት በከፈተችበት ዘመን በመሆኑ በዘመኑም የምድር መናወጥና አስከፊ ረሀብ ተነሥቶ ስለነበር ሕዝቡ ይህ ሁሉ የሆነው ክርስቲያኖች አማልክትን ስላስቆጡ ነው በማለቱ ታላቅ ዓመፅ ስለተነሣበት ፣ ዓመፁን ለማስቆምና ጥላቻውንም ለመግለጥ ክርስቲያኖች እንዲገደሉ አድርጓል ።
ዘመነ ሰማዕት በማለት አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች የሚጠሩት ይህን ከ160-312 ዓ.ም ያለውን ጊዜ ነው ። ከዚህ በፊት የነበሩት ስደቶች በሁሉም የሮም ግዛት የተፈጸሙ ሳይሆን በአንዳንድ ግዛቶች የተፈጸሙ ነበሩ ። ከዚህ ጊዜ በኋላ ግን በሁሉም የሮም ግዛቶች ክርስቲያኖች አለቁ ፣ መጻሕፍት ተቃጠሉ ፤ ስለዚህ ዘመነ ሰማዕታት የሚል ስያሜ ተሰጠው ።
ኮሞዶስ 180-192 ዓም . የነገሠ ሲሆን የማርቆስ አውሬልዮስ ልጅ ነው ። እንደ አባቱ የክርስቲያኖችን ስደት ቢያፋፍምም ከ300 እቁባቶቹ አንዷ ይህን በመቃወሟ ስደቱ ቆመ ፣ ለሃያ ዓመታትም የክርስቲያኖች መከራ ጋብ አለ  ። ይህች ሴት ማርሲያ የተባለች ባሪያ ስትሆን ለአገልግሎት ወደ ቤተ መንግሥት ተወስዳ ሳለ የኮሞዱስ አገልጋይ ሆነች ። እርሱ ግን እጅግ ስለወደዳት እቁባቱ አደረጋት ። በጣምም ይወዳት ስለነበር እርስዋም ክርስቲያን ስለሆነች ስደቱ እንዲቆምና በግዞት ያሉ እንዲፈቱ አደረገ ።
እስክንድሮ ሳዊሮስ 222-235 የነገሠ ፣ ፊልጶስ ዐረባዊ 244-249 የነገሠ ሲሆን እነዚህ ቄሣሮች ክርስቲያኖችን ተጽይፈው ንቀው ብዙ መከራ አላመጡባቸውም ። ታላቁ የመከራ ዘመን የጀመረው በዳክዮስ ዘመን ነው ።
ይቀጥላል
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ