መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ሕያው መሥዋዕት

የትምህርቱ ርዕስ | ሕያው መሥዋዕት

መሥዋዕት ከእህልና ከእንስሳት ለእግዚአብሔር የሚቀርብ እጅ መንሻ ነው ። መሥዋዕት ለምስጋና ፣ ራስን ለመስጠት ፣ ለኃጢአት ስርየት ፣ ለጸሎት ፣ ለቤዛነት የሚቀርብ ነው ። መሥዋዕትን የጀመረው ራሱ እግዚአብሔር ነው ። ለአዳም የቍርበት ልብስ ባለበሰው ጊዜ አንድ በግ በገነት እንደ ተሠዋ ታውቋል ። ቍርበት ወይም የቆዳ ልብስ የመሥዋዕት ውጤት ነውና ። አቤልም እስካሁን ድረስ የሚናገረው በስብከቱ ፣ በመጻሕፍቱ ሳይሆን በመሥዋዕቱ ነው ። ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክታቱ እስካሁን ይናገራል ፣ አቤል ደግሞ በመሥዋዕቱ እስካሁን ድረስ ይናገራል ። ሰው ሁሉ የሚናገርበት አንድ ነገር ያስፈልገዋል ፤ ከሞተ በኋላ የሚናገር ሥራ ያሻዋል ። ሌሎች ነገሮች ሁሉ የሚያስወቅሱ ሲሆኑ በእግዚአብሔር ስም የተደረጉ ነገሮች ግን ቋሚ ሁነው ይኖራሉ ። ሰው በሥራው ሕያው ሁኖ ይኖራል ። ስም ከመቃብር በላይ ነው እንዲሉ ስምን መቅበር አይቻልምና መልካም መሥራት በማይኖሩበት ዘመን መግዛት ነው ። ጻድቃን በዘመናቸው ስደተኛ ናቸው ፣ ያለ ዘመናቸው ግን ትውልድን የሚማርኩ ናቸው ። የሰናዖር ግንብ በዘመኑ የተደነቀና መላው ዓለም ያወራለት ነበር ። ዛሬ ግን የሚያስበው የለም ። ከሰናዖር ግንብ በፊት የነበረው አቤል ግን በአንድ ቀን መሥዋዕቱ ሲታወስ ይኖራል ። ፈርዖን በዘመኑ ዓለምን ያንቀጠቀጠ ንጉሥ ፣ ተፈሪና ተደናቂ ነበር ፣ ዛሬ ግን ትዕቢት የሚያስከፍለውን ዋጋ የሚያብራራ መዝገበ ቃላት ሁኗል ።

በሙሴ ሕግ የመሥዋዕት ዓይነታቸው ተጠቅሷል ። የአቀራረባቸው ሥርዓትም ተገልጧል ። ማንም ሰው እንደ ፈለገው ማምለክ አይችልም ። የአምልኮን ሕግ ማወቅ አለበት ። እግዚአብሔር መሥዋዕትን የፈለገው ዋጋ መክፈል አስፈላጊ መሆኑን ሊገልጥልን ነው ። መሥዋዕት ለማቅረብ እንስሳውን በገንዘብ መግዛት ያስፈልጋል ። ዋጋ የማይከፈልበት ነገር እንደ ቀላል የሚቆጠር ፣ ደግሞም እርካታ የሌለው ነው ። ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ፣ መጻሕፍትን መማር ዋጋ ያስከፍላል ። አምልኮተ እግዚአብሔርን ለመፈጸም የጊዜ ፣ የገንዘብ ፣ የእንቅልፍ ፣ የጉልበት ዋጋ ይከፈላል ። እውነተኛ ፍቅር ዋጋ የሚከፍል ነው ። ሰዎች ዋጋ ከፍለው ወደ እኛ ሲመጡ እውነተኛ ጓደኞቻችን መሆናቸውን እንረዳለን ። እግዚአብሔርም ዋጋ ከፍለው ወደ እርሱ በሚመጡት ደስ ይለዋል ።

መሥዋዕት ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ነው ። እግዚአብሔር አምልኮቱን ማንም አይጋራውም ። ከእርሱ ጋር ተካክሎ የሚሰገድለት ማንም የለም ። ጉልበት የሚቀደሰው ለእግዚአብሔር ሲሰግድ ነው ። ለእግዚአብሔር የሰገደ ለጨካኞች ፣ ለገንዘብና ለጥቅም አይሰግድም ። ለመኖር ብሎም አይዋሽም ። መሥዋዕት የሚታረድ ነው ። የታረደ ነገር መልሶ ሕያው መሆን አይችልም ፣ ለታረደለት አምላክ እንደ ተሠዋ ይቀራል ። ለእግዚአብሔር የሰጡትን ነገር መልሶ መቀበል አይገባም ። በመንፈሳዊ ውሳኔም መጸጸት ወግ አይደለም ። አገልግሎትን ከጀመሩ ፣ ገዳም ከገቡ ፣ ምንኵስናን ከተቀበሉ በኋላ መጸጸት አይገባም ። ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ ቢሉ መንገዱ አውሬ ያለበት ፣ ድልድዩ የተሰበረ ነው ። መሥዋዕት ስጦታ ነው ። የተሰጠ ነገር አይመለስም ። እንኳን የሰጡትን ቃል የገቡትንም ነገር ማጠፍ ተገቢ አይደለም ። መሥዋዕት የሚቀደሰው በእሳት ነው ። መንፈሳዊነትም እሳታዊ የሆነ ፍቅር ይፈልጋል ። ፍቅራችን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደመጣንበት እንደ መጀመሪያው ጊዜ አይደለም ። በብዙ ነገር ተባርደናል ። መሥዋዕቱ ሲያርግ ቀጥታ ወደ ላይ ነው ። አምልኮታችንም አድራሻው ሰማይ ነው ። መሥዋዕት በምድር ላይ ላሉት ሽታው አይጣፍጥም ፣ በሰማይ ያለው ጌታ ግን በደስታ ይቀበለዋል ። እግዚአብሔርን ማስቀደማችን በቤተሰባችን ፣ በትዳራችን ላይወደድ ይችላል ። ብዙዎችም ሊነቅፉን ይችላሉ ፣ እግዚአብሔር ከተደሰተ ግን በቂያችን ነው ። የመኖር አቅማችን የእግዚአብሔር ደስታ ነው ።

መሥዋዕት ሞቶ ሕያው የሚሆን ነው ። በአካል ሞቷል ፣ በገለጠው ፍቅር ግን ሕያው ሁኖ ሲታሰብ ይኖራል ። እውነተኛ ክርስቲያንም ለዚህ ዓለም ነገር የሞተ ፣ ለእግዚአብሔር ግን የሚኖር ነው ። የእህሉን ቍርባን ስናስብ ብዙ ሂደት ያለፈ ነው ። ስንዴ ከቤት ወጥቶ ይዘራል ፣ ከአባት እናት አብራክ ተከፍለን በዚህ ዓለም ላይ ተዘርተናል ። በብዙ ፈተና ውስጥ ያድጋል ፣ ከበሽታ ፣ ከረሀብ ፣ ከጥፋት አምልጠን ኖረናል ። ይታጨዳል ፣ ከዚህ ዓለም ተለይተን ክርስቶስን እንመርጣለን ። ይወቃል ፣ ደካማ አስተሳሰባችን ይወገዳል ። ይለቀማል ፣ ክፋትን እንተዋለን ። ይበጠራል ፣ በአስቸጋሪ መንገድ እናልፋለን ። ይፈጫል ፣ ትዕቢትን እንጥላለን ። ይጋገራል ፣ ለዚህ ዓለም ክብር እንሞታለን ፤ ይበስላል ፣ በመንፈሳዊ ነገር እናድጋለን ። ይበላል ፣ ለሌሎች ጠቃሚ እንሆናለን ። ይሠዋል ፣ ሕይወታችንን ለእግዚአብሔር እንሰጣለን ።

ሐዋርያው፡- “እንግዲህ ፥ ወንድሞች ሆይ ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው” ይላል ። (ሮሜ. 12፡1)። በብሉይ ኪዳን መሠዊያ ላይ ይቀርብ የነበረው ሙት መሥዋዕት ነው ፣ በአዲስ ኪዳን ግን ሕያው መሥዋዕት ተፈልጓል ። መሥዋዕት ብሎ ሕያው በራሱ አስገራሚ ነው ። መሥዋዕት ከሆነ ሕያው አይሆንም ፣ ሕያው ከሆነ መሥዋዕት መሆን አይችልም ። እግዚአብሔር የፈለገው ሕያው መሥዋዕትን ነው ። የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች ምሳሌ ነበሩ ። እውነተኛው መሥዋዕት አንድ ጊዜ ታርዶ የሚሞት ሳይሆን ዘወትር ፈቃድን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ማስገዛት ነው ። ይህም ከራሳችን ጋር ጠበኛ እንዳንሆን ያደርገናል ። አገልግሎታችን ቅንነት ካለው የአእምሮ ሰላም ይኖረናል ። በየቀኑ ጊዜአችንን ለእግዚአብሔር በመስጠት ፣ ገንዘባችንን ለወንጌል መፋጠን እየሠዋን ፣ ክፋትን እየጣልን ፣ ከአገልጋዮች ጋር አብረን እያገለገልን ሕያው መሥዋዕትነታችንን መጠበቅ አለብን ።

እግዚአብሔር ይርዳን !

ሐምሌ 3 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ