ጸሎትና የእኛ ዘመን
ክፍል ሁለት
ምስኪንን ሰው ሁሉ ይንቀዋል ፣ እንዲያጫውታቸው ይፈልጉታል ፣ እንደሚበልጡት ያስባሉና ደስታ ይሰማቸዋል ። እንደ ኳስም የሚጫወቱበት ሰው ያገኙ ይመስላቸዋል ። ጸሎት የተሠራው ለእነዚህ ምስኪኖች ነው ። ማንም ሰው በልብ መሰበር ሁኖ ካልቀረበ ጸሎት ሊጠቅመው አይችልም ። ሰዎች ከዚያ አልፈው ጸሎትን ጸሎተኛ ለመባል ይጠቀሙበታል ። ዓይናቸው ወደ ሰማይ ቢያንጋጥጥም ልባቸው ግን ወደ ሰው ክብር ያስሳል ። ሃይማኖትን እንደ ንግድ ፈቃድ መጠቀም ከባድ ነው ። የሚለምነንን ሰው አንዴና ሁለት ጊዜ በደስታ እንሰጠዋለን ፣ ከዚያ በኋላ ደስተኛ አንሆንም ። ሰው በጠባዩ መለመን አይወድም ። ጸሎት ግን የተሠራው ብዙ ልመና ላላቸው ሰዎች ነው ። እግዚአብሔር መለመን ክብሩ ነው ። ፊታቸው የተከፋ ፣ እንባ ሊያመልጣቸው የሚታገላቸው ፣ ብሶተኛ ሰዎችን እንሸሻለን ። ጸሎት ግን ለእነዚህ ምንዱባን መጠጊያ ነው ። ኃጢአቱ የሚረብሸው ኃጢአተኛ ፣ ሁሉ የፈረደበት ወንጀለኛ አንድ በር ብቻ ተከፍቶ ይታየዋል ፣ እርሱም ንስሐ ነው ። ጸሎት ንስሐ ማፍሰሻ ፣ ምሕረት መቀበያ ነው ። በተንቀለቀለ ልብ የሚመጡ ሁሉ የጸሎት በር ይከፈትላቸዋል ። ጸሎት ለመጸለይ ምሁርነት ፣ ጥሩ የጀርባ ታሪክ ፣ በሰዎች ዘንድ ተደማጭነት ማትረፍ አያስፈልገውም ። እንደውም ጸሎትን በእውነት የሚጸልዩት ከብርቱዎች ይልቅ ደካሞች ናቸው ። ከልብ የሚመነጭ ጸሎት እንድናቀርብ በሕመምና በጭንቅ ውስጥ ልናልፍ እንችላለን ።
ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ማድረግ ነው ። እርሱ የሚያስፈልገንን ያውቃል ። እናት ለልጅዋ የሚያስፈልገውን አውቃ ትሰጣለች ። ልጅዋንም ማግኘት ትሻለች ። እግዚአብሔር ፍላጎታችንን በመልእክተኛ ለመላክ ፣ ወይም ተኝተን ስንነቃ ምግቡን ለማስቀመጥ አይፈቅድም ። ከእርሱ ጋር በጸሎት ኅብረት እንድናደርግ ይፈልጋል ። የልባችንን ስንነግረው የልቡን በቃሉ በኩል ይነግረናል ። ወደ ሞት እየሄደና እየቀዘቀዘ ያለው መንፈሳችንም ጤና ማግኘት ይጀምራል ። እግዚአብሔርን ስናገኝ የእግዚአብሔር የሆነውንም እናገኛለን ። እኛ በጸሎት ለእግዚአብሔር ስንናገር እግዚአብሔር ለእኛ በቃሉ በኩል ይናገራል ። እግዚአብሔር እንዲናገረን ቅዱሳን መጻሕፍትን ማንበብ አለብን ። ጸሎትን የልጅነት መብት አድርጎ የሰጠን ፣ በአባትነቱ ጥላ ያሳረፈን እግዚአብሔር ነው ። መብት ሁሉ ግዴታ አለው ። እርሱም የድሆችን ጩኸት መስማት ነው ። የሰው ገንዘብ ነክቼ አላውቅም እንላለን ። እውነት ሊሆን ይችላል ። የእግዚአብሔርን ገንዘብ ግን ሰርቀናል ። ለወንጌል ሥራ አሥራት አላወጣንም ፣ አገልጋዮች ሲቸገሩ ቆመን ተመልክተናል ። ድሆችን በረሀባቸውና በእርዛታቸው አላሰብናቸውም ።
“እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳሁ” የሚለውን ጥቅስ ሁላችንም እንወደዋለን ። እኛ የእርሱን በር የምናንኳኳ ይመስለን ነበር ። ለካ እውነቱ እርሱ የእኛን በር ማንኳኳቱ ነው ። በሩ ሲንኳኳ አንዳንዱ ምግቡን ይዞ ይሮጣል ። ይህ የእግዚአብሔርን ገንዘብ ለእግዚአብሔር አለመስጠት ነው ። በሩ ሲንኳኳ አንዳንዱ ቤቱን ለማስተካከል ይጥራል ። በሩን ብቻ እንክፈት ፣ እርሱ ያስተካክለዋል ። ጸሎት የልብን በር ለእግዚአብሔር መክፈት ነው ። እንድንጸልይ በብዙ መንገድ እያንኳኳ ነው ። በስጦታው ፣ በፍቅሩ ፣ አንዳንድ ጊዜም በስህተታችን ውጤቶች እያንኳኳ ነው ። “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” ይላል ። (ራእ. 3 ፡ 20) ። ሦስት ነገሮች በዚህ ውስጥ ያስደንቁናል ። የመጀመሪያው ይህ መልእክት የተላለፈው ለለዘብተኛዋ ቤተ ክርስቲያን ነው ። ይህች ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻዋን ዘመን ማኅበረ ምእመናን ትወክላለች ። ዓለሙም ሰማዩም ፣ ትዳሩም ምንኵስናውም ፣ ኃጢአቱም ጽድቁም አይቅርብኝ የምትል ሚና የለሽ ማኅበረ ምእመናን በመጨረሻው ዘመን ትነሣለች ። ጌታ ለዚህች ለዘብተኛና የጸሎት መባረድ ለገጠማት አካሉ ይናገራል ። ትልቁ ለዘብተኛነት ጸሎትን ችላ ማለት ነው ።
ሁለተኛው ነገር ለጸሎት የሚቀሰቅሰን እርሱ ነው ፣ ያንኳኳል ። ጸሎት ፀሐይን ለማውጣት የሚደረግ ጥረት ሳይሆን በርን ከፍቶ ብርሃንዋን ማስገባት ፣ ልብስን ገልጦ ሙቀቷን መውሰድ ነው ። ጸሎት ሙሉ በሙሉ የጸጋ መንገድ ነው ። እግዚአብሔር የሚሰማን በቸርነቱ ነው ። እንኳን ስጦታውን ሥጋውና ደሙንም የሰጠን በነጻ ነው ። ሦስተኛው በሩን የሚያንኳኳበት ሰዓቱ ምሽት ነው ። ሲመሽ የሚመጣ አምላክ መሆኑን አዳምን በፈለገበት ሁኔታ እንረዳለን (ዘፍ. 3 ፡ 8) ። የዓለም ዘፈኑ እንኳ፡- “ጭር ሲል አልወድም” የሚል ነው ። ጭር ሲል ፣ ሲመሽ የሚመጣ ፣ የቀኑን የክትና የማዕረግ ልብስ ስናወልቅ የሚደርስ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ከእኛ ጋር እራት እንደሚበላ ነግሮናል ፣ እራት ትልቅ የክብር ግብዣ ነው ። በምድር ደግሶ ያበላናል ፣ በሰማይ ደግሶ ይጠብቀናል ። ምን ዓይነት አምላክ ነህ ! ቀኑ ሲጨልም ትመጣለህ ። ጉልበትም ፣ ሥልጣንም ሲመሽበት አንተ ትደርሳለህ ። በጉብዝናችን ብንኮራብህም ሲንንገዳገድ ወዳንተ መጥተናል ። ሳትታዘብ ተቀበልከን ። ተመስገን ። ወደ አንተ መምጣት እንደማንችል አውቀህ ወደ እኛ መጣህ ። ከብዙ ዘመን በፊት ዛሬን አየሃት ፣ ቀድመህ ሁሉን አዘጋጀህልን ፣ ለስምህ ክብር ምስጋናን እንሰጣለን ።
አሜን !
ሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም.