የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ደብረ እግዚአብሔር

“ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል ፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና” /ዮሐ. 4፥23/ ።
ጌታችን ስግደትን እውነተኛ የሚያደርገው ደብረ ገሪዛን ነው ወይስ ኢየሩሳሌም ? ለሚለው ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ስግደትን እውነተኛ የሚያደርገው ከመልክአ ምድር ይልቅ የልብ ዝንባሌ መሆኑን ገለጠ ። እግዚአብሔር የሚሻው ይህንን ነው ። ደብረ ገሪዛን ለመውጣት ኢየሩሳሌም ለመውረድ የሚያስፈልገው ጉልበትና ገንዘብ ነው ። እግዚአብሔርን ለማምለክ ግን የሚያስፈልገው ሃይማኖት ነው ። ጌታችን ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ እንደሚመጣ አሁንም እንደሆነ አበሰረ ። ከደብተራ ኦሪት ወደ ሰሎሞን መቅደስ ፣ ከሰሎሞን መቅደስ ወደ ምኩራብ ሲሸጋገር የኖረው የአምልኮ ማዕከል አሁን ደግሞ በሰማያዊት መቅደስ በእምነት በመገኘት የሚቀጥል መሆኑን ተናገረ ። በአባወራ ይፈጸም የነበረው አምልኮ ወደ ሌዋውያን ካህናት አደገ ። በሌዋውያን ካህናት ይፈጸም የነበረው አገልግሎት በአዲስ ኪዳን አማንያን ተተካ ። በፈቃድ ይደረግ የነበረው አምልኮ የሕግ ከለላ አገኘ ። በሕግ ከለላ ይደረግ የነበረው አምልኮ በእውቀትና በእምነት እንዲሁም በዳነ ማንነት የሚከናወን ሆነ ።
ሊቀ ካህናት አሮን ሟች ነበረ ። የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለም ሕያው ነው /ዕብ. 7፥24/ ። በእንስሳት መሥዋዕት ይፈጸም የነበረው የቆየው አምልኮ አሁን ግን ሕያውና ቅዱስ የሆነውን ሰውነታችን በማቅረብ ደግሞም በምስጋናና በምጽዋት የሚተካ አምልኮ ሆነ /ሮሜ. 12፥1፤ዕብ. 13፥15-16/ ።
ጌታችን ፡- “አብ እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና” በማለት ተናገረ ። እግዚአብሔርን እንደምንፈልገው ማምለክ አንችልም ። እርሱ በሰጠን የአምልኮ መስፈርት ልናመልከው ግድ ነው ። አምልኮ ማለት መገዛት ማለት ነው ። ስለዚህ ከምናቀርበው አገልግሎት ጀምሮ ለእግዚአብሔር መገዛት ፣ እርሱ እንደሚፈልገው ማምለክ ይገባል ። ለዚህም የብሉይ ኪዳን መሥዋዕት ፣ መቅደስና አገልጋዮች ሁሉም በእግዚአብሔር ልዩ ትእዛዝ የሚቀርቡ ነበሩ። አምልኮ ሦስት ነገሮች በዋናነት ይፈልጋል ። እነርሱም፡-
1-  መሥዋዕት
2-  ካህን
3-  መቅደስ ናቸው ።
መሥዋዕቱ ማምለኪያው ወይም እጅ መንሻ ፣ ካህኑ አሳራጊው ፣ መቅደሱ ደግሞ መሠዊያው ነው ። እነዚህ በሁለቱም ኪዳናት ጽኑ ናቸው ። የብሉይ ኪዳን አምልኮ የሚፈጸምባቸው ሦስቱ ነገሮች ግዙፍና ውስን ናቸው ። መሥዋዕቱ የእንስሳት ነበር ። ካህናቱም አሮናውያን ነበሩ ። መቅደሱም በኢየሩሳሌም የነበረው የአምልኮ ማዕከል ነው ። እግዚአብሔር ግን ይህንን ግዙፍና ውስን መሥዋዕት በመንፈሳዊ ሊለውጠው ፈለገ ። መንፈሳዊ ማለት ሕያውነትና ጥልቅነት ደግሞም እውነተኛነት ያለው ነው ፣ መሥዋዕት ወርውሮ የሚኬድበት ሳይሆን ራስን መሥዋዕት ማድረግ ያለበት ነው ። እግዚአብሔር ይህንን የፈለገው እርሱ ባሕርዩ መንፈስ ስለሆነ ነው ። በመቀጠል ጌታችን እንዲህ አለ ፡-
“እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል” /ዮሐ. 4፥24/ ። አንድ ሕዝብን ያማከለ ብሉይ ኪዳን ፣ ኢየሩሳሌምን ማዕከል ያደረገ የጥንቱ አምልኮ አሁን ጽንፍ የለሽ ሁኖ በመላው ዓለም እንደሚዘረጋ የሚገልጥ ነው ። በየስፍራው ሁሉ የእግዚአብሔር ስም እንደሚጠራ ፣ ምድረ እስራኤል የተወሰነው የአንዱ አምላክ አምልኮ በዳርቻዎች ሁሉ እንደሚገንን የሚገልጥ ነው ። በዚህ ምዕራፍ ላይ ጌታችን ሳምራዊቷን ሴት “ውኃ አጠጪኝ” በማለት ጥማቱ የእርስዋ መዳን እንደነበር አይተናል ። አሁን ደግሞ የእግዚአብሔር አብን መሻት እየነገረን ነው ። እግዚአብሔር አብ እንደፈለጋቸው የሚያመልኩ ብዙዎችን አይቷል ። አሁን በደብረ ገሪዛንና በኢየሩሳሌም ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ስሙን የሚጠሩትን ናፍቋል ። ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ነውና ።
ከእግዚአብሔር የባሕርይ መገለጫዎች አንዱ መንፈስ የሚል ነው ። እግዚአብሔር መንፈስ ነው ። መንፈስ የሚለው ቃል እንደ አገባቡ ትርጉሙ እየሰፋ የሚሄድ ነው ። ለሰው መንፈስ የሚለው ቃል ሲጠቀስ ነፍሱን ወይም በሥጋው ውስጥ ያደረችውን ለባዊት ነባቢትና ሕያዊት ተፈጥሮውን ይገልጣል /ሉቃ. 1፥47፤ 1ተሰ. 5፥23/ ። ለመላእክት መንፈስ የሚለው ቃል ይነገራል /መዝ. 103፥4/ ። ተፈጥሮአቸውን ያስረዳል ። ረቂቃን ማለት ነው ። ለእግዚአብሔር መንፈስ የሚለው ቃል ሲነገር ግን በጊዜና በቦታ የማይወሰን ማለት ነው /ዮሐ. 4፥24 ፤ መዝ. 138፥7-12/ ። ምሉዕ በኩለሄ ነው ለማለት እግዚአብሔር መንፈስ ነው የሚለው ቃል ይውላል ።
እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ በጊዜና በቦታ የማይወሰን ስለሆነ በጊዜና በቦታ የማይወሰን አምልኮ እንደፈለገ ያሳያል ። ይህ ቃል ከተነገረበት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ድረስ በመላው ዓለም የእግዚአብሔር ስም በቀንና በሌሊት በምስጋና ይጠራል ። ይልቁንም እግዚአብሔርን ለማምለክ ነጻ መውጣት ያስፈልጋል ። ለዚህ ነው ስለ አምልኮ የሚናገረው የአስርቱ ትእዛዛት የመጀመሪያው አንቀጽ ፡- “ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ ። ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ” የሚለው /ዘጸ. 20፥2-3/ ። ከአምልኮ ትእዛዝ ጋር ከግብፅ ምድር ነጻ መውጣታቸው ተገልጿል ። ጌታችንም፡- “እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን” ብሏል /ዮሐ. 4፥22/ ። አምልኮት ወይም ስግደት ከመዳን ጋር የተያያዘ ነው ። የምናመልከው የመዳናችንን ራስ ፣ የነጻነታችን ጌታ የሆነውን እግዚአብሔር ነው ።
በመንፈስና በእውነት ማለት ምን ማለት ነው ? በመንፈስ ሲል ባለመወሰን በዳርቻዎች ሁሉ ማምለክ ማለት ነው ። በእውነት ሲል ደግሞ ከልብ እንዲሁም በተግባር ማለት ነው ። በመንፈስ መስገድ ሲባል እኛ ስፍራችንን እንለቃለን ወይም ሥጋችንን አውልቀን እንሄዳለን ማለት ሳይሆን የእግዚአብሔርን የማይወሰን ባሕርይ እያሰብን እንሰግዳለን ማለት ነው ።በውስጣዊ ዓይኖቻችን እርሱን እያየን የሰማይ ማደሪያውን በእምነት እየጎበኘን እንሰግዳለን ማለት ነው ። መንፈስ የሚለውን ቃል በመጠቀም ሁሉም ነገር የማይታይ መሆን አለበት ወደሚል አስተሳሰብ ልንገባ አይገባም ። ክፍሉ የሚናገረው በደብረ ገሪዛንና በኢየሩሳሌም የተወሰነው አምልኮ በመላው ዓለም ወይም በመንፈስ እንደሚሰፋ የሚናገር ነው ። ይህን ቃል በመጥቀስ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አያስፈልግም ማለት አይገባም ። ምክንያቱም መሰብሰብ ካለ መሰብሰቢያ በግድ ይኖራል ። ከርደተ መንፈስ ቅዱስ በኋላ ጴጥሮስና ዮሐንስ በ9 ሰዓት ለጸሎት ወደ ቤተ መቅደስ የመሄድ ልማድ ነበራቸው /የሐዋ. 3፥1/። የጸሎት ሰዓቶችን መቊረጥ ፣ የመገናኛ ቤተ ጸሎቶችን መጠቀም ፣ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚመሩ ቀሳውስትን መፈለግ ተገቢ እንጂ ከቃሉ ጋር የሚጋጭ አይደለም ። ይህን ቃል በመጥቀስ የሚታዩ ምሥጢራትን ማቃለል አይገባም ። ምክንያቱም ጥምቀትም ቊርባንም በጌታችን የታዘዙና የተሠሩ ናቸው ። ጥቅሱን ስንለጥጠው ስህተት ውስጥ እንዳይከተን በተነገረበት መንፈስና በዐውዱ መረዳት የተሻለ ነው ። ሁሉን ነገር በመንፈስ ማድረግ አንችልም ። ምክንያቱም ያለነው በሥጋም ነው ። ሥጋም የተፈጠረና የዳነ ነውና ሊሰግድ ይገባዋል /1ቆሮ. 6፥19-20/ ። ሥጋችን አስፈላጊ ባይሆን ጌታ አይለብሰውም ነበር ። ደግሞም በደሙ አይዋጀውም ነበር ። ዝማሬአችን ረቂቅ ነው ። ነገር ግን ረቂቁ ቃል ከግዙፉ ምላስ ጋር ካልተዋሐደ ዝማሬ ወይም ዜማ ሊኖር አይችልም ። ሥጋ አስፈላጊ ባይሆን ኑሮ ትንሣኤ ሙታን አይኖርም ነበር ። ትንሣኤ ሙታን የሥጋም ክብር ነው። ሐዋርያው ፡- “ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው” ይላል /ፊልጵ.2፥10-11/ ። ጉልበትም መላስም ሁለቱም ሥጋ ናቸው ። ነፍስም አብራ ተዋሕዳ አክብሮቷን ታቀርባለች ። ዳግመኛም ፡- “እንግዲህ ወንዶች በስፍራ ሁሉ አለ ቍጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሱ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ” ይላል /1ጢሞ. 2፥8/ ። እጆችን ወደ ላይ መዘርጋት ለተማረከው ልባችን መግለጫ እንዲሆን አሳሰበ እንጂ እጆችን መዘርጋት አያስፈልግም አላለም ። “የጅል ዘፈን አንድ ነው” እንዲሉ ጅል ልቅሶ ቤትም ሰርግ ቤትም የሚያዜመው እርስዋን ነው ። እንዲሁም በአንድ ጥቅስ ነገረ መለኮትን መመሥረት በጣም የሚጎዳ ነው ። ነገረ መለኮትን ለመመሥረት ብሉያትና ሐዲሳትን ሊቃውንትና የዓለም አቀፍ ጉባዔያት ውሳኔዎች ማየት ይጠይቃል።በትችት ሁሉንም ማስጣል አይገባም ። አንድን ጥቅስ ለመረዳት አባቶች ፡- “ከላይ አርእስቱን ከሥር ኅዳጉን ተመልከቱ” የሚሉት ከብዙ ስህተት የሚጠብቅ መሆኑን እያየነው ነው ። ሙሉ ምዕራፉን አንብቡ ማለት ነው ።
     ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በተረጎሙት ደቂቀ እስጢፋኖስ በሚለው መጽሐፍ ላይ እንዲህ ይነበባል ፡-
“ከዚያ ደግሞ እነዚያን መነኵሲቶች አገረ ገዥውና በምንኵስና ስም በሚጠሩ ንቡራነ እዶች በነበሩበት አደባባይ ሁሉ ፊት አቆሟቸው ። የንጉሡ መልእክተኛ ከነሱ አንዷን ትልቋን ንግሥት ማርያም የምትባለውን እኅት ፥ “ሃይማኖትሽ ምንድነው ? “ብሎ ጠየቃት ። ቅድስቷ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተጎላምሳ የዚህ ዓለም ባለሥልጣኖችን ግልምጫ ሳትፈራ፥ በጣዖት አምልኪ ንጉሦች ዘመን ሰማዕት እንደሆኑት የቀድሞ ሴቶች፥ “ስለ ሃይማኖቴ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን አመልካለሁ” አለችው ። ደግሞ “መምህርሽ ማነው ?” ብሎ ጠየቃት ። ቅድስቷ፥ “መምህሬ ክርስቶስ ነው” አለችው ። “የምንኵስና ልብስ ያለበሰሽ ማነው ?” አላት ። ቅድስቷ “የእግዚአብሔር ካህን አለበሰኝ” አለችው ። “ደብሩ የት ነው?” አላት ። ቅድስቷ፥ “ደብሩ ደብረ እግዚአብሔር ነው” አለችው ።
የንጉሡ መልክተኛ ሲሰማ በጣም አደነቀና አብረውት ያሉትን፥ “ይቺ ሴት ደብረ እግዚአብሔር የምትለው ወዴት ነው ?” ብሎ ጠየቃቸው ። እነሱም “ደብረ እግዚአብሔር መላው ምድር ነው” አሉት ። እዚያ የነበሩ በችሎታ ያደረገችውን ያፏን መልስና የነገሯን ሁሉ አስተዋይነት ሲሰሙ አደነቁ ። ምክንያቱም የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በሷ ላይ አድሮ ይናገር ነበር ።” /ደቂቀ እስጢፋኖስ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ 1996 ዓ.ም. ሚኒሶታ ገጽ 127 ።
አዎ  ደብረ እግዚአብሔር መላው ምድር ነው ። ጌታችንም በመንፈስና በእውነት እንድንሰግድ ተናገረ ። ቅዱሳንም ያ በመንፈስ የተባለው ደብረ እግዚአብሔር መሆኑን አመኑ ።
በዐፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት ለብዙ እልቂት ምክንያት የሆነው ካቶሊካዊ አልፎንዙ ሜንዴዝ ንጉሡ ከሞቱና ሃይማኖት ከተመለሰ በኋላ ክርክር እንዲካሄድ ኦርቶዶክሳውያን አባቶቻችን ጠየቁ ። ክርክሩም ሲደረግ አልፎንዙ ሜንዴዝ ከጠየቀው ጥያቄዎች አንዱ ፡-
“የእግዚአብሔር ፊቱ ወዴት ነው” የሚል ነው ። መልሱን የሰጡት የተዋሕዶው ሊቅ እጨጌ በትረ ጊዮርጊስ መብራት አስበርተው በጉባዔው መካከል አደረጉና ፡-
“የዚህ መብራት ፊቱ ወዴት ነው ? ብለው ጠየቁት ።
እርሱ ግን መልስ አልሰጣቸውም ። እርሳቸውም ፡-
“የዚህ መብራት ፊት በዚህ በኩል ብቻ ነው እንደማይባል የእግዚአብሔርም ፊት በዓለም ሁሉ ምሉዕ ነው” አሉት ይባላል ። /የኢት/ኦር/ተዋሕዶ ቤ/ክ ታሪክ አቡነ ጎርጎርዮስ1974 ዓ.ም ገጽ 61/ ።
ጌታችን በመንፈስ ስለ መስገድ የተናገረው ምሉዕ በኩለሄ የሆነውን ባሕርዩን ተገንዝቦ በዳርቻዎች ሁሉ ምስጋናና ክብርን ለእግዚአብሔር ስለ ማቅረብ ነው ። የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ማዕከል ኢየሩሳሌም ስለነበረች እስራኤላውያን ቢያንስ በዓመት ሦስት ጊዜ ካሉበት አገር መጥተው መስገድ ነበረባቸው ። በኢየሩሳሌም ያለው መቅደስ በመፍረሱም እስከ ዛሬ መሥዋዕት ማቅረብ አይችሉም ። ስፍራው ላይ ሁነው እንኳ የኦሪቱን ሥርዓታቸውን በሙሉነት መፈጸም አይችሉም ። ኢየሩሳሌም ለመገኘት ባልቻሉበት በስደትና በእስር ዘመን ወደ ኢየሩሳሌም አቅጫጫ ዞረው አምልኮታቸውን ይፈጽሙ ነበር /ዳን. 6፥10/ ። ወደ ይሁዲ እምነት የገቡም ለመስገድ ኢየሩሳሌም መገኘት እንደ ነበረባቸው ከኢትዮጵያዊ ጃንደረባ እንረዳለን /የሐዋ. 8፥27/ ። በጣም አድካሚ ነበር ። ዛሬ ቢሆን ብላችሁ አስቡት ። ገንዘቡና ጉልበቱን ትታችሁ የእስራኤልን ቪዛ ማግኘት ጭንቅ ይሆን ነበር ። ታዲያ ለምን በብሉይ ኪዳን ይህ ታዘዘ ? ስንል ኪዳኑ የተሰጠው ለአንድ ሕዝብ ነበርና ያ ሕዝብም በኢየሩሳሌም ውስጥና ዙሪያ ስለነበር ቀላል ትእዛዝ ሆኖለታል ። በአዲስ ኪዳን ግን ለእግዚአብሔር ባሕርይ የሚስማማ አምልኮት እናቀርባለን ። በሁሉ ቦታ ስሙን እንቀድሳለን ። አሮናውያን ካህናትንም አንፈልግም ። ከተለያየ ነገድና ወገን ካህናትን አድርጓል ። ከሰማይ ሠራዊት ጋር እንዲህ እያልን እናመስግነው ፡-
“መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፥ ታርደሃልና፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፥ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።” /ራእ. 5፥9-10/።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ