የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የጾታ ግንብ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያፈረሰው የዘረኝነትን ግንብ ብቻ አይደለም የጾታ ግንብንም አፍርሷል ። በሰማርያ ሊያልፍ ግድ የሆነበት በዚህ ምክንያት ነው ። ሴቶች ከተንቀሳቃሽ ዕቃ ተለይተው የማይታዩበትን የዚያን ማኅበረሰብ አስተሳሰብ ጌታችን ሻረ ። የሻረው በሰማርያ በማለፉ ብቻ አይደለም ። ገና በጽንሰቱ ነው ። እርሱ በሥጋ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ የሴት ዘር ሁኖ ነው የመጣው ። እርሱ የሴት ዘር ነው ። በዚህም ሴትን አክብሯል ። እናቱን እመቤታችን ድንግል ማርያምን እየታዘዘም ሠላሳ ዓመት ኑሯል ። ሴት መባል የማነስ ወይም የጉድለት መጠሪያ ሳይሆን የክብር መጠሪያ መሆኑን ለመግለጥ እናቱን ድንግል ማርያምን “አንቺ ሴት” በማለት ጠርቷታል ። ሔዋን ከአዳም ጎን ተገኝታ ነበር ። ዳግማዊ አዳም ደግሞ ከድንግል ማርያም ተገኘ። ሔዋን ከአዳም ጎን ስትገኝ ያለ እናት ነው ። ዳግማዊ አዳም ክርስቶስም ከድንግል ማርያም ሲገኝ ያለ አባት ነው ። ሔዋን ከአዳም ጎን ስትገኝ ከአዳም አጥንት አልጎደለም ። እንዲሁም ጌታችን ከድንግል ማርያም ሲወለድ ማኅተመ ድንግልናዋ አልተለወጠም ።
ጌታችን በጽንሰቱ ሴትን አከበረ ። እርሱ በምድር ላይ አባት የሌለው የሴት ዘር ነው ። ሠላሳ ስድስት ቅዱሳት አንዕስትን ከመቶ ሃያው ቤተሰብ ጋር ቆጥሯል ። ብዙ ሴቶችም በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበር ። ትንሣኤውንም የገለጠው ለሴቶች ነው ። ሁሉም ፈርቶ በተቀመጠበት በዚያ ሌሊት ጨለማውንና የአይሁድን ዛቻ እንዲሁም የወታደሮችን ግርማ ደፍረው ወደ መቃብሩ የሄዱት ሴቶች ናቸው ። ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ብዙ ገድል የፈጸሙ የወንጌልን ሩጫ በሁለንተናቸው ያገዙ ናቸው ። ክርስትናን ለማሳነስ የሚፈልጉ ወገኖች ሴቶች እንዴት ከክህነት ይገለላሉ ? በማለት ይተቻሉ ። ክህነት ግን ለተማረ ሁሉ አይሰጥም ። ጌታችን ሐዋርያነትን ከመቶ ሃያው ቤተሰብ ለአሥራ ሁለቱ ሰጠ ። ሐዋርያነት ያልተሰጣቸው ሰባ ሁለት አርድእትም ነበሩ ። የሥራ ድርሻ የመብለጥና የማነስ ምልክት አይደለም ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሴትን ክብር ሊያስመልስ መጥቷል ። ቀድሞ በፍጥረትም የከበረች ናትና ። “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ይላል /ዘፍ. 1፥27/። ሴትና ወንድ መሆን የሰብእና ልዩነት ሳይሆን የጾታ ልዩነት መሆኑን ይነግረናል ። ሴትና ወንድ መሆን የአንዱ ሰው ሁለት ክፍሎች ማለት ነው ። እግዚአብሔር አምላክ ምንጩን አንድ ለማድረግ አዳምን ፈጠረ ። ከአዳም ሔዋን ተገኘች ። ስለዚህ አንዱ ሰው ሁለት ሆነ ። እንደገና በጋብቻ ሁለቱን አንድ አደረጋቸው። በጋብቻ አንድ ከሆኑ በኋላ ልጆችን በመውለድ ብዙ ሆኑ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ስለ ብዙ ታላላቅ ሴቶች እናነባለን ። ከሁሉ በላይ ከሴቶች ተለይታ የተባረከችው ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን ስናስብ የሴት ዓለም መመኪያ እንደሆነች እንረዳለን ።
ጌታችን ያችን ሳምራዊት ሴት ለማግኘት መሄዱ ይህንን መገለል ለመሻር ነው ። እርሱ ወደ ቀደመው የፍጥረት ክብር ሊመልሰን መጥቷልና ። የቀደመው የፍጥረት ክብር አንዱ አንዱን እንዲረግጥ ሳይሆን አንዱ በአንዱ ውስጥ ያለውን ክብርና ጸጋ እንዲቀበል ነው ። ይህችን ሳምራዊት ሴት በማናገሩ ደቀ መዛሙርቱ ሳይቀር ደንግጠዋል ። “በዚያም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ መጡና ከሴት ጋር በመነጋገሩ ተደነቁ፤ ነገር ግን። ምን ትፈልጊያለሽ? ወይም። ስለ ምን ትናገራታለህ? ያለ ማንም አልነበረም” /ዮሐ. 4፥27/። የአይሁድ መምህራን ከሴት ጋር በአደባባይ አይነጋገሩም ። ደቀ መዛሙርቱም ይህ አስተሳሰብ አለቀቃቸውም ነበር ። ጌታችን ግን በአገልግሎት ዘመኑ ፡-
–    ከሴት ወይም ከድንግል ተወለደ ።
–    ብዙ ሴቶችም በገንዘባቸው ያገለግሉት ነበረ ።
–    ኃጢአተኛ ሴቶችን ከንቀትና ከመወገር አዳነ ።
–    ትንሣኤውን ለሴቶች ገለጠ ።
ቤተ ክርስቲያንም በአገልግሎት ዘመኗ የሴቶችን እምነት አክብራለች ። ቅደስት በማለትም ብዙ ሴቶችን ሰይማለች ። የመታሰቢያ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንም አንጻለች ። ጌታችን በሰማርያ ሊያልፍ ግድ የሆነበት ይህን የጾታ ግንብ ለመናድ ነው ። ሰዎች እናታቸውን እያከበሩ የልጃቸውን እናት ወይም ሚስታቸውን ግን ማክበር ይከብዳቸዋል ። እግዚአብሔር ከመረጠልን ነገር አንዱ ጾታችን ነውና እርሱ በሰጠን ነገር ደስ ሊለን ይገባል ።
የመልክአ ምድር ግንብ
 ጌታችን በሰማርያ ሊያልፍ ግድ የሆነበት የመልክአ ምድር ግንብን ለማፍረስም ነው ። ይህንንም በሁለት መንገድ እናየዋለን ። የመጀመሪያው ሰማርያና ይሁዳ የሚለውን የድንበር መስመር እግዚአብሔር አላስቀመጠም ። ከላይ ወደ ታች ሲታይ ከድንበር ወዲያና ከድንበር ወዲህ አፈር አንድ ነው ። ከላይ ስናየው የሚታይ ምንም መስመር የለም ። ሕሊና ግን መስመር እያበጀ ይፋለማል ። ወገንተኝነትን የሚወልደው የታች አስተሳሰብ ነው ። አስተሳሰባችን ከፍ ሲል የሚታየን አንድ ምድር አንድ የሰው ዘር ነው ። አውሮፓውያንና ምዕራባውያን ይህን መቀበል አቅቶአቸው ለዘመናት ብዙ ግፍ ፈጽመዋል ። በክርስትና ስምም በሠሩት ግፍ ለብዙዎች መዳን እንቅፋት ሆነዋል ። አፍሪካንም በመቀራመትና አፍሪካውያን በገዛ ሀብታቸው የበዪ ተመልካች የሆኑት በዚህ ዘረኛ አስተሳሰብ ነው ። እግዚአብሔር ግን እንደ አንድ ስለቆጠረን አንድ ፀሐይን ለቀን ፣ አንድ ጨረቃን ለሌሊት አደረገልን ። ወንዝና ውቅያኖሱም የምንዝናናበት እንጂ የድንበር መስመር አድርገን የምንፋጅበት አልነበረም ። ከእግዚአብሔር አሳብ ስንስት ይህ ተከሰተ ። ጌታችን የመልክአ ምድር ግርዶሽን አፈረሰ ። ዛሬ አንዱ ወደ አንዱ ቦታ ሲሄድ ባይተዋርነት እንዳይሰማው ምድር የእግዚአብሔር መሆኗን ገለጠ ። ሌላው ወደ እኛ ሲመጣ እንዳናገልለው እንግዳን ተቀበሉ በሚለው ቃሉ አስጠነቀቀን ። ከዚህ ሁሉ በላይ ይህች ዓለም የሁላችንም የእንግድነት ቤት ናት ። በሰማይ ከምናሳልፈው ዕድሜ አንጻር የዚህ ዓለም ቆይታችን የእንግድነት ዕድሜ ነው ። አንድ እንግዳ ወደ ቤታችሁ መጥቶ በትንሹ አንድና ሁለት ሰዓት ይቆያል ። በእግዚአብሔር ዘንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ነው ። ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ከሆነ 500 ዓመት እንደ 12 ሰዓት ነው ። 250 ዓመት ደግሞ እንደ 6 ሰዓት ነው ። 125 ዓመት ደግሞ እንደ 3 ሰዓት ነው ። 62 ዓመት ደግሞ 1 ሰዓት ተኩል ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ሰባ ዓመት ብንኖር 2 ሰዓት እንኳ አይሞላም ። በጣም አጭር ዘመን ነው። ሁላችንም እንግዶች ነን ። የተሰፈረልን ዘመን እንኳን ለጠብ ለፍቅርም አይበቃም ። እኛ ግን ስንቱን እንሆንበታለን ?
የመልክአ ምድሩን ግንብ ያፈረሰው በቤተ መቅደስም ነው ። በቤተ መቅደሱ የአይሁድ አደባባይና የአሕዛብ አደባባይ ተብሎ በትልቅ ግንብ ተከፍሎ ነበር ። ከአሕዛብነት ወደ ይሁዲ እምነት የመጡ እንኳ በሁለተኛ ዜግነት ይቆሙ ነበር ። ያ ግንብም የመለያየት ግንብ ነው ። ጌታችን ይህን ግንብ በደሙ አፈረሰው ። ሐዋርያው ይህን አስታውሶ አሕዛብ ለነበሩት የኤፌሶን አማንያን ፡- “እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው”  በማለት የግንቡ መፍረስ በተዋህዶውና በደሙ መሆኑን ይገልጻል ። በተዋህዶው ከሕዝብና ከአሕዛብ በመወለዱ ነው ። “በሥጋው ያፈረሰ” ያለው ይህን ነው ። ቤተ ክርስቲያንም አንድ አካል ናት ስንል ከሕዝብና ከአሕዛብ የተውጣጣች ማለት ነው ። በዚህ ምክንያት ሁላችን በክርስቶስ አንድ ሆነናል ። “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” /ገላ. 3፥28/። በምድር ላይ የተለያየ ቀለም ይታያል ። እግዚአብሔር ይህን ህብረ መልክ ስለወደደው ነው። ጥቁሮች ፣ ነጮች ፣ ቀዮችና ብርቱካናማ ቀለም ያላቸው የሰው ዘሮች አሉ ። የሁላችንም ደም ግን አንድ ያው ቀይ ነው ። እግዚአብሔር ሊያየው የፈለገውንና የሠራውን ቀለም እኛ ለመለያየት መጠቀማችን ተገቢ አይደለም። በሰማርያ ሊያልፍ ግድ የሆነበት ይህን እስከ መቅደሱ የደረሰውን የመልክአ ምድር ግንብ ለማፍረስ ነው ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ