የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የእግዚአብሔር ልጅ ድምፅ

“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ” /ዮሐ. 5፡25/፡፡
ጌታችን አሁንም አጽንዖት እየሰጠ ነው ፡፡ ሰዎች እውነተኛ ሕልም ከሆነ ይደገማል ይላሉ ፡፡ መድገም ማጽናት ነውና ፡፡ ከእግዚአብሔር የሆኑ መልእክቶች አጽንኦት አላቸው ፡፡ አንዱን መልእክት በተለያየ ድምፅ እንሰማዋለን ፡፡ የሰማነው ወይም የተሰማን መልካም አሳብና መንገድ ከእግዚአብሔር መሆኑን ለማረጋገጥ ቢያንስ አራት ነገሮች አስፈላጊ ናቸው፡-
1-  እንደ ቃሉ መሆኑን ማረጋገጥ
2-  በጉዳዩ ላይ መጸለይ
3-  መንፈሳውያን አባቶችን ማማከር
4-  የልብን ሰላም ማዳመጥ ወሳኝ ናቸው ፡፡
ከእግዚአብሔር የሆኑ ጥሪዎች ግን አጽንኦት አላቸው ፡፡ ሥራን ለቅቆ ሙሉ ጊዜን ለእግዚአብሔር ለመስጠት ፣ ጋብቻን ትቶ በምንኩስና ለመኖር ፣ አገርን ለቆ ሌላ አገር ለመሄድ… ድምፅ ሲመጣልን ቢደጋገም የተሻለ ነው ፡፡ ሰው የሚሰማው ውስጡ የሚያስበውን ነው ፡፡ ውስጣችን የሚያስበውን ነገር ሰምተን እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል ፡፡ ግጥምጥሞሽን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መውሰድ ፣ ከክፉና ከደጉ ዕጣ አውጥቶ መለየት እነዚህ አደገኛ መንገዶች ሊሆኑ ይችላሉ ፡፡ ከእግዚአብሔር ሆነ ድምፅ ግን ይደጋገማል ፡፡ እንዲሁም ቃለ እግዚአብሔርን በትንቢት አንቀጽ ብቻ መተርጎም አደጋ አለው ፡፡ ለምሳሌ ፡- “መንገድህን ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ” የሚለውን ጥቅስ ስንሰማ “በዚህ ዓመት አገር እለቃለሁ ፣ እግዚአብሔር ተናግሮኛል” ማለት አደጋ አለው ፡፡ አንድ የሰማሁትን ላሰማችሁ ፡፡ የአንድ ፈላስፋ ንግግር ፡- “ዛሬ ማታ እንደሚሞት ሁነህ ተዘጋጅ ፣ ዘላለም እንደሚኖር ሁነህ ሥራህን ሥራ” የሚለውን ንግግር አንዲት እህት ወደ ውጭ እሄዳለሁ ግን እስከዚያው ሥራ እሠራለሁ ብላ ተረጎመችው ፡፡ የመጀመሪያ ንግግሩ የአንድ ፈላስፋ ነው ፡፡ ሁለተኛው የፈላስፋውንም ንግግር በቅጡ አልሰማችውም ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ እግዚአብሔር በሚገባን መንገድ እንጂ በአዙሪት አይናገርም ፡፡ ዘወር
ጌታ አጽንኦት የሚያደርገው ከእርሱ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው ፡፡  በድምፅ የተሞላ ዓለም ነውና ከብዙ ድምፆች መሐል የእግዚአብሔርን ድምፅ መለየት ያስፈልጋል ፡፡ የእግዚአብሔርን ድምፅ ለመለየት የተጻፈው ቃሉ ፣ ጸሎትና ጊዜ መስጠት ወሳኝ ነው ፡፡ ጌታችን እውነት እውነት እላችኋለሁ አለ፡፡
በመቀጠል ፡- “ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል” አለ ፡፡ ጌታችን ሙታን ያለው ሙታነ ኅሊና የሆኑትን ፣ ልባቸውን ለፍቅር ፣ ጆሮአቸውን ለቃሉ የቆጠቡትን ነው ፡፡ የሚሰሙት ድምፅም የእግዚአብሔር ልጅን ድምፅ ነው ፡፡ ብዙ ድምፆች አሉ ፡፡ ሁሉም ድምፆች ግን ሕይወት አይሰጡም ፡፡ ሕይወት የሚሰጠው ድምፅ የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ድምፅ ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የእምነት ማዋለጃ ነው፡ ሐዋርያው ፡- “እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው” ይላል /ሮሜ. 10፡17/፡፡ የምንሰማው ሁሉ እምነትን አያስገኝም ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን እምነትን ያስገኛል ፡፡ ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ የሚለው ቃል የምንሰማው ወደ ጥርጣሬ ማዕበል ስለሚጥልም ነው ፡፡ የእምነት መሠረቱ ልማድ ወይም አፈ ታሪክ ወይም ውርስ አይደለም ፡፡ የክርስትና ሃይማኖት ባለ መጽሐፍ ነው ፡፡ አመክንዮአዊ በመሆኑ ለመነጋገርም ለመቀባበልም ለትውልድም የሚሆን ሃይማኖት ነው ፡፡
የተዘናጋ ሰው መስማት አይችልም ፡፡ የተኛ ሰው ደግሞ ይበልጥ አይሰማም ፡፡ ኅሊናቸው በኃጢአት ብዛት ፣ መንፈሳቸው በክህደት የሞተባቸው ደግሞ ይበልጥ አይሰሙም ፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ድምፅ ግን ሙታን ይሰሙታል ፡፡ እንደ ዘኬዎስ ላሉ ትንሣኤ ልቡና የሚሰጠው ድምፅ እንደ አልዓዛር ላሉ ደግሞ ትንሣኤ ሙታንን የሚሰጥ ድምፅ ነው ፡፡ በዓለም ላይ ድምፅ ከፍተኛ ኃይል ያለው ነገር ነው ፡፡ ድምፅ ያድናል ፣ ድምፅ ይገድላል ፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ድምፅ ግን ሕይወት ይሰጣል ፡፡
የሞት ትክክለኛ ትርጉም መጥፋት ሳይሆን መለየት ማለት ነው ፡፡ አንድ ሰው ለአንድ ነገር ሲኖር ለአንድ ነገር ሙቷል ማለት ነው ፡፡ ለዓለም ሲኖር ለእግዚአብሔር ይሞታል ፣ ለእግዚአብሔር ሲኖርም ለዓለም ይሞታል፡ ትልቁ ሞትም ከእግዚአብሔር መለየት ነው ፡፡ አዳም ሞተ የተባለው በሥጋ የሞተ ቀን ወይም ወደ ሲኦልም በወረደ ቀን አይደለም ፡፡ አዳም ሞተ የተባለው ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ኅብረት ባጣ ቀን ነው ፡፡ ኅብረትን የጣለው ኅብረትን ጀምሮ ነው ፡፡ ከሰይጣን ጋር የማይፈቀድ ኅብረት ፣ ከሚስቱ ጋር እግዚአብሔርን ገሸሽ ያለ ኅብረት ጀመረ ፡፡ ስለዚህ ሞተ ፡፡ መንፈሱ ከእግዚአብሔር አንድነት ተለየ ፡፡
ኃጢአት ፍጻሜው ሞት ነው ፡፡ “የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ ምን ትሞታላችሁ? የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ” ይላል /ሕዝ. 18፡32/፡፡ መሞት ምርጫ እንጂ ግዴታ አይደለም ፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃዱ የሰዎች መዳን ነው ፡፡ ኃጢአት ሞትን ያመጣል ፡፡ የሞት ጥላ በሆነው በቀቢፀ ተስፋና አልድንም በሚል ስሜት ያኖራል ፡፡ ጌታችን አባቴን ቀብሬ ልምጣ በማለት ወደ ኋላ ሊል ያለውን ደቀ መዝሙር፡- “ተከተለኝ፥ ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው” ብሎታል /ማቴ. 8፡22/፡፡ ሙታነ ሥጋን እንዲቀብሩ ሙታነ ኅሊናን ተዋቸው ማለቱ ነው ፡፡ ስለዚህ ሙታን የሚባሉ ነፍስና ሥጋቸው የተለያየ ብቻ አይደሉም ፡፡ ነፍሳቸው ከእግዚአብሔር አንድነት የተለየችም ሙታን ይባላሉ ፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ፡- “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ” በማለት ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የተመለሱትን የኤፌሶን ሰዎች የምሥራች ይላቸዋል /ኤፌ. 2፡1/፡፡ ክርስቶስን ካላገኙ በቀር ሞትን በነበር ማውራት አይቻልም ፡፡ እርሱ ባለቤቱም፡- “ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ” እንዳለ ሙታን ነበርን ለማለት ያበቃናል /ራእ. 1፡18/፡፡
በጌታችን አገላለጥ ሙታን የተባሉ ለሥጋዊ ጥቅም የሚነቁ ፣ ለመንፈሳዊ ተጋድሎ ግን ያንቀላፉ ናቸው ፡፡ ሙታን የተባሉ ሕይወታቸው ውስጥ የፍቅር እንጥፍጣፊ እንዳይኖር ሁነው ራሳቸውን ባዶ ያደረጉ ናቸው፡፡ ሙታን የተባሉ በሌሎች ማግኘት ወይም መዳን የሚበሳጩ ፣ ያገኘውን ሰው የሚጠሉ ፣ የሰጠውን ጌታ የሚከስሱ ናቸው ፡፡ ስጠን ከማለት ለምን ሰጠህ የሚሉ ፣ ሰዎች እንዳይነሡ መቃብር የሚጠብቁ ናቸው ፡፡ እሳት እሳት ውስጥ አይቃጠልም ፡፡ ሙታንም መቃብር ውስጥ አይበርዳቸውም ፡፡ ካሉበት ዓለም የተሻለ ዓለም ያለ ስለማይመስላቸው ከሞት ጋር ተላምደው ለመኖር ገና እቅድ ያወጣሉ ፡፡ ጌታችን እነዚህን ሊቀሰቅስ መጣ ፡፡ አካሉ የሞተበት መጻጉዕን በተአምራት አስነሣው ፡፡ እርሱ መዳን ይፈልጋል ፡፡ የኅሊናና የመንፈስ ሙታን ግን የሚነሡት በእግዚአብሔር ቃል ነው ፡፡ ያለ ፈቃዳቸውም የነፍስ ትንሣኤን አያዩም ፡፡ ያወቁ ስለሚመስላቸው ነፍሳቸው እንዳትሞት መማር አይፈልጉም ፡፡ የጨረሱ ስለሚመስላቸው መንፈሳቸው እንድትድን ንስሐ አይገቡም ፡፡ ጌታችን ሁሉንም ወደ ሕይወት ጋበዘ ፡፡ ከመጻጉዕ አንጻር ስንተነትን የሕይወት ትርጉም ይገባናል ፡፡ ለዘመናት በአልጋ ላይ እንደ ኖረ ሙታነ ኅሊናም ለዘመናት በድንቁርና ነበሩ ፡፡ ለዘመናት ራስ ወዳዶችን እንዳየ ሙታነ ኅሊናም ለዘመናት ፍቅር የተራቡ ናቸው ፡፡ ጥሩ ኑሮን ትቶ ጥሩ ሞትን እንደ ናፈቀ ሙታነ ኅሊናም ተስፋ የለሽ ናቸው ፡፡ በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘው ሕይወት ግን ብርሃንና ሰላም ያለው ነው ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ