የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዘወር በሉ

“እንግዲህ፡- ኢየሱስ ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል ያጠምቅማል ማለትን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ጌታ ባወቀ ጊዜ፥ ይሁዳን ትቶ ወደ ገሊላ ደግሞ ሄደ፤ ዳሩ ግን ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም” /ዮሐ. 4፥1-3/።
ዓለም ሰፊ ነው ። እዚህ አለመፈለግ ሁሉ ቦታ አለመፈለግ አይደለም ። በአንድና በአሥር ሰው መጠላትም በሰው ዘር ሁሉ መጠላት አይደለም ። ዓለም ሰፊ ነውና ከዚህ ሲገፉን ወደ ሌላ ዘወር ማለት ፣ ጠላቶች ሲያስጨንቁን የሚጸልዩልንን ወዳጆች ማሰብ ተገቢ ነው ። አቤልን የጠላው አንድ ቃየን ነው። አቤል ግን እስከ አሁን ሊቀ ሰማዕታት ሁኖ ይኖራል ። ኖኅን አልሰማ ያለው ሕዝብ በዚያ ዘመን ቊጥር ምናልባት ሁለት መቶ ሺህ ቢሆን ነው ። ዛሬ ያለው ስምንት ቢሊየን ሕዝብ ግን የኖኅ የልጅ ልጅ ነው ። ዮሴፍ እረኛ እንዳይሆን ወንድሞቹ ገፉት ። በእረኝነት ቀንተውበት እርሱ ግን የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ ። በከነዓን ይሸጣል ፣ በግብጽ ይገዛል ። አዎ ዓለም ሰፊ ነው ፣ የሰው ዘርም ስምንት ቢሊየን ነው ። ይልቁንም በብቸኝነት ስሜት ለሚንገላቱ ወገኖች እግዚአብሔር አንድ ብርሃን ያበራላቸዋል ብለን እናምናለን ። ይኸውም በቅዱሳን መላእክት መከበባችን ነው ። እያንዳንዱን ሰው በቀንና በሌሊት የሚጠብቁት ቅዱሳን መላእክት አሉ /ማቴ. 18፥10/። ከእነዚህ በተጨማሪ እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ሰዎች ብዙ ሠራዊት ይላክላቸዋል ። “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል” ይላል /መዝ. 33 ፥ 7/። የመላእክት ሰራዊት ከከበበን ብቸኛ አይደለንም ። የከበቡን ቅዱሳን ናቸው ፣ የተለዩን ግን ከዳተኞች ናቸው ። ያተረፍነው ሌላ ፈተና የማይገጥማቸውን ተፈትነው ያለፉትን መላእክት ነው። አጣን የምንለው ግን ፈተናቸውን ያልጨረሱትን ነው ። የተገፋነው ከአንድ ስፍራ ነው ፣ ሰማይ ግን የእኛ ነው ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል ያጠምቃል ማለትን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ባወቀ ጊዜ ደቡባዊውን ይሁዳ ትቶ ወደ ሰሜን ገሊላ ሄደ ። የአክራሪዎችን የፈሪሳውያን መዲና ትቶ ወደ ገሊላ ዘወር አለ ። እነዚህ ፈሪሳውያን ጌታችን ዮሐንስ መጥምቅን በሦስት ነገሮች እንደ በለጠ አስተውለዋል፡-
1-  በትምህርቱ
2-  ደቀ መዛሙር በማድረጉ
3-  በጥምቀቱ
ዮሐንስ መጥምቅ በምድረ በዳ ተቀምጦ ከረበሻቸው መቅደስ ድረስ መጥቶ የሚያስተምረው ክርስቶስ ይበልጥ ይረብሻቸዋል ። የዋዜማው አገልጋይ ዮሐንስ መጥምቅ ካሰጋቸው ፣ የበዓሉ ድግስ የሆነው ክርስቶስ ይበልጥ ያሰጋቸዋል ። መንገድ ጠራጊው ይጥፋ ካሉ ንጉሡን የበለጠ ይጠሉታል ። ጌታችን ይህንን ስሜታቸውን አወቀ ። ሁሉ ተምሮ አይለወጥም ። የማይለወጠውን መጠንቀቅ መልካም ነው ። ሞት የማይቀር ቢሆንም ያለ ቀኑ መሞት ግን ክብር የለውም ። ስለዚህ ጌታችን ወደ ገሊላ ዘወር አለ ። ጌታችን ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል የሚለውን ቃል ይናገሩ የነበሩት ያመኑት ሕዝቦች ናቸው ። ሕዝቡ በደስታ የሚናገረውን ፈሪሳውያን ግን ጥርሳቸውን ነክሰው ይሰሙ ነበር ። የአንዱ ደስታ ለአንዱ ኀዘን ነው ። ፈሪሳውያን ከእነርሱ ውጭ የሚደነቅ ሲመጣ የልባቸው ትርታ ሊቆም ይደርሳል ። ያንን ሰው በመብለጥ ከመገለጥ ወይም ያጎደሉትን ለመሙላት ከመፈለግ ማጥፋትና እጃቸውን በደም ማጨቅየት ይመርጣሉ ። ሉተር አብዮት አድርጎ የፕሮቴስታንት እምነትን ሲመሠርት ስለ ክርስቶስ እየተናገረ ብዙ ሕዝብን ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወሰደ ። መላው ዓለም ሊከዳት መሆኑን ያወቀች ካቶሊክ ኢየሱሳውያን የሚባሉ መልእክተኞችን ወደ ዓለም ላከች ። እነዚህ ሰዎች ስለ ክርስቶስ የሚናገሩና የሚመሰክሩ ናቸው ። እነርሱ በደረሱበት አካባቢ የፕሮቴስታንቱ ንቅናቄ ክርስቶስ እያለ ሲመጣ አስቀድመን ሰምተናል እያለ ይመልሳቸዋል ። ቀድሞ ጆሮን ከያዙ ቀጥሎ ለሚናገረው ቦታ የለውም ። ይህንን ሰዋዊ ስልት በመንደፍ ካቶሊክ ራሷን አትርፋለች ። ፈሪሳውያን ግን ይህንን ብልሃት እንኳ ማየት አልቻሉም ። ዓሣውን ከነባሕሩ ወደ ማድረቅ እርምጃ ይገባሉ ።
ጌታችን ከይሁዳ ወደ ገሊላ ዘወር ያለው ሁለት ወገኖችን ሰግቶ ነው ፡-
1-  አድናቂዎችን
2-  ፈሪሳውያንን
 አድናቂዎች አማኞች አይደሉም ። እውነተኛ መደነቅ እግዚአብሔርን ለማመስገን ያበቃል እንጂ ለፍላፊ ብቻ አያደርግም ። አድናቂዎች ጠላት የለባቸውም ተደናቂው ግን በየሰዓቱ ጠላት ይመረትበታል ። አድናቂዎች የእውነትን ድንበር የሚዞሩ እንጂ በእውነት ግዛት ውስጥ የሚጠለሉ አይደሉም። የእውነትን ቅርፊቱን የሚልሱ እንጂ ቡጡን የሚገምጡ አይደሉም። ጌታችን እምነት የሌለበትን ከንቱ ውዳሴ ሸሸ ። ውዳሴን ከንቱ የሚያደርገው የሚናገሩት ሰዎች የእምነት ልብ ከሌላቸው ነው ። እንዲህ ያለው ውዳሴ ዓላማው ተደናቂውን ትዕቢተኛ ማድረግ ነው ። አድናቂዎች ራሳቸውን እንደ ደረጃ መዳቢ ቆጥረው አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ ሲያደርጉ ይውላሉ ። ይህ ብቻ አይደለም ። ትላንት ያመሰገኑትን ሰው ዛሬ ሲራገሙ ይሉኝታን እንኳ አይፈሩም ። እነዚህ ሰዎች በሰማበት ጣዱኝ የሚሉ ለአሙቁልኝ የሚፈለጉ ናቸው ። ጌታችን እነዚህን ሰዎች ሸሸ ። ዓለም የሁሉም ቤት ናት ፣ የአማኙም የከሃዲውም ፣ የደጉም የክፉውም ቤት ናት ። ይህ የእግዚአብሔርን የነጻነት አምላክነት የሚያሳይ ነው ። የምንኖርበትን ዓለም እንዲሁም ሰዎች ጠባይ ማወቅ ግን ከብዙ ጉዳት ይጠብቃል ። የብዙ ጉዳታችን ምንጩ አለማወቅ ነው ። ዛሬ የሚያስደነግጡን ሰዎች ዛሬ አመል አውጥተው አይደለም ። የነበራቸውን አመል እንዳናይ ግን በውዳሴ ከንቱ ስላሳወሩን ነው ። ጉቦና ውዳሴ ከንቱ የተቀባዩን ልብ ያሳውራል ። ጌታ ከእነዚህ ሰዎች ሸሸ ። ለአገልግሎቱ በመሰሰት ሥር እንዲሰድድ ያደረጉት ጥረት የለም ። ገዳዮች ቶሎ እንዲገድሉ ግን ማነሣሣት ጀመሩ ። ከከንቱ አድናቂ ጥሩ ተቃዋሚ ሥራ ያሠራል ።
ጌታችን የሸሸው በሁለተኛ ደረጃ ፈሪሳውያንን ነው ። ፈሪሳውያን በሃይማኖት ካባ ውስጥ ሁነው ወንጀል የጣማቸው ፣ ለመግደል ሳይሆን ለአገዳደል ስልት የሚጨነቁ ሰዎች ናቸው ። ፖለቲካውንና ስልቱን የሚያከብሩ እንጂ እግዚአብሔርን የሚፈሩ አልነበሩም ። ቄሣርን ከልባቸው ለማገልገል ሲፈልጉ እንጀራ የሆናቸውን እግዚአብሔር ግን አያከብሩም ነበር ። እነዚህ ፈሪሳውያን ዮሐንስ መናኔ ንብረት መሆኑ ሕመም ሁኖባቸው ነበር ። እነርሱ ያቃታቸውን ሌላው ሲያደርገው ምንድነው ምሥጢሩ ? ከማለት እኛን ያሳጣናል ብለው ለመግደል ይፈልጉ ነበሩ ። ቅንዓታቸውም ገደብ ስላጣ በእግዚአብሔር ልጅ ቀንተው እስከ መስቀል ደረሱ ። ቅንዓት ገደቡን ሲስት በእግዚአብሔርም ይቀናል ። ቅናት በዝግታ አያስቀምጥም ። አእምሮን ለውጦ እስከ መግደል ያደርሳል ። የቀኑበትን ሰው ወይ በአካል ካልተቻለም በኅሊና በመግደል እንዲወገድ ይፈልጋሉ ። ጌታችን ዘወር አለ ።
ገሊላ መሸሻ ነበረች ። ከአሕዛብም ሆነ ከአይሁድ የሆኑ ሰዎች በነጻነት የሚንቀሳቀሱባት አውራጃ ናት ። ከስሜታውያንና ከአክራሪዎች መሸሻ የነበረችው ገሊላ ናት ። ገሊላ ሰፊ ናት ። ልበ ሰፊዎችም እንደ ገሊላ መሸሻ ናቸው ። ጌታችን ደቀ መዛሙርትን የመረጠውም ከገሊላ ነው ። ደቀ መዛሙርት ልበ ሰፊ መሆን አለባቸው ። በአንድ ጥቅስ የማይፋንኑ ፣ በደህና ደመወዝ የማይመኩ ፣ በአድናቂዎች አፍ የማይወድቁ ፣ ገና ለማወቅ የሚኖሩ ፣ መሠረት ይዘው ሕንጻውን ለማሳደግ የሚጥሩ ሊሆኑ ይገባቸዋል።
1-ጥቂት እውቀትን ከስድብ ጋር የያዙ
2-የሰማይን ዋጋ ረስተው በምድር ገንዘብ የሚመኩ
3-  ያስተማሩትን ትምህርት እንዴት ነበር ? እያሉ አድናቂ የሚሹ
4-  ትምህርትን የጠገቡ
5-  ሃይማኖታዊ መሠረት የሌላቸው
6-  በሁለንተናዊ እድገት የማያሳዩ
7-  ሁሉን ሰምተው የተሻለውን ለማሳየት ልበ ሰፊ ያልሆኑ ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ አይችሉም ።
ጌታችን ብዙ ጊዜ ዘወር ይል ነበር ። ምንም እንኳ ለመሞት ቢመጣም ያለ ጊዜው ላለመሞት ተጠንቅቋል ። እርሱ ከባላጋራዎቹ ጋር በነበረው ሙግት ያለፈው ፡-
1-  የእግዚአብሔርን ቃል በመጥቀስ ፡- እናምነዋለን የምትሉትን ቃል አታምኑትም ለማለት ይጠቅስላቸው ነበር ።
    2-  ጥያቄን በጥያቄ በመመለስ ፡- መልሱን እስኪፈልጉ እርሱ መልእክቱን ለሰሚው ሕዝብ ያስተላልፍ ነበር ።
      3-  በመገሰጽ፡- ከታላቅ ፍቅርና ከያገባኛል ስሜት የሚመነጨውን ተግሣጽ በማስተላለፉ እንዳልጠላቸው አሳይቷል ።
      4-  መስቀለኛ ጥያቄ በማቅረብ፡- ከጠሉት ክርስቶስ ሳይሆን ካከበሩት ከዮሐንስ ጋር በማፋጠጥ
      5-  ሊወግሩት ሲፈልጉ ዘወር በማለት፡- ለእውነት መወገር ክብር ነው ። ነገር ግን ሰማዕትነት በጣም ግድ ሲሆን ካልሆነ እየቆሰቆሱ ሰማዕት መሆን ክብር የለውም ። ለምን ? ቢሉ እኛ ሰማዕት ስንሆን ያ ሰው ግን ነፍሰ ገዳይ እየሆነ ነውና ።
      6-  በጊዜው እጁን በመስጠት ፡- ብዙ ጊዜ ሊገድሉት ሲሉ ዘወር አለ ። በሐሙስ ምሽት ግን በፈቃዱ ተያዘ ።
      7-  ይቅርታን በመስጠት፡- በመስቀል ላይ ይቅር ብሏቸው አባቱ ይቅርታ እንዲያደርግላቸውም ለመነ ። የመጀመሪያው የመስቀሉ ጩኸት ለጠላቶቹ ይቅርታ የለመነበት ነው ። ምክንያቱም ሰቅለውት ሳይሄዱ ይቅርታውን እንዲሰሙ ብሎ ነው ። እነርሱ ያላቸውን ሰጡ ፣ እርሱም ያለውን ይቅርታ ሰጣቸው ።
 እልፍ ማለት ወይም ዘወር ማለት ብዙ ጥቅም አለው ። ዘወር ማለት በአካል ብቻ አይደለም ። አንዳንዴ ችግሮች የሚመጡበትን መንገድ በመዝጋትም ዘወር ማለት ይቻላል ። ዘወር ማለት ብዙ ጥቅሞች አሉት ። የእኛን ኅሊናና ሕይወት ከሞት ሲያድን የሌሎችን ኃጢአትም ይቀንሳል ። ያልሰሙት ነገር አይቆጭምና አለመስማትም ዘወር ማለት ነው ። እግዚአብሔርን ሲያዩ ጠላት ያንሳልና ስለ ጠላት ርእስ ይዞ አለማውራትም ዘወር ማለት ነው ። ሰዎች በስሜት ያደረጉብንን እኛም በስሜት ስንመልስ በማግሥቱ ሁለታችንም በጸጸት ውስጥ እንወድቃለን ። ዘወር ማለት ግን ቤትንና ኅሊናን ያተርፋል ። ዘወር ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መስማማት ነው ። በንስሐ ከእርሱ ጋር መታረቅ ዘወር ማለት ነው ። ከዚያ በኋላ የእኛ ተከራካሪ እርሱ ይሆናል ። እግዚአብሔር ካስጠጋንም ማንም ወደ ውጭ አያወጣንም ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ