መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የኃጢአት ስሞች » የኃጢአት ስሞች -2

የትምህርቱ ርዕስ | የኃጢአት ስሞች -2

ኃጢአት ማለት ማጣት ማለት ነው ። የእግዚአብሔርን አባትነት ፣ የቅዱሳንን ኅብረት ፣ የመንግሥተ ሰማያትን ርስት ማጣት ማለት ነው ። ኀጥእ ማለት አግኝቶ ያጣ ማለት ነው ። ኃጢአት የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ቋንቋ “ዓላማ መሳት” የሚል ትርጉም አለው ። ይህም የተፈጥሮ ዓላማን መሳት ማለት ነው ። ሰው ለጽድቅ ፣ ለእግዚአብሔር ፈቃድ ተፈጥሮአልና ራሱን በኃጢአት ውስጥ ሲያገኘው ዓላማውን ስቷል ማለት ነው ። እግዚአብሔር በሰው ላይ ዓላማ አለው ፣ ሰው በራሱ ላይ ካለው ዓላማ እግዚአብሔር በሰው ላይ ያለው ዓላማ ይበልጣል ። ሰውም ራሱን ያልፈጠረ ፣ በእግዚአብሔር ዓላማ የተፈጠረ ነው ። ሰው ከመፈጠሩ በፊት ክፋት በፍጥረት መካከል ተገኝቶና ሰልጥኖ ነበር ። ያም ክፋት የሰይጣን ክፋት ነው ። ሰውን ሲፈጥረው ክፋት በተገኘበት ዓለም ነውና ትእዛዝን መስጠት ነበረበት ። ሰው ግን ከተፈጥሮ ዓላማ ፣ ከሕጉ ማስጠንቀቂያ አፈንግጦ በኃጢአት ወደቀ ። በዚህም አግኝቶ ያጣ ሆነ ። እግዚአብሔርን አግኝቶ ነበር አጣ ፣ ገነትን አግኝቶ ነበር አጣ ፣ እውቀትን አግኝቶ ነበር አጣ ።

ኃጢአት ከእግዚአብሔር አባትነት ይለያል ። እግዚአብሔር ፈጣሪ ፣ አባት ፣ ንጉሥ ነው ። ይህን ዓለም ያስገኘ ፣ በርኅራኄው የሚመግብ ፣ በንጉሥነቱ የሚያስተዳድርና የሚቀጣ ነው ። በምድር ያሉ አባቶች ንግሥና ቢኖራቸው ፈጣሪነት ግን የላቸውም ። ደግሞም አባትነትም ፣ ንጉሥነትም በጸጋ የተቀበሉት እንጂ በባሕርይ ያገኙት አይደለም ። ደግሞም በአንድ ዘመን ልጅ የነበሩ ቆይተው አባት ይሆናሉ ፣ እግዚአብሔር ግን በዕድገት አባት አልሆነም ። አባት የሚባሉትም አባት አላቸው ። እግዚአብሔር ግን በመኖር የሚቀድመው ማንም የለም ። በአፍአዊ ግብር የሁላችን አባት ነው ። በሥላሴ ውሳጣዊ ግብር ግን አብ አባት ፣ ወልድ ልጅ ነው ። አፍአዊ ግብር የምንለው እግዚአብሔር በአንድነቱና በጸጋው ለፍጥረት የሚያደርገው ቸርነት ነው ። እርሱ የእኛ አባት ተብሎ ሲጠራ እኛንም ልጆቼ ሲለን አላፈረብንም ። እኛ በሰካራም ዘመዳችን ፣ ድሪቶ በለበሰው ወንድማችን እናፍራለን ። እግዚአብሔር ግን በማንም የማያፍር ፣ ክብሩን ሊያካፍል የሚጠራን ነው ። እኛ ውጫዊ ማንነትን በማየት ሰውን እንቀርባለን ፣ እንርቃለን ፤ እግዚአብሔር ግን ልብን የሚያይ ፣ ከልብ ጋርም የሚያብር ነው ። አዳም ኀጥእ ወይም ያጣ በሆነ ጊዜ ገነት ነበረችው አሁን አጣ ፣ ቅድስና ነበረው አሁን አጣ ፣ ልጅነት ነበረው አሁን አጣ ፣ ነቢይነት ነበረው አላዋቂ ሆነ ፣ የእግዚአብሔርን ድምፅ ይሰማ ነበር ፣ አሁን ራቀው ። በዚህ ዓለምም ኃጢአት ብዙ ነገሮችን ያሳጣል ። ሰላምን አሳጥቶ ጦርነትን ይወልዳል ፣ ሕይወትን አሳጥቶ ሞትን ያመጣል ። ሦስቱንም የሰውነት ክፍሎች ይጎዳል ። ሥጋን በበሽታ ፣ በወንጀል ፣ በእስራት ፣ በሱስ ይቀጣል ። ነፍስን በክፉ ምኞት ፣ በሁከትና በብቸኝነት ያንገላታል ። መንፈስን ከንጹሕ ምንጭ ፣ ከአምልኮተ እግዚአብሔር ፣ ከፍቅር ያራቁታል ። ሁሉንም ኪሣራዎች በአንድ ጊዜ የሚያመጣ ቢኖር ኃጢአት ነው ።

ዘመናዊው ሰው ኃጢአትንና እግዚአብሔርን ለማስታረቅ በብርቱ ይታገላል ። ጌታችን በመስቀል ላይ ኃጢአተኞችን ከአባቱ ጋር አስታረቀ እንጂ ኃጢአትን ከራሱ ጋር አላስታረቀም ። ሰዎች ኃጢአትን በመከልከላቸው ነጻነታቸው እንደ ተጎዳ ፣ በራሳቸው ማዘዝ እንደማይችሉ እንዲሰማቸው አድርጓል ። እግዚአብሔር ኃጢአትን የከለከለው ለሥልጣኑ ሰግቶ ፣ ወይም ቅድስናው የሚጎዳ ሁኖ አይደለም ። የሰው ልጅ የተሟላ ሰላም የሚያገኘው በጽድቅ ስለሆነ ነው ። እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር የገለጠው ሕግን በመስጠቱ ነው ። የምንወደውን እናስጠነቅቃለን ። ማስጠንቀቅ የታላቅ አሳቢነት ምንጭ ነው ። ብትጎዳ እኔም እጎዳለሁ የሚል ስስትም ነው ። በአንዳንድ አገራት ስብከትን የሚገድብ ሕግ እየተረቀቀ ነው ። ሰውን ይህን አድርግ አታድርግ ማለት ገደብና ነጻነትን የሚነሣ ነው በሚል እሳቤ ሕግጋት እየተረቀቁ ነው ። ይህ ድርጊት ትክክል አይደለም ብሎ መናገር የሚያስጠይቅባቸው አገራት አሉ ። ዘመናዊነት ኃጢአትን የሚያቆነጅ ነው።

እኛም የንስሐ ስብከትን እየጠላን ነው ። አገልጋዮቹም ንስሐን መስበክ ሰውን ማጨናነቅ እንደሆነ እየተሰማቸው ይመስላል ። ንስሐ ሲሰበክ ሰው ራሱን ያያል ፣ የቆመበትን አድራሻ ይመረምራል ። ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት ነውና ልብን ያሳርፋል ። ሲሰሙት መራራ ፣ ሲያደርጉት ግን ጣፋጭ ፍሬ ቢኖር ንስሐ ነው ። የታወቀው ጸሎት ፣ ጸሎተ ኢየሱስ ተብሎ የሚጠራው “የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እኔን ኃጢአተኛውን አቤቱ ይቅር በለኝ” የሚለው ነው ። “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” ብለን የምንጸልየው በመላው ዓለም የታወቀ ተወዳጅ ጸሎት ነው ። ማረኝ ማለት እኮ ታምሜአለሁ ማለት ነው ። የጸሎት አውራው ማረኝ ነው ። እርሱ ከማረን ምን ይቀርብናል ?

እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ።

ይቀጥላል

ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ