“እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር ፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው ።” ሉቃ. 24፡21 ።
በመጽሐፈ መሳፍንት በምዕራፍ 8፡4 ላይ ያለው ቃል በጣም ይገርማል፡- “ጌዴዎንም ከሦስቱ መቶ ሰዎች ጋር ወደ ዮርዳኖስ ደርሶ ተሻገረ ምንም እንኳ ቢደክሙ ያሳድዱ ነበር” ይላል ። ደክሞ ማሳደድ ፣ ወድቆ ማፍራት ፣ ጠውልጎ ስለ ክርስቶስ መናገር ይኖራል ። መድከማችንን የምናውቀው እኛ ነን ። ጠላት የሚያየው የሚዋጋልን ጌታ የማይደክመው መሆኑን ነው ። እንደ ወደቅን የምናውቀው እኛ ነን ። ቃሉ ግን ትንሣኤና ሕይወት ነው ። መጠውለጋችን ለራሳችን የነገርነው “ደክሞኛል” የሚል ዜና ነው ። ብቻ ስለ ክርስቶስ መናገር ካላቆምን እርሱ አብሮን ይጓዛል ። እግዚአብሔር መድከምን ፣ መውደቅን ፣ መጠውለግን መጨረሻችን አላደረገውምና ምስጋና ይገባዋል ። ከድካማችን የተነሣ አሁንስ ያሳደድሁት ሊያሳድደኝ ነው ስንል ጠላት እየመጡ ነው ብሎ መለከት ይነፋል ። እኛ ድካማችንን ጠላት ብርታታችንን ያወራል ። እኔ ወድቄአለሁ ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔርን ሥራ መሥራት አልችልም ስንል ብዙዎች በእኛ ሲነሡ እናያለን ። ጠውልገንና ተሰላችተን ሳለ ግድ ሆኖብን የምንናገረው ዜና ክርስቶስ ብዙዎችን እንዳበረታ ምስክርነት ስንሰማ እንደነቃለን ። በጸሎት አስቡን ሲሉን ውስጣችን እየሳቀ እሺ እንላለን ፣ ከቀናት በኋላ ጸሎታችሁ ሠመረ ብለው ሰዎች ወደ እኛ ሲመጡ እግዚአብሔር ስለ ስሙ ከእኛ ጋር እየሠራ እንደሆነ ይገባናል ። ዛሬ የምጸልይለት ድውይ አይፈወስም ፣ ምክንያም ጥሩ አይደለሁም ስንል በሽተኛው ዘሎ ይቆማል ። ፈውስ የእኛ ብቃት ማረጋገጫ ሳይሆን እግዚአብሔር ለሚያቃስተው በሽተኛ ያለው ደግነት መሆኑን የምንረዳው ቆይተን ነው ።
የኤማሁስ መንገደኞች ሰንበትን ውለው አርፈው የጀመሩት ጉዞ ቢሆንም ጠውልገው ነበር ። ውስጣቸው ደክሞ ነበርና እግራቸውን ማንሣት አቅቷቸው ፣ በተሰላቸ ድምፀት ስለ ክርስቶስ ሞት ይናገሩ ነበር ። ሰዎች ክርስቶስን ስለ ሰቀሉበት ምክንያታቸው እንጂ ክርስቶስ ስለ ተሰቀለበት የሥላሴ ፈቃድ አልተረዱም ነበር ። ሁሉም ነገር ከምድር ስናየውና ከሰማይ ስናየው ልዩነት አለው ። ተኝተን ብናድርም ፣ ዐርፈን ጉዞ ብንጀምርም ውስጣችን ተስፋ ከቆረጠ አሁንም እንደ ደከምን ነው ። ተኝቶ አለመንቃት ፣ በልቶ አለመበርታት ከተስፋ ጋር የተያያዘ ነው ።
እግዚአብሔር የቆምንበት ስውር እጅ ፣ የምንነሣበት የትንሣኤ ምሥጢር ነው ። የኤማሁስ መንገደኞች ስለ ክርስቶስ ሞት ሲያወሩ ሁለት ሰዎች የሚናገሩ ብቻ አይመስሉም ። የደመቀ ጉባዔ ይመስል ነበር ። ይነጋገሩ ነበርና ሁለቱም አድማጭም ተናጋሪም ነበሩ ። ይመራመሩም ነበረ ። ለምንና እንዴት እያሉ ይጠይቁ ነበር ። በዚህ ጊዜ ክርስቶስ አብሮአቸው ሦስተኛ ሁኖ ይጓዝ ነበር ። እነርሱ ግን ልብ አላሉትም ነበር ። እንዳያዩት ዓይናቸው ተይዞ ነበር ። እርሱን ዓይናማዎች ፣ አሻግረው የማየት አቅም ያላቸው ሳይሆን የሚያምኑ ብቻ ያዩታል ። ጉዞአቸው ወደ ፀሐይ መጥለቂያ በመሆኑ ምንም ነገር እንዳያዩ ተሰናበቿ ፀሐይ ጋርዳቸው ነበር ። ሁሉም ነገር አብቅቷል በሚል ስሜት ተስፋቸው ልትጠልቅ ተቃርባ ነበር ። ተስፋ መቍረጥና ጨለማ ሁለቱ ከባድ ናቸው ። ወደ ሁለቱም ይጓዙ ነበር ። ተስፋ የቆረጡ ልጆቹ ባያዩትም ክርስቶስ አብሯቸው ይጓዛል ። ምክንያም ሰይጣን ተስፋ የቆረጡትን በጣቱ ወደ ሲኦል ቢገፋቸው ጥልቁ ላይ ይገኛሉ ። ተስፋ መቍረጥ ለሰይጣን በፈቃድ እጅን መስጠት ነው ።
ትሑቱ ጌታ ንግግራቸውን በትሕትና አቋረጠ ። ስለ እርሱ ከመናገሩ በፊት ስለ እርሱ እንዲናገሩ ፈቀደ ። ስለ እርሱ የሚናገሩት ጨለማ ያጠላበት ቢሆንም እርሱ ግን ተሸናፊ አይደለሁም ብሎ ቸኩሎ ራሱን አላስተዋወቀም ። እግዚአብሔር የማይቸኩለው የሚሰጋው ነገር ስለሌለ ነው ። “እርሱም፦ እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፥ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው ? አላቸው ።” የልባቸው ብሎን እንደ ላላ ፣ ለመበተን እንደ ተቃረቡ ተረድቷል ። እኛን ሳያስፈቅድ ልባችንን የማየት አቅም አለው ። ልባችን የእርሱ ነበር ፣ ቀጥሎ ሁለት ቁልፍ ቀርፆ አንዱን በእጁ ሲይዝ አንዱን ለእኛ ሰጠን ። መጠውለጋቸው በፀሐይ ትኩሳት አልነበረም ፣ ሰዓቱ ሠርክ ነውና ። መጠውለጋቸው የመንገድ ድካም የወለደው አልነበረም ። ተስፋ መቍረጥ ጉልበታቸውን መትቶባቸው ፣ ፊታቸውን አጨልሞባቸው ነበር ። ተስፋ የሚሰጠውን ማማር አጥተውት ነበርና አዘነላቸው ።
“ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ፦ አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው።” ለቀባሪው አረዱት የተባለው ተፈጸመ ። እርሱ በርግጥም እንግዳ ነበረ ፣ ዓለም ግን አልተቀበለችውም ። ሲወለድም በበረት የተወለደ ትልቅ እንግዳ ነበር ። ሰዎች ልባቸውን ዘግተውበት መስቀል ላይ የዋለ ነው ። ደቀ መዛሙርቱ ትተውት ቢሸሹም የአባትነት መነሻ የሆነው እግዚአብሔር አብ ከእርሱ ጋር ነው ። ብቸኝነት ያለ እግዚአብሔር መኖር እንጂ ያለ ሰው መኖር አይደለም ። ከብቸኝነት የማይሻሉ ፣ ከባዶ ቤት ከፍ የማይሉ ሰዎች አሉ ። ኖረው የሌሉ ፣ ተገኝተው የሚያደክሙ ፣ ራሳቸውን እንጂ ስሜታችንን ለማዳመጥ ያልታደሉ አሉ ። መጠውለግን የሚያነብ ፣ ስሜትን የሚረዳ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ሰዎች ጋር ለመኖር ስሜትን መቆጣጠር ግድ ነው ። ከነሐቃችን የሚቀበለን መድኃኔ ዓለም ብቻ ነው ። ራሳችንን በሸሸን ሰዓት የተቀበለን እርሱ ነው ። ራሳችንን ለማየት ባፈርን ጊዜ በእቅፉ ያረጋጋን አማኑኤል ነው ። በርግጥ ጌታ አላውቅም ያለው አንድ ነገር አለ ። ጠላት እስከ ዘለቄታው ማሸነፉን ጌታ አያውቅም ። እርሱ እያወቀ እንዳላወቀ አብሮን ይጓዛል ። የእኛን መንገድ ስንጨርስ ወደ እርሱ መንገድ እንደምንመለስ ተስፋ በማድረግ በሙከራዎቻችን ሁሉ በዝግታ ያየናል ።
“እርሱም፦ ይህ ምንድር ነው? አላቸው ። እነርሱም እንዲህ አሉት ። በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ ፤ እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር ፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው ። ደግሞም ከእኛ ውስጥ ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ፡- ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ ደግሞ አየን ሲሉ መጥተው ነበር ። ከእኛም ጋር ከነበሩት ወደ መቃብር ሄደው ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፥ እርሱን ግን አላዩትም ።”
እግዚአብሔር ስለ እግዚአብሔር ጠየቀ ። ሊተርክ የሚገባው ሟች ሲተረክለት ሰማ ። መሥዋዕት ሁሉ በዝምታው ሲናገር ይኖራል ። አንድ መሥዋዕት ብቻ ነባቢ/ተናጋሪ ነው ። እርሱም ከሞት የተነሣው ክርስቶስ ነው ። እምነት ማለት ዓለምን ኰንኖ ክርስቶስን ማጽደቅ ነውና ክርስቶስን አክብረው ዓለምን ወቀሱ ። በሰው ፊት ብርቱ የሆኑ አሉ ፣ በእግዚአብሔር ፊት ግን የተናቁ ብዙ ነገሥታትን እናውቃለን ። ክርስቶስ ግን በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ብርቱ ነበረ ። ብርታቱ የቃሉ ትምህርት የእጁ ተአምራት ነው ። ሌላ ብርታት አለው ፣ ስለ ጠላቶቹ ቤዛ የሆነ ነው ። ይህን ብርታት አላወቁም ነበረ ። እስራኤልን ነጻ ያወጣል ብለው ጠብቀውት ነበረ ፣ እርሱ ግን የመጣው መላው ዓለምን ነጻ ለማውጣት ነው ። እርሱ የነፍስ ነጻ አውጪ ነው ። የመነሣቱን ዜና ቢሰሙም ፣ መቃብሩ ባዶ መሆኑን ሌሎች ቢያረጋግጡላቸውም እነርሱ ግን አላመኑም ነበር ። አለማመን ተስፋ አስቆረጣቸው ። ወደ መኖሪያ ከተማቸው እንዲሄዱ አደረጋቸው ። የተዉትን መጀመር ፣ የጀመሩትን መተው ከተስፋ መቍረጥ ውስጥ ይወጣል ። ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው የተዉትን ሱስ ጀምረዋል ፣ የጀመሩትን ወንጌል ጥለዋል ።
“እርሱም፦ እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ” በማለት ገሠጻቸው ። ተግሣጹን ስለ ተቀበሉ ቀጣዩን ምሥጢር አወቁ ። የክርስቶስ ሞት ገዳዮች መግደል ስለቻሉ ያከናወኑት ሳይሆን መላው ብሉይ ኪዳን እውነት የሆነበት ነው ። ምክንያቱም በተስፋ ፣ በምሳሌ ፣ በመሥዋዕት ፣ በትንቢት ፣ በክህነት ፣ በመቅደስ የክርስቶስ ሞት ሲነገር ኑሯልና ። የገላትያ ሰዎችም የተሰቀለውን ክርስቶስ ስለ ረሱ የማታስተውሉ ተብለዋል ። የማያስተውሉ የሚባሉት ንግድ ያልገባቸው ሳይሆኑ ክርስቶስ ያልገባቸው ወይም ለመስቀሉ ጀርባቸውን ለዓለም ፊታቸውን የሰጡ ናቸው ። በመንፈስ ጀምሮ በሥጋ መጨረስ አለማስተዋል ነው ።
የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን በሙሉ ተረጎመላቸው ። ባያውቁትም እርሱ ግን ያውቃቸው ነበር ። የአማኝ ዋስትናውም በእግዚአብሔር መታወቁ ነው ። የመንግሥተ ሰማያት ደስታም እግዚአብሔር እኛን ማወቁ ነው ። እነርሱም እንግዳ ነው ሳይሉ ፣ አናውቀውም በማለት ሳይገፉት ፣ ለእምነታቸው አስቧልና ለሥጋው አሰቡለት ። “ከእኛ ጋር እደር ፥ ማታ ቀርቦአልና ቀኑም ሊመሽ ጀምሮአል” ብለው ግድ አሉት ፤ ከእነርሱም ጋር ሊያድር ገባ ። ይህ ተማጽኖ ከዚያ ዘመን ይልቅ ዛሬ ያስፈልጋል ። ማታው እየቀረበ ፣ ቀኑ እየመሸ ነውና አብሮን ቢያድር መልካም ነው ። የጨለማ ወዳጅ እርሱ ብቻ ነውና ። የሚያስፈራንን የሚያስፈራው ስለ እኛ የሚዋጋው ጌታ ብቻ ነው ።
በቤታቸው የአባወራው ወንበር ላይ አስቀመጡት ። አባወራው መባረክ የሚገባውን ማዕድ እንዲባርክ ጋበዙት ። እንግዳውን አከበሩት ። ትልቅነታቸውን ለእርሱ ተዉለት ። በቤታቸው ሾሙት ። እርሱም እንጀራውን ባርኮ ሲሰጣቸው ዓይኖቻቸው ተከፈቱ ። ጠውልገው የነበሩ እንደገና ታደሱ ። ደክሟቸው የነበሩ እንደገና ተነሡ ። የምሥራቹን ይዞ ማደር ነውር ነው ብለው አሰቡ ። ለአሥራ አንድ ኪሎ ሜትር የዛሉ እንደገና ተመለሱ ። ቅድም በዝለት አሁን በብርታት ። ቅድም በተስፋ መቍረጥ አሁን በተስፋ ተመለሱ ። ክርስቶስን ሲያገኙ እንደ እነርሱ አዝነው የነበሩት ደቀ መዛሙርት ትዝ አሏቸው ። በበረቱበት ምሥጢር ሊያበረቱአቸው ተመለሱ ። ቀኑ ሳይመሽ ከጌታቸው ጋር ታረቁ ። በቍጣችሁ ፀሐይ አይጥለቅ ያለው በተስፋ መቍረጣችሁም ፀሐይ አይጥለቅ ይላል ። በዋሉበት ስሜት እንዳያድሩ አዳምን በምሽት የፈለገ ፣ ሲመሽ ደረሰላቸው ።
ዛሬም ሰው ያሸነፈ መስሎአችሁ ያዘናችሁ ፣ የውግረት ድንጋይ ቀና አላደርግ ብሎአችሁ በካብ ውስጥ የምታጣጥሩ ክርስቶስ ተነሥቷል ። ወደ ኤማሁስ በዝለት የሄዳችሁ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ ። ኢየሩሳሌም የገዳዮች ሳይሆን የምስክሮች ቤት ናት ። ወደ ፀሐይ መጥለቂያ ጉዞ የጀመራችሁ ፣ እየተናገራችሁ እንኳ እግዚአብሔር ትቶኛል የምትሉ ይህች ጀንበር ሳትጠልቅ ተመለሱ ። ክርስቶስ ተነሥቷል ። ኢየሩሳሌምን ለክፉዎች አትልቀቁ ። እውነት ብታጎነብስም አትሰበርም ።
ጸሎት
ተስፋ ያደረግሁት ባይሆንም ተስፋ የሆንከው አንተ አምላኬ ግን ካጠገቤ ነህ ። አንተ እያለኸኝ ዓለም ጎደለብኝ ማለቴ ነውር ነው ። ከቤት ውጭ ያሉ ሳቆች በቤት ውስጥ የሉም ። እቤት ያልጀመሩ ደግነቶች ከተማውን ሞልተውታል ። የእይታ እንጂ የእውነታ ሰው መሆን ርቆኛል ። እግዚአብሔር ሆይ ፣ በተስፋህ እንደገና አንሣኝ ። ተስፋ አዳምን 5500 ዘመን አኖረው ። ተስፋ በዋዜማውም በበዓሉም ደስታ ነው ። እንዲሁ በተስፋ ደስ አሰኘኝ ። መነሣትህ መነሣቴ ይሁንልኝ ። በከበረው ደምህ አሜን ።
የመስቀሉ ገጽ 7/ለ
ሚያዝያ 18 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን