እግዚአብሔር ሕይወት ነው የሚለው የክርስትናችን ትልቅ ትምህርት ነው ። ኃጢአት ሕይወት ከሆነው ከእግዚአብሔር የሚለየን ነው ። ሞት የሚለው ትክክለኛ ትርጉምም የነፍስ ከሥጋ መለየት ሳይሆን የነፍስ ከእግዚአብሔር አንድነት መለየት ነው ። ኃጢአትን በትክክለኛ ስሙ ካልጠራነው ከኃጢአት አንርቅም ። ዘመናችን ለኃጢአት የተለያየ ስም ይሰጠዋል ። አንዳንድ አነጋገሮችም የኃጢአትን ዕድሜ ያረዝማሉ ። ሚስቶች፡- “ወንድ ልጅ አይሄድም ማለት ቆሞ አይሸናም ማለት ነው” ይላሉ ። ይህ ትክክል አይደለም ። በፈሪሀ እግዚአብሔር የሚኖሩ ለቃል ኪዳናቸው የሚታመኑ ብዙ ወንዶች አሉ ። “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚል አባባልም ሌባ ማምረቻ ሆኗል ። የብዙዎች ሹመት ለመገልገል እንጂ ለማገልገል አይደለም ። ከዚያም አልፎ ልበ ሙሉ ቀማኛ ለመሆን ሹመትን የበቀል በትር የሚያደርጉት ይኖራሉ ። “ያባት ዕዳ ለልጅ ይባል ነበር ድሮ ፣ ባያት ዕዳ ገባሁ እኔማ ዘንድሮ” እያለ ገጣሚ የተናገረው የሚፈጸምበት ጊዜ ብዙ ነው ።
“ሲሾም ያላበላ ሲሻር ይቆጨዋል” ተብሎ መስተካከል አለበት ። ሹመት ሲያገለግሉበት እንጂ ሲገለገሉበት አስደሳች አይደለም ። ደግሞም “መጠጣትና መስከር የወንድ ልጅ ወጉ ነው” ብለው ብዙዎች ይናገራሉ ። ብዙ ወላጆች ልጃቸው መጽሐፍ ቅዱስ በእጁ ከሚጨብጥ የመጠጥ ብርጭቆ ቢጨብጥ ይመርጣሉ ። ሱስ ለብሰው የሚያጭበረብሩ ቢዝነስ እየሠራሁ ነው ብለው ይናገራሉ ። እንዴት ሰው አጊጦ ይፈርሳል ። ብዙ ዘማ ሰዎች ታጥበው ታጥነው ከቤታቸው ይወጣሉ ፣ ለመቆሸሽ ይጸዳሉ ። በአደንዳዥ ዕፅ የተያዙ ወጣቶች እየተዝናናሁ ነው ይላሉ ። መቅደስ የሆነውን ሰውነታቸውን በማጎሳቆላቸው ኀዘን አይሰማቸውም ። የማይገባ ባልንጀርነት የጀመሩ ሰዎች እግዚአብሔር ፍቅርን ይወዳልና ተውን ፣ ስህተት ነው አትበሉን ይላሉ ። ስንፍና ኃጢአት ነው ብለው ብዙዎች አያምኑም ። ስንፍናቸውን ግን ትዕግሥት ብለው ይጠሩታል ። ችኮላ መዘግየትን ይወልዳል ። ችኩልነት ለኃጢአት ለክህደት አሳልፎ ይሰጣል ። ይህን በጴጥሮስ ሕይወት ያየነው ነው ። ችኩልነታቸውን ግን ትጋት ብለው ከጠሩት መቼም አይረጋጉም ። መብላት ተገቢ ነው ፣ ሆዳምነት ግን ኃጢአት ነው ። አንዳንድ ጊዜም በርኵስ መንፈስ የተያዙ ሰዎች ብዙ ምግብን ይመገባሉ ። ሆዳምነት ከፍቅር የሚያራቁት ፣ ራስ ወዳድ ፣ በምኞት ነዋሪ የሚያደርግ ነው ።
አንድ ሰው “ስለ ኃጢአት አንቀጣም ኃጢአታችን ራሱ ይቀጣናል” ብሏል ። አንድ አባትም “እግዚአብሔር ማንንም አይቀጣም ፣ የገዛ ጥፋቱ ይቀጣዋል” ብለዋል ። ሲኦል የምንለውም በገዛ ስህተታችን ፊት መኖር ነው ። ምሕረት ባላገኘ ሕሊና መመላለስ እርሱ ብርቱ ቅጣት ነው ። እርሱ ጨለማ ነው ፣ ተስፋ የለውም ። ነገን ለማየት የትላንትን የስህተት ገመድ መቍረጥ ያስፈልጋል ። እሳት ስንል የሚነድ እሳት ላይሆን ይችላል ። አንደበት እሳት ነው ስንል ሕሊናን ያቃጥላል ማለት እንጂ ቁሳዊ ነገርን ስለሚበላ እሳት እየተናገርን አይደለም ። የእግዚአብሔርን ምሕረት ያላገኘች ነፍስ ሞትን የምትኖር ፣ በሕሊና ቃጠሎ የምትሰቃይ ናት ። ሲኦልን የምንጀምረው ከበደልንበት ጊዜ አንሥቶ ነው ። የመንግሥተ ሰማያትንም ደስታ በማመን እንለማመደዋለን ። አንዳንድ ሰዎች ግፈኞች መቼ ተቀጡ ብለው ፍትሕ በሚፈልግና በሚበሳጭ አእምሮ ይናገራሉ ። ስለ ኃጢአታቸው ሲቀጡ ማየት ይፈልጋሉ ፣ እነዚያ ሰዎች ግን በራሱ በኃጢአት እየተቀጡ የሚኖሩ ናቸው ። ሥጋን ከሚልጥ ጅራፍ ውስጥን የሚወጋ የጸጸት መርፌ ይበልጣል ።
የኃጢአት ሌላኛው መጠሪያ በደል የሚል ነው ። በደለኛ መልካምን በክፉ የሚለውጥ ነው ። መልካም ለማድረግ ተፈጥሮ ክፉ ነገርን የሚፈጽም ነው ። በደለኛ የዛሬ ስህተተኛ ሳይሆን በደልን እንደ ጽድቅ የሚፈጽም ነው ። ኃጢአት ስህተት ነው ፣ በደል ድፍረት ነው ። የድፍረት ኃጢአት ከሁሉ በላይ አስፈሪ ነገር ነው ። የልብ መደንደን በመሆኑ በመሰበር የሚቆም ሊሆን ይችላል ። ነቢዩ፡- “የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ ፥ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ” ብሏል (መዝ. 18 ፡ 13)። ከመረረን ኃጢአት የመውጣት ዕድል አለን ፣ ከጣፈጠን ኃጢአት ግን የትኛውም ነጻ አውጪ ነጻ አያወጣንም ። የድፍረት ኃጢአት ታላቅ ኃጢአት ነው ። የደፈረ ሰው የማይነካው የኃጢአት ዓይነት የለም ። ኃጢአት ሲለመድ ጽድቅ ይመስላል ይባላል ።
የሰው ልጆች ኃጢአትን በሚመለከት የማያልቅ ፍለጋ ውስጥ ናቸው ። የሚፈልጉትን ነገር ማግኘት ስላልቻሉ ሁልጊዜ በሙከራ ውስጥ ያልፋሉ ። የሚሞክሩት ሥጋቸውንና ነፍሳቸውን አስይዘው ነውና ከባድ ነው ። ኃጢአት በምድር በሰማይ የሚጎዳ ነው ። አማኒ እንደ ዮሴፍ ኃጢአትን አልሠራም ብሎ ሊታሰር ይገባል እንጂ ስለ ሠራው ግፍ ሊታሰር አይገባውም ። በተሳሳተ መንገድ ደስታን የሚፈልጉ ሰዎች ይበልጥ እያጡት ይመጣል ። በሬን ጨው እያላሱ ከፊቱ ይሮጣሉ ፣ እየጣመው ሲከተል መጨረሻ ቄራ ይደርሳል ። ሰይጣንም እያታለለ የሚሰርቅ ፣ እያሰባ የሚያርድ ክፉ ነው ። ስንቱ ሰው በምስጋና ፣ ክብር በሚመስል ነገር ፣ በሥልጣን እየሰባ ለእርድ ተዘጋጅቷል ።
ይቀጥላል
ሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም.