መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም » የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም -1

የትምህርቱ ርዕስ | የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም -1

ማፈር ትልቅ ሕመም አለው ። ሰማይና ምድርን ደብቁኝ የሚያሰኝ ውስጣዊ መራቆት ነው ። ማፈር ኪሎ እንድንቀንስ ፣ እንድናንስ ፣ እንድንሸማቀቅ ፣ የሰውን ፊት እንድናፍር ፣ ራሳችንን እንድንሸሽ ያደርጋል ። ሰው በራሱ ሊያፍር ይችላል ። በሚገባው ስፍራ ላይ ባለ መገኘቱ ፣ እውነትን ትቶ ስሜቱን በማድመጡ ፣ ያለ እኩያው በመዝመቱ ፣ አደርጋለሁ ያለውን ማድረግ ባለ መቻሉ ፣ በሁለት ቃል ትዝብት ላይ በመውደቁ ሊያፍር ይችላል ። ከላይ እግዚአብሔርን የሚፈራ ፣ ከታች ሰውን የሚያፍር ወገን ያስፈልጋል ። ማፈር በጥቂቱ መልካም ነው ። ክብርን የመክሰር ስሜት የሚያመጣው እፍረት ግን አስጨናቂ ነው ። በራስ ሕሊና ፊት ለፍርድ መቆም ፣ በሰዎች ዘንድ ዋጋ ማጣት ትልቅ ኪሣራ መስሎ ይሰማል ። ሰዎች በራሳቸው ያልተገባ ኑሮ ብቻ ሳይሆን በሰዎችም ያፍራሉ ። ይልቁንም የእኔ የሚሉት ሰው በማኅበረሰቡ ፊት ዕርቃኑን ሲቆም መሸማቀቅ ሊከሰት ይችላል ። ከሞኝ ጋር የሚኖሩም ሁልጊዜ ያፍራሉ ። ቃሉን የማይጠብቅ የቅርብ ሰው ተጨማሪ ሐፍረትን ይዞብን ይመጣል ። ይልቁንም በእኛ አኗኗር ያመንበትን ከማድረግ በይሉኝታ መኖር ይቀናናል ። ሰዎች ስለ እኛ የሚሰጡት አስተያየት ብቻ ሳይሆን ሊሰጡ ይችላሉ የምንለውን ግምት እያሰብን ራሳችንን በሐፍረት እንቀጣዋለን ። ማኅበራዊነት መልካም ነው ። ጥብቅ ትስስር ባለው ማኅበረሰብ ዘንድ መኖር ራሱን የቻለ እስራትም አለው ። ከአቅም በላይ መኖር ፣ ሁሉን ደስ ለማሰኘት መሞከር ፣ ያመኑበትን ነገር ማድረግ አለመቻል ፣ ምን ይሉኛል እያሉ እያነሱ መኖር የተለመደ ነው ።

ተመልሰው እንዳይመጡ ከምንመኛቸው ጊዜያቶች አንዱ የሐፍረት ገጠመኛችን ነው ። በማፈር ምክንያት ወጥተው የቀሩ ፣ ዳግም ገጻችንን ያላዩ ሰዎች አሉ ፤ ማፈር መቻልም አንዱ ሰዋዊነት ነው ። የሚያፍሩ ሰዎች ያከብሩን እንደ ነበር መረዳት እንችላለን ። እኛ ጠይቀናቸው የማናውቃቸው እነርሱ ሁልጊዜ የሚጠይቁን ሰዎች አሉ ። ታዲያ በመጥፋታቸው መልሰው ያፍራሉ እንጂ እነርሱስ እንዴት አይፈልጉኝም  ብለው ከእኛ አይጠብቁም ። እነዚህን ሰዎች ማበረታታት አለብን ። የሚደግሱበት ተራ ደርሶ ምንም ስለሌላቸው የሚለምኑ ፣ ከሐፍረት አድኑኝ የሚሉ ብዙ ወገኖችን እናውቃለን ። አንድ እናት በልጅነት ዘመኔ አስታውሳለሁ ። ቀጣዩ የሴቶች ማኅበር እርሳቸው ጋ ነበርና እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ እንደሚችሉ ይሰማቸው ነበር ። ችግር መቼም ሁሉን አሳጥቶ ምኞትን ግን አይነሣም ። ጠላው ፣ ዳቦው በአንድ ቀን ሊደርስ አይችልም ። እርሳቸው ግን አንድ ተአምር ይፈጸማል እያሉ ሲጠብቁ ቀኑ ደረሰ ። ማኅበርተኞች የሚመጡበት ሰዓት ሲደርስ ቤታቸውን ለቀው ከከተማው ጠፉ ። ቤታቸው ትልቅ ነው ። በትልቅ ቤት ያለውን ችግር ማንም አያውቀውም ። ቤት ልመና ከልክል ነው ። የእኚህን እናት ሐፍረት ሳስታውስ የቃና ዘገሊላ ደጋሾችም ትዝ ይሉኛል ።

በቃና ዘገሊላ የሆነውም ልክ እንደዚህ ነው ። የአይሁድ ባሕል እርስ በርስ በጣም መቀራረብ አለው ። በእርስ በርስ መቀራረብ ውስጥ ክብር ትልቅ ድርሻ ይሰጠዋል ። አንሶ ላለመገኘት ፣ የእገሌን በልቻለሁ ብድር እመልሳለሁ ማለት የተለመደ ነው ። የአይሁድ ሰርግ በትንሹ ለሰባት ቀን የሚቆይ ነው ። ከየአገሩ የተጠራው ወገን እየመጣ ሳለ በመጀመሪያው ቀን ወይን ጠጁ አለቀ ። እንደ ዛሬ ደርሶ የሚመለስ ሳይሆን የሚሰነብት እንግዳ ገና ገብቶ ሳያልቅ ድግሱ አለቀ ። ምክንያቱ ምን እንደሆነ አልተጠቀሰም ። ተድፋፍቶ ነው እንዳይባል በዕለት ሊያልቅ አይችልም ። ካላቸው መጠነኛ ኑሮ የተነሣ ድግሱ አነስተኛ ሁኖ ይሆናል ። ይህም በጣም ያሳዝናል ። በመደገስና ባለመደገስ መካከል የነበረ ቤተሰብ ነው ። ይህ ሰርግ ግን ለየት ያለ ነገር አስተናግዷል ። ሰማይና ምድር የእርሱ የሆኑት አምላክ ሥጋ ለብሶ ሰርጉ ላይ ተገኝቷል ። ዓለም ሁሉ የሚወዳት ፣ ሰማይ ያከበራት ድንግል ማርያም በዚያ ሰርግ ላይ በአካል ነበረች ። ዓለምን በወንጌል የሚያበሩት የጽዮን ሙሽሮች አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት በዚያ ሰርግ ላይ ተገኝተዋል ። ጸጋው አነሰብን የሚሉት እነዚያ ደጋሾች ባለጠጋው ጌታ በመካከላቸው መኖሩን አላወቁም ።

ይህ የሰርግ መርሐ ግብር ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ ከመሄዱ በፊት የተሰማ ነው ። አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሞ በተመለሰ በሦስተኛው ቀን እዚህ ሰርግ ላይ ተገኘ ። ሦስቱን ቀን ተከታዮቹን እየሰበሰበ ነበር ። አሁን አሥራ ሁለት ደርሰዋል ። እርሱ ቀጠሮን የማይረሳ አምላክ ነው ። አክባሪዎቹንም ያከብራል ። ከዐርባ ቀን በፊት እናቱን ሲለይ የነበረው ገጽታ አሁን ተለውጧል ። በጾም በጣም ከስቶ ስታየው የእናትነት አንጀትዋ ይላወሳል ። እንኳን ኢየሱስን ያህል ልጅ አስቸጋሪ ልጅም ያራራል ። እርስዋ የሆነላት ነገር ብዙ ነው ። በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቷታል ። በአንድ ጊዜ እናትም ድንግልም ናት ። በአንድ ጊዜ ክርስቶስ አምላክዋም ልጅዋም ነው ። የቃና ዘገሊላን ሰርግ የሚመስለው ሰርግ እንደሌለ ድንግል ማርያምንም ከፍጥረት የሚመስላት የለም ።

የቃናው ሰርግ በጅምሩ አለቀ ። የሰዎች መግባባት በዚህ ዘመን ፈጣን ነው ። ወዲያው የተዋወቁ መስሎአቸው ይናናቃሉ ። ወረት የብዙዎችን ሕይወት እያዘዘ ነው ። ሰዎች ብዙ አማራጭ ያላቸው ይመስላቸዋል ። ስሜት እያየለ ቃል ኪዳን እየጠፋ ነው ። ለገዛ ልቡ ታማኝ ያልሆነ ለሌላው ታማኝ መሆን አይችልም ። ሁሉም የድርሻውን ዘግኖ ዞር ማለት ፣ በር ዘግቶ ሌላው ሲራወጥ ማየት ይፈልጋል ። ውሸት ብዙ ግንኙነቶችን ሳይጀመሩ እንዲያልቁ እያደረገ ነው ። አለሁ ያሉ አይገኙም ፣ በሚያስፈልገው ሁሉ ጥሩኝ የሚሉት ስልካቸው አይነሣም ። ሰው መሰሉን ሰው እየፈራ በር እየዘጋ ያለበት ዘመን ነው ። የሕዝብ ቍጥር እየጨመረ ነው ። ሰው ግን ሰው አጥቶ እየተራበ ነው ። የሰው ረሀብ ከእህል ረሀብ ይከፋል ። ገና በሰርጉ ቀን መቃቃር ይጀመራል ፣ እቤት ሲገቡ ወደ ደጅ መውጣት የሚያምራቸው ብዙ ሙሽሮች አሉ ፤ እግዚአብሔር ካልገዛን ወረት በግድ ይገዛናል ።

“የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” የሚለው የድንግል ማርያም ልመና ዘመን ተሻግሮ ለዛሬው ዘመን የሚያስፈልግ ነው ። ወይን ጠጅ ፍቅርን የሚገልጥ ነው ። ያለ ፍቅር ሕይወት ጣዕም የላትም ። ሰዎች ተሰብስበዋል ወይን ጠጁ ግን አልቋል ። ፍቅር ጭል ጭል በሚልበት ዘመን ፣ አፍቃሪዎችም በመውደዳቸው በሚጸጸቱበት ዘመን እነሆ አለነ ።

የቅድስት ማርያም በረከት ይደርብን !

ይቀጥላል

ሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ