መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የኃጢአት ስሞች » የኃጢአት ስሞች -4

የትምህርቱ ርዕስ | የኃጢአት ስሞች -4

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በአንድ ዓይናችን እያለቀስን በአንድ ዓይናችን የምንስቅበት ነው ። ስለ እኛ ኃጢአት ብዙ መከራ በመቀበሉ እናለቅሳለን ። የመስቀሉን ሕማም እያሰቡ ዘመናቸውን በእንባ የፈጸሙ አባቶች ብዙ ናቸው ። አንዳንድ ወገኖች የትንሣኤውን ደስታ ብቻ ማሰብ ይፈልጋሉ ፣ ትንሣኤ ግን ዋዜማው ሞት መሆኑን አይረዱም ። እውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን ሕማምና መከራ የምታስብ ናት ። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን፡- “ንዜኑ ሞተከ ወትንሣኤከ- ሞትህን ትንሣኤህን እንናገራለን” ትላለች ። ይህም የትእዛዝ ቃል ያለው ነው ። የክርስቶስን ሞት እንድናስበው ታዘናል (ሉቃ. 22፡19) ። ለመታሰቢያዬ አድርጉት ያለው እንድናስበው ያዘዘው ሞቱን ነው ። ትንሣኤውን ግን እናውጃለን ። ሐዋርያውም፡- “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና” ብሏል (1ቆሮ. 11 ፡ 26) ። ሞቱን ማሰብና መናገር ይገባናል ። አባቶቻችን በእንባ አስበውታል ፣ ሰብከውታል ። የክርስቶስ ሞት የነጻነታችን ምሥጢር በመሆኑ እንደሰታለን ። እርሱ ታስሮ እኛ ተፈተናልና።

ክርስቶስን ለመስቀል ሞት የዳረጉት አይሁድ እንደሆኑ እናስባለን ፣ እርሱ ግን የሞተው በፈቃዱ ነው ። ሰው የሆነውም ስለ እኛ ለመሞት ነው ። ክርስቶስን ለመስቀል ሞት የዳረገው የሁላችን ኃጢአት ነው ። ኃጢአትን መራቅ ያለብን ክርስቶስን ለሞት የዳረገ ምክንያት በመሆኑ ነው ። የምንወደው ልጃችን በሞተበት ቢላዋ ሥራ እንደማንሠራ ሁሉ ክርስቶስን ለሞት ባበቃ ኃጢአትም መጫወት አይገባንም ። ሰዎች በሽታን ይልቁንም በወቅቱ መድኃኒት ያልተገኘላቸውን ሕመሞች በጣም ይፈራሉ ። መፍራታቸው ተፈጥሮአዊ ነው ። ከሁሉ በላይ ሊያስፈራ የሚገባው ግን ኃጢአት ነው ። በሽታዎች አንዳንድ ጊዜ ከቤተሰብ ይወረሳሉ ፣ የኃጢአት ዝለትም ከአዳም የመጣብን ነው ። በሽታዎች ተላላፊ ናቸው ፣ ኃጢአትም በአንድ ሰው የሚወሰን ሳይሆን ብዙዎችን የሚነካ ነው ። ዝሙት ሌላውን ንጹሕ ሰው ያረክሳል ፣ ስርቆትም የሌላን ሰው ልፋት ያጠፋል ። መግደልም ገዳዩን ወንጀለኛ ሟችን ሕይወት አልባ ያደርጋል ። ኃጢአት ተዛማች በሽታ ነው ። በሽታ ውስጥ ውስጡን ይገዘግዛል ፣ ኃጢአትም ቀስ በቀስ ወደ ሞት ሊያደርሰን ይተጋል ። በሽታ ለሥጋ ሞት ብቻ የሚያጋልጥ ነው ፣ ካንሰር የነፍስ ሞትን አያመጣም ። ኃጢአት ግን ዘላለማዊ ሞትን ያስከትላል ። እንዴት እግዚአብሔር ፍቅር ነው እያላችሁ ዘላለማዊ ሞትን ያመጣል ትላላችሁ የሚሉ ወገኖች አሉ ። መንግሥተ ሰማያት ዘላለማዊ ከሆነ ገሀነመ እሳትም ዘላለማዊ ነው ። የሁለቱንም ዘላለማዊነት የነገረን ራሱ እግዚአብሔር ነው ።

ከኃጢአት መደምሰስን የሚያመጣ ፣ ከህልውና ዓለም የሚያወጣ አይደለም ። ሰው እንዳይጠፋ ሁኖ ተፈጥሮአል ። በመዳኑ በገነት ሲሆን ፣ በኃጢአቱ ግን በሲኦል ይኖራል ። ኃጢአት መደምሰስን አያመጣም ፣ ከእግዚአብሔር ተለይቶ ለዘላለም መሞትን ያስከትላል ። እግዚአብሔር ሰላምና ደስታ ነው ፣ ከእግዚአብሔር መለየትም ከሰላምና ከደስታ መለየት ነው ፣ ለዘላለም ከሰላምና ከደስታ መለየት በኃጢአት ምክንያት ይመጣል ። ጎረቤቶቻችን ሲበድሉን ወይም ኃጢአት ሲሠሩብን እናዝናለን ፣ እንቀየማለን ። የጎረቤቶቻችን ግፍ ለሲኦል አያበቃንም ። የገዛ ምርጫችንና የስህተት መንገዳችን ግን ሞትን ያመጣብናል ። ኃጢአት ማጥፋትና መጥፋት ነው ። ማጥፋት ነው ስንል ጤናን ፣ ገንዘብን ፣ ክብርን ፣ ነጻነትን ፣ ኅብረትን መክሰር ነው ። መጥፋት ነው ማለታችን ደግሞ ኃጢአተኛው እዚህ ነኝ እስከማይል ድረስ ባካና ያደርገዋል ። ኃጢአት ተቅበዝባዥ ያደርጋልና ። “የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው።” (ሉቃ. 19 ፡ 10)።

“ኃጢአት ከቃሉ ያርቀናል አሊያ ቃሉ ከኃጢአት ያርቀናል ።” ከቃሉ ያራቀን ስፖርት ቢሆን ፣ ንግድ ቢሆን ኃጢአት ነው ። ፍጥረትን ሁሉ የደገፈው ክርስቶስ ነው ። ሰማይ ያለ ምሰሶ የጸናው ፣ ግዙፍ ፕላኔቶች ያለ መናጋት እየተጓዙ ያሉት በክርስቶስ ነው ። ታዲያ ይህን የሚያህል ግዙፍና ኃያል ፍጥረት በቃሉ ከተደገፈ የሁልጊዜ ሰባራ የሆነው የሰው ልጅ በቃሉ መደገፍ አለበት ። ኃጢአት ሌላው ስሙ መተላለፍ ነው ። ሕይወት ሕግ ፣ ደንብና መመሪያ አላት ። የሕይወት ሕግ የሰውን ተፈጥሮ ቀጣይ የሚያደርገው ነው ። ይህ ሕግ ስለ መብላት ብቻ ሳይሆን ስለ መጾምም ይናገራል ። ያንን ሕግ ካላከበርን በምንበላው እንሞታለን ። ማለፍ የሌለብን ደንቦች አሉ ፣ መሄድ ያለብን መንገድ አለ ። መብት ብቻ ሳይሆን ግዳጅም አለ ። እነዚህን የሕይወት ሕጎች መተላለፍ ኃጢአት ይባላል ። ብዙ ሰው ስለ ጤናው ቸልተኛ ነው ። በራሱ ላይ መብት ያለው ይመስለዋል ። በራሳችን ላይ ባለ አደራዎች እንጂ ባለቤቶች አይደለንም ። ይህ አካል የሥላሴ መቅደስ ነው ። ንጽሕናን መጠበቅ ፣ በአግባቡ መኖር ግዴታ ነው ።

በዚህ ዓለም ላይ ሦስት ኃይላት አሉ ይባላል ። ሕግ አውጪ ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ ናቸው ። ሕግ አውጪው ፓርላማው ነው ። ሕግ ተርጓሚው የዳኝነት ሥርዓቱ ነው ። ሕግ አስፈጻሚው የፖሊስና የጸጥታ አስከባሪው ነው ። በመንፈሳዊው ዓለም የሕጉ ባለቤት እግዚአብሔር ነው ፣ ሕግ ከጽዮን ይወጣል እንደ ተባለ የክርስቶስ እንደራሴ የሆነች ቤተ ክርስቲያንም የሥርዓት መገኛ ናት ። የሕግ ተርጓሚዎች ሰባክያን ናቸው ። የሕግ አስፈጻሚው ምእመናን ናቸው ። የሚያስፈጽሙትም በራሳቸው ላይ ነው ።

ይቀጥላል

ሰኔ 16 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ