የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሁሉን ይነግረናል

“ሴቲቱ፡- ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው ። ኢየሱስ፦ የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት” /ዮሐ. 4፥25/ ።
በዕብራይስጥ ፣ በአራማይክ ፣ በዐረቢኛ መሢሕ ሲባል በግሪክ ደግሞ ክርስቶስ ይባላል ። ትርጉሙ የተቀባ ወይም የከበረ ማለት ነው ። ይህን ስያሜ ያገኙ የነበሩ እስራኤልን በዙሪያቸው ካሉ ጠላቶች የሚታደጉ ነጻ አውጪዎች ሲሆኑ በቅዱስ ዘይት የከበሩ ነቢያት ፣ ነገሥታትና ካህናትም እንደ መሢሓውያን ይታዩ ነበር ። እስራኤል ሁሉ ይጠብቁት የነበረው አንድ መሢሕ ግን አለ ። እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ነገር ግን በተስፋ የናፈቁትን ፣ በትንቢት ያከበሩትን ፣ በሱባዔ ያሰሱትን ክርስቶስ በመጣ ጊዜ አልተቀበሉትም ። ምክንያቱ ምንድነው ? ስንል ይጠብቁት የነበረው ከምድራውያን ጠላቶቻችን ተዋግቶ ነጻ ያወጣናል ። ዙፋኑንም በኢየሩሳሌም አጽንቶ ያከብረናል ብለው ነው ። እንደ ጠበቁት ስላልተገለጠ ሊቀበሉት አልቻሉም ። ክርስቶስ ምድራዊ መንግሥትን ይይዛል የሚል አሳብ በደቀ መዛሙርቱ ልብ እስከ ዕርገቱ ቀን ድረስ ነበረ /የሐዋ. 1፥6/ ። በመካከላቸውም የነበረው ክርክር በዚያች መንግሥት ከፍተኛው ሹመት ለማን ይሰጣል ? የሚል ነበረ ። ይህንን ምኞታቸውን ያምኑትና እርስ በርሳቸው ይጣላሉ ። ጌታችን ኅብስት አበርክቶ ሺህዎችን በመገበ ጊዜም ሊያነግሡት ፈልገው ነበረ /ዮሐ. 6፥15/ ። ሆሳዕና በአርያም እያሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ያጀቡት ከፊት ለፊቱ መስቀል እንዳለበት አልተገነዘቡም ። በዚህ ምክንያት ሊቀበሉት አልተቻላቸውም ።
ሐዋርያት በስብከታቸው ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ይናገሩ ነበር /የሐዋ. 5፥42/ ። ሌላ አትጠብቁ ነጻ አውጪው መጥቷል ማለታቸው ነው ። አይሁድ ኢየሱስ መባሉን ተቀብለዋል ። ክርስቶስ መባሉን ግን አልተቀበሉም ። ክርስቶስ መዐርግንና ትንቢት ፈጻሚነትን የሚያመለክት ስም እንደሆነ ያውቃሉ ። ሐዋርያት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያጠምቁ እንደ ነበር ተጽፏል /የሐዋ. 10፥48/ ። የጥምቀት ትእዛዙ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው /ማቴ. 28፥20/ ። እነርሱ ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያጠምቁ የነበረው አይሁድ አንዱን አምላክ በአርያም ያለውን አብን መቀበል አልቸገራቸውም ። ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ማመን ግን ከብዷቸው ነበር ። ጥምቀትም በክርስቶስ ካላመኑ ጥቅም የለውም ። ምክንያቱም ከእርሱ ሞትና ትንሣኤ ጋር መተባበር ነውና ። ስለዚህ በክርስቶስ ማመናቸውን ለማስረገጥ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያጠምቁ ነበር ። አንዳንድ ጊዜም አጥማቂው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሲል ተጠማቂው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እያለ ይጠመቃል ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነጻ ሊያወጣን ነው ። ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነጻ ሊያወጣ የከጀለ ብርቱ ማንም አልነበረም ። ሁሉ በኃጢአትና በሞት ተይዞ ነበርና ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከኃጢአት ሊያድነን መጣ ። በምድር ላይ ያሉ ጠበብቶች ቢሰባሰቡ ኃጢአትን ማከም አይችሉም ። የኃጢአትንም ዋጋ መክፈል አይቻላቸውም ። ጌታችን ግን ከኃጢአታችን ያዳነን መሢሕ ነው ። የኃጢአትን አስከፊነት ስናውቅ የእርሱ አዳኝነት ምን እንደሆነ ይገባናል ። እግዚአብሔር የኃጢአትን አስከፊነት የገለጠው መስቀል ላይ ነው ። አንድ ልጁ ለሞት ተላልፎ መሰጠቱ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው የፍቅር መግለጫ ነው ። ይህ ብቻም አይደለም ለኃጢአት ያለው የመረረ ጥላቻም ነው ። በየትኛውም ዘመን ኃጢአተኞችና እግዚአብሔር ይታረቃሉ ። ኃጢአትና እግዚአብሔር ግን አይታረቁም ። ጥንትም አሁንም ወደፊትም ኃጢአት ኃጢአት ነው ። ሐዋርያው ፡- “ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም?” ይላል /ሮሜ. 8፥32/ ። እግዚአብሔር በልጁ ጨክኖ ለእኛ ራራ ። ልጁን ለሞት አሳልፎ መስጠቱ ግን በኃጢአት ላይ ያለውን ጽኑ አቋም ሊገልጥልን ነው ። ቀራንዮ የፍቅር ትርጉም ብቻ ሳይሆን የኃጢአት ትርጉም ምን እንደሆነ የምናውቅበት ነው ። ኃጢአት በጥንት ዘመን ሕግን ማፍረስ ነው ። አሁን ግን ክርስቶስን ለሞት ካበቃው ምክንያት ጋር መተባበር ነው ። ወዳጁ በተገደለበት ዕቃ ሥራ የሚሠራና የሚደሰት ማነው ? ክርስቶስ ለሞት በበቃበት ኃጢአት ኑሮን ማደላደል ደግሞም ደስታን መፈለግ አይገባም ።
ጌታችን እስራኤል እንደ ተመኙት ከሮማውያን ነጻ አውጥቶአቸው ነፍሳቸውን ግን ትቶ ቢሆንስ ? የዓለም መድኃኒት አይሆንም ነበር ። ቤዛ ኩሉ ዓለም በመሆኑ ቅኝ ገዢዎቹንም ተገዢዎቹንም ነጻ አወጣ ። በኃጢአት ባርነት ያልተያዘ የለምና ። የመግዛትና የመገዛዛትን አስተሳሰብ የሚወልደው የነፍስ ነጻ አለመውጣት ነው ። የበላይነት መንፈስ ምንጩ የበታችነት መንፈስ ነውና ። ሰው የበታችነት ሲሰማው የበላይ መሆንና ሌሎችን መግዛት ይፈልጋል። ጌታችን የቅኝ ግዛትን ሥሩን ሊቆርጥ መጣ ። ነጻ የወጣች ነፍስ ስግብግብነት ፣ ጨቋኝነት የለባትም ። በዓለም ላይ ታላላቅ ጭካኔዎችን ፈጽመው የሄዱ ሰዎች ውስጣቸው የነበረው ይህ ነጻ አለመውጣት ነው ። ጌታችን ከነፍስ ባርነት ነጻ ሊያወጣን መጣ ።
ነፍስ የጽድቅና የኰነኔ መነሻ ናት ። ሥጋ ግን ጉዳይ አስፈጻሚ ነው ። ለዚህ ነው በአዲስ ኪዳን ስለ ምኞት ስለ ቊጣ በአጠቃላይ ከውስጥ ስለሚወጡ ነገሮች የተነገረው /ማቴ. 15፥19 ፤ 5፥21 እና 28/ ። ረቂቅ ምኞት ግዙፍ ዝሙትን ፣ ረቂቅ ቊጣ ግዙፍ መግደልን ያመጣል ። ነፍስ ከሥጋ ስትለይ ቅጣቱንም ዕረፍቱንም ከሥጋ ቀድማ የምትቀበለው ዋነኛ ወሳኝ ስለሆነች ነው። በትንሣኤ ሙታን ግን ሥጋም ተባብሯልና አብሮ ሊከብር ወይም ሊቀጣ ይነሣል ። ነፍስ ትልቅ አቅም ያላት ናት ። ፍቅሯ እንኳ ኃይለኛ ነው። በነፍስ ኃይል መውደድ የሚገባን እግዚአብሔርን ነው /ማር. 12፥30/ ። ምክንያቱም ይህን ፍቅር መሸከም የሚችል እርሱ ብቻ ነው ። ሰዎችን እንደ ራሳችን መውደድ ይገባናል ። ሰዎችን በነፍስ ኃይል ስንወዳቸው እስረኛና መከረኛ እናደርጋቸዋለን ። እኛም ተንቀሳቃሽ ሬሣ እንሆናለን ። ልጆቻቸውን በጣም በመውደዳቸው ከትምህርት ቤት እስኪወጡ ትምህርት ቤት ደጃፍ ላይ የሚውሉ ወላጆች አሉ ። የትዳር አጋራቸውን በጣም በመውደዳቸው ቢሞትብኝስ እያሉ ለአእምሮ ጭንቀት የሚዳረጉ አሉ ። በነፍስ ኃይል መውደድ ሁልጊዜ የሚገኘውን እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ደግሞም ይገባዋል ።
ሳምራዊቷ ሴት የንስሐውን ጥሪ ለማስቀየስ ባቀረበችው የሃይማኖት ክርክር የአዲስ ኪዳን አምልኮ ተብራራ ። እግዚአብሔር ድንቅ ነው ። ለኒቆዲሞስ ስለ ዳግመኛ መወለድ ለዚህች ሴት ስለ አምልኮ ምልአት ነገራት። መሆን የነበረበት አምልኮ ለኒቆዲሞስ ፣ ዳግም ልደት ለሳምራዊቷ ሴት ቢነገር ነበር ። እግዚአብሔር ግን እውቀቱ ከሰው የተለየ ነው ። ኒቆዲሞስ ዘመደ እግዚአብሔር ለመሆን ከባዶ መጀመር አለበት ። ብዙ ነገር እንዳለው ያስባልና ። ይህች ሴት ምንም የላትምና ጌታችን በማራቆት አይሰብካትም ። አለሽ እያለ ተስፋ ይሰጣታል ። ለማን ምን እንደሚነገር የሚያውቀው የፈጠረን እርሱ ነው ።
መሢሑ እንደሚመጣ የተፋፋመ ወሬ ነበረ ። ይህ ወሬ በኢየሩሳሌም ብቻ ሳይሆን በሰማርያ ፣ በቤተ መቅደስ ብቻ ሳይሆን በመሸታ ቤት ይወራ ነበር ። ይህች ሴት መሢሑን የምትጠብቀው ለንግሥና አይመስልም ። እርስዋና ወዳጆቿ ከኃጢአት ነጻ ያወጣናል ብለው ይጠብቁት ነበር ። መሢሑ የመገለጥ ወይም የአስተርእዮ ፍጻሜ መሆኑን ተናገረች ። “ሴቲቱ፡- ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው ።” በእውነትም በመጀመሪያው ምጽአቱ ላይ ሁኖ የዳግም መምጣቱን ነገር ነግሮናል ። እርሱ ሁሉን ነግሮናልና አዋቂ ፍለጋ መንከራተት የለብንም። ሐዋርያው ፡- “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” ያለውን ሳምራዊቷ ሴት ቀድማ ተናገረች /ዕብ. 1፥1-2/ ። እግዚአብሔር በሕልም በራእይ በትንቢት ሳይሆን በአንድ ልጁ ከተናገረን ይህ የመገለጥ ዳርቻ ነው።
እስከ ክርስቶስ መምጣት ድረስ የተሰወሩ መንፈሳዊ ምሥጢራት በክርስቶስ መምጣት ተገልጠዋል ። የሥላሴ ምሥጢር ፣ ዳግም ልደት ፣ መንፈሳዊ አምልኮ በእርሱ ተብራርተዋል ። ፍጹም ትምህርት ፍጹሙን መምህር ሲጠብቅ ኑሯል ። የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ምሥጢረ ሥጋዌ ነው ። የምሥጢረ ሥጋዌ መሠረትም ምሥጢረ ሥላሴ ነው ። ምሥጢረ ሥላሴ በክርስቶስ ተገለጠ ። ሁሉን የነገረን ጌታችን ስሙ የተመሰገነ ይሁን ። የሁሉ መሠረት ስለሆነው ሥላሴነት የነገረን በሁሉ የተመሰገነው እርሱ መሢሑ ነው ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ