“እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? ” /ዮሐ. 5፥44/።
ጌታችን መጻጕን በመፈወሱ የተነሣው ሙግትና ክርክር እስካሁን አላባራም። በሐሰት ለሚከሱት ጌታችን በእውነት በመመለሱ ለእኛ ብዙ የእውቀት ብርሃን ሰጥቶናል ። በትዕቢት ለሚናገሩት በትሕትና መመለሱ ለእኛ ብዙ ሐቅ ፈንጥቆልናል ። አይሁድ ላይበሉት ያንን በግ እንዳረዱት ፣ ላያርፉበት ብዙ ጥያቄ ጠየቁት ። እግዚአብሔር በሌሎች አፍ እያስጠየቀ ፣ ለልጆቹ ይመልሳል ። የእግዚአብሔርን መልስ የማይቀበሉ ጥያቄአቸውን አዝለው ይኖራሉ ። የጥያቄውን መልስ የማይቀበሉ ቀድሞም ጥያቄው አልገባቸውም ማለት ነው ። ጌታችን ሰዎችን ከእግዚአብሔር ክብር ወደ ኋላ የሚመልሳቸው የሰው ክብር መሆኑን ተናገረ ። የሰው ክብር እንዲህ ብለህ በአደባባይ አወድሰኝና እኔም ላወድስህ የሚል ነው ። ኪሎ ለሰፈረ ኪሎ ሲሰፍሩ መኖር ነው ። የሰው ክብር ረቂቅ እስር ቤት ነው ። የሚያስረው አካልን ብቻ ሳይሆንም ኅሊናንም ነው ። በዚህ ክብር የታሰሩ ራእያቸውን ፣ ጥሪአቸውን የሚቃኙት ሰውን በሚያስደስት መልኩ ነው ። የሰው ክብር አዲስ ነገር እንዳይፈልቅ የተለመደው ነገር እንዲኖር የሚታገል ነው ። የሰው ክብር ካለመዱት መልአክ የለመዱት ሰይጣን ይሻላል የሚል ነው ። ለአሚና ፣ ለአዝማሪ እየከፈሉ ማስገጠም ፣ ባለቅኔዎችን እየጋበዙ ተናገርልኝ ማለት በጣም ምስኪንነት የልጅ ጨዋታም ነው ። “በእብዶች ከተማ ጤነኛው እብድ ነው” እንደሚባለው የሰው ክብር በሚፈልጉት ዘንድ ባለ ራእይ የተዋረደ ነው።
ፈሪሳውያን በዚህ በሰው ክብር የታሰሩ ነበሩ ። እንግዳ ሕዝብ ሲመጣ እንዲያይላቸው የክት ልብሳቸውን ፣ የሃይማኖት ዘርፋቸውን ለብሰው እየጸለዩ መሄድ ፣ እየፎከሩ ስመ እግዚአብሔር መጥራት ያስደስታቸው ነበር ። የእግዚአብሔር ቃል ከልባቸው ተርፎ በቀሚሳቸው ዘርፍ ላይ ተጽፏል እንዲባሉ የሕጉን ተምሳሌት ይዘው ይዞሩ ነበር ። ይህ ግን የቀን ጻድቃን የጨለማ ኃጥአን አደረጋቸው ። ለልብሳቸው እንጂ ለልባቸው እንዳይጨነቁ ያደረጋቸው ይህ የሰው ክብር ነው ። ስለ ሰንበት ተጨንቀው የሰንበትን ጌታ እንዲሰቅሉ ያደረገው ይህ ኃላፊ ሰው ክብር ነው ።የሰው ክብር የእውነትን ሚዛን ያስጥላል ። ከትልቁ የእግዚአብሔር ክብርም ያስቀራል ። ጠዋት የተናገረውን ማታ በማይደግመው በሰው ክብር ከመታሰር በእግዚአብሔር ቤት መጣል ይሻላል ። ነቢዩ፡- “ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ።” ያለው ለዚህ ነው /መዝ. 83፥10/። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ክብርና ከሰው ክብር ምርጫ ማድረግ ይጠይቃል ።
ከዕድሩ ፣ ከዕቁቡ ላለመለየት የሚፈልግ ሰው የእግዚአብሔር ክብር ሊያልፈው ይችላል ። የሰው ክብር ቅዱስ አባታችን እያለ ዞር ብሎ ደግሞ ሳይበቁ ቅዱስ ፣ ሳይወልዱ አባት ይላል ። በዚህ የሰው ክብር የተለከፉ ከስማቸው በፊት ብዙ ነገር እንዲደረደርላቸው ይፈልጋሉ ። ቶሎ ስማቸው ሲጠራ ይበሳጫሉ ። ራሳቸውን ለሸርዳጆችና ለአስብቶ አራጆች አሳልፈው ሰጥተዋል ። የሰው ክብር መፈለግ ሕጻን ያደርጋል ። በትንሹ መፈንደቅ ፣ በትንሹ መከፋት የሰውን ክብር ከመፈለግም የሚመጣ ነው ። በዛሬ ምስጋና ልቡ የነሆለለ የትላንትናዎቹን ባለጊዜዎች አወዳደቅ ያላነበበ ነው ።ዓለም ከፍቅሯ ጋር አርጅታ አታውቅም ። ተረኛ ካገኘች በጨረታው አትገደድም ። ያከበረችው ሰው ከፍ እያለ ሲመጣ ሳናውቀው ነው ያከበርነው ትላለች ። ያዋረደችው የሞተ ቀን ሳናውቅ ነው የጠላነው ትላለች ። ግን መሻሻል አታሳይም አሁንም ለሽንገላዋ ትፋጠናለች ። አዞ ልጁን በልቶ መልሶ እንደሚያለቅስ ዓለምም የአዞ ዕንባ ታፈሳለች ። “እየወጉ ይማርህ” እንደሌለ ዓለም እየወጋች ይማርህ ትላለች ። እየገደለች ልቅሶ ትደርሳለች ። የሰው ክብር የበረሃ አዙሪት ነው ። የመጣንበትን መልሰን እንረግጣለን ። የሚኖሩበትን ከተማ መንገድ የሚያገኙ የእግዚአብሔርን ክብር የሚናፍቁ ብቻ ናቸው ። ዓለም ፍቅሯ የውሸት ፣ ጠቧ የእውነት ነው ።
“ጊዜ የሰጠው ዘፈን እንቅርት ያፈርጣል” እንዲሉ ስንት የተወራላቸው ፣ ለዝንተ ዓለም የማይረሱ የሚመስሉ ይኸው ፍጹም ተዘነጉ ። ከተማውን በሙሉ ያነቃነቁ ዘፈኖች ፣ ድርሰቶች ዛሬ ደግሞ የሚያወራቸው የለም ። ዓለም ላታነሣ ትጥላለች ። ፈሪሳውያን የእግዚአብሔርን ሥራ ለማየት ፣ በሌሎች መዳን ለመደሰት ፣ መሢሑን ለመቀበል የቸገራቸው ይህ የሰው ክብር እንደ ሙጫ አንቆ ይዟቸው ነው ።
አንድ የመርሐ ግብር መሪን ቀጥሎ የሚያስተምረው አስተማሪ እንዲህ እያለ ያስጠነቅቀዋል ። በዚህ ኮሌጅ በነገረ መለኮት ዲፕሎማውን ፣ በዚህ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪውን …አሁን በዚህ ኃላፊነት ላይ ያለ …ብለህ ተናገር እያለ ያስፈራራዋል ። ሰሚዎቹን ግን የሚያድነው በመስቀል ላይ ርቃኑን የተሰቀለው ፣ የሰውን ክብር ንቆ በውርደት ሞት የሞተው ክርስቶስ ነው ። ከያዝነው እንዲነገርልን ለምን እንፈልጋለን ? እንደ ያዝን ስላላረጋገጥን ነው ። አንዳንድ ሰዎች ደህነት ሄዶላቸዋል ። መሄዱን ግን ማመን አልቻሉም ። ትዝታው እያስበረገጋቸው ዛሬም አወድሱኝ ይላሉ ። ዛሬም ሲጣሉ ይኖራሉ። የሰው ክብር እከክልኝ ልከክልህ የሚል ደካማ ባህል ነው ። ሔዋን የሌላት አምላክነት ሲነገራት በደስታ ተቀበለች ። ፍጻሜው ግን ዛሬም ያላባራ ውድቀት ሆነ ። ከሆነው በላይ ሲነገር አይደለም የሆነውን ያህል ሲነገርም ክብርን ለእግዚአብሔር መስጠት ፣ ልብን ከትዕቢት መጠበቅ ይገባል ። ዲያቆኑ “ድምፅህ እንዴት ያምራል” ቢሉት ፡- “ያውም ጉንፋን ይዞኝ ነው” አለ ይባላል ።
ቅኔ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የመገዛትና የአምልኮ መሳሪያ ነው ። የሰው ክብር ግን ቅኔን መወዳደሻ ፣ የሥራ ማመልከቻ ማቅረቢያ አደረገው ። በአምልኮቱ በማይደራደረው በእግዚአብሔር ፊት እንድንበድል አደረገን ። በእውነተኛ ስሜት ስለ ሰዎች ምስክርነት መስጠት ተገቢ ነው ። የምናቀርብበትና የምንቀበልበት ልብ ግን ውዳሴ ከንቱ ያሰኘዋል ። ውዳሴ ከንቱ የልብ ጉዳይ እንጂ የቃል ጉዳይ ብቻ አይደለም ። የእርስ በርስ የክብር ሙቀት የእግዚአብሔርን ክብር እንዳንናፍቅ ያደርጋል ። ለእግዚአብሔርም ክብርን እንዳንሰጥ የአምልኮም ልብ እንዳይኖረን ያደርጋል ። የመድረክ ሰዎች ተከብረው የሚኖሩት ለምንድነው ? ስንል የሚኖሩት ለሰው ደስታ ብቻ ስለሆነ ነው ። ዓለሙ ካልነኩት አይነካም ። ከነኩት አይለቅም ።
በክርስቶስ ለማመን አስፈላጊው ነገር የሰውን ክብር መናቅና የእግዚአብሔርን ክብር መናፈቅ ነው ። የእግዚአብሔር ክብር የማይናፍቀው ሰው ሊያምንና መንግሥቱን ሊወርስ አይችልም ። ማመን ትልቅ ነገር ነው ። በማመን ውስጥ መተማመንና ዕረፍት አለ ። ማመን የነገ ስንቅ ነው ። ካላመንን እንኳን በሰማይ በምድር መኖር እንቸገራለን ። ሰዎች በዚህ ምድር ላይ ክብርን የሚፈልጉት የእግዚአብሔርን ክብር ስላላዩ ነው ። ማር የቀመሰ በስኳር አይገረምም ። በወርቅ ያጌጠም ለነሐስ አይጋደልም ። ዓባይንም ያየ ምንጭ አያመሰግንም ። የእግዚአብሔር ክብር የክብር ራስ ነው ። ነቢዩ፡- “በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ።”ይላል /ኢሳ. 2፥2/።
በአደባባይ እጅ መነሣሣት ፣ እርስዎ ይቅደሙ እርስዎ መባባል ተመልካቹንና ያልተማረውን ሰው ለመማረክ የሚደረግ ጥረት ነው ። ዝቅ ማለት ሁሉ ክብር መስጠት ላይሆን ይችላል ። ሰውዬውን ከሥሩ ነቅሎ ለመጣልም ነው። እውነተኛ ክብር አስቀድሞ ልብ ቀጥሎ አንገት ጎንበስ የሚልበት ነው ። አዎ የእግዚአብሔርን ክብር መናፈቅ እንቢ እያልን ፣ እግዚአብሔር ያከበራቸውን ማክበርም እያንገሸገሸን በተቃራኒው እርስ በርሳችን ክብር እንፈላለጋለን ። የነገዎቹ እንዲያከብሩን የትላንትናዎቹን ማክበር ግድ ይላል ። ያልዘሩትን ማጨድ የለምና ።
ጌታችን በዚህ ክፍል እግዚአብሔር አንድ መሆኑን ተናገረ ። ያ አንዱ እግዚአብሔር በሦስት አካላት በአንድ አምላክነት ያለ መሆኑንም በክፍሉ አስረድቷል ።