የትምህርቱ ርዕስ | ስብከት አምስት

… የተባረከው ሐዋርያ ጳውሎስ የመንፈስ ጸጋ ስለሆነው ስለ ሰማያዊ ሀብትና ይህንን ለማግኘት ስለሚገጥመን ታላቅ መከራ ሲገልጥና ሁላችንም በዚህ ሕይወት ምን ለማግኘት መጣር እንዳለብን ሲናገር እንዲህ አለ “ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና” (2ቆሮ.5፥1) ። ስለዚህ ሁላችንም በሁሉም ዓይነት ጸጋዎች መጣርና መታገል ሰማያዊውንም ቤት እዚህ ማግኘት እንደምንችል ማመን ግድ ይለናል። የሰውነታችን ቤት ከጠፋ ነፍሳችን የምትመለስበት ሌላ ቤት የለንም። “ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም” (2ቆሮ.5፥3) ራቁት ማለት ከመንፈስ ቅዱስ ኅብረትና ስምረት መነጠል ማለት ነው። በዚህ ምክንያት እውነተኛ ክርስቲያኖች የሆኑ ክርስቲያኖች ከሥጋቸው ሲለዩ/ሲሞቱ በደስታ የሰማዩን መንገድ ይጀምራሉ። ምክንያቱም በእጅ ያልተሠራ ቤት ስላላቸው ነው ። ይህም ቤት በእነርሱ የሚያድረው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ነው ። ስለዚህ የሥጋ መኖሪያቸው ቢጠፋም ምንም የሚያስፈራቸው ነገር የለም ። ምክንያቱም የመንፈስ ቅዱስ የሆነው ሰማያዊ ቤትና የማይጠፋው ክብር ስላላቸው ነው ።ይህም ክብር በትንሣኤ ጊዜ ሥጋ ለሆነው ሰውነታችን ሕይወትንና ክብርን የሚሰጥ ነው ። ሐዋርያው እንዲህ አለ፡- ”ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል”(ሮሜ 8፥11)። ዳግመኛምእንዲህ አለ፡- “የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ” (2ኛቆሮ 4፥11)።“በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ” ( 2ኛቆሮ 5፥4) ።
                                                                                                                                                                                         
8. እንግዲህ በእምነትና በመልካም አኗኗራችን እዚሁ ምድር ላይ ሳለን ያንን ልብስ ለማግኘት እንጣር ። በኋለኛው ሕይወትም ከሥጋችን ስንለይ ርቃናችንን እንዳንሆን ሰውነታችንንም የሚያስጌጥ አንዳች ነገር እንዳናጣ እንትጋ ። ሁሉም ሰው በእምነትና ትጋት በእኩልነት የመንፈስ ቅዱስ ተካፋይ እንዲሆን ስለተፈቀደለት በዛ በፍርድ ቀን ሰውነቱም ይከብራል። አሁን ነፍስ በውስጧ ያከማቸችው በዚያንጊዜ በውጫዊው ሰውነታችን ይገለጣል ። ልክ በክረምት ወቅት ውኃ ያገኙ ዛፎች በማይታየው ፀሐይና ነፋስ ሲሞቁ ከውስጣቸው እንደሚያወጡትና የሚያለብሳቸውም ቅጠል እንደሚያብብ ፣በዚህ ወቅትም አበባዎች ከምድር እቅፍ እንደሚወጡ በዚህም ምድር እንደምትሸፈንና እንደምትለብስ ሁል ጊዜ የምናየው እውነት ነው። ይህም የምድር አበባ ጌታ እንዲህ ብሎ የገለፀው ነው፡-“ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም” (ማቴ 6፥29) ።ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ክርስቲያኖች በትንሣኤ ለሚያገኙት ክብር ምሳሌዎች ናቸው ።
                                                                                                                                                                                             
9. ስለዚህ እግዚአብሔርን ለሚወዱ ነፍሳት ሁሉ ፣ለእውነተኛ ክርስቲያኖች መስከረም የተባለ የመጀመሪያ  ወር ይመጣላቸዋል ። ይህ ቀን የትንሣኤ ቀን ነው ። በእውነተኛው ፀሐይ ኃይልም የመንፈስ ቅዱስ ክብር ከውስጥ ይወጣል።በቅዱሳኑ አስቀድሞ የነበረው ነገር ግን በነፍሳቸው ተደብቆ የኖረውን  ክብር  በመግለጥ ሰውነት እያስጌጠና እየሸፈነ ይመጣል ። ሰው አሁን ያለው ነገር በዚያንቀን በውጭ ሰውነት ይገለጣል ። መጽሐፍም ስለዚህ ወር እንዲህ ይላል፡-“ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ” (ዘፀ 12፥2)።ይህም ለሁሉም ፍጥረታት ደስታን ያመጣል ፣ምድርንም በመክፈት የተራቆቱትን ዛፎች ያለብሳል ። ለፍጥረትም ደስታንና ፍንደቃን ያመጣል ። ይህ ለክርስቲያኖች የመጀመሪያው ወር ፣የትንሣኤ ጊዜ ሰውነታቸው አሁን በውስጣቸው ባለው ከቃላት በላይ በሆነው ብርሃን ማለትም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚከብርበትና የሚያጌጥበት ነው ። ይህም ክብር ለእነርሱ የሚበላ ፣የሚጠጣ ፣የደስታ ፣የሐሴት ፣የሰላም ፣የዘላለም ሕይወት ካባና መጎናጸፊያ ይሆናቸዋል ። አሁን በቅምሻ ለመቀበል የታደሉትን ክብር በዚያን ጊዜ በምልአት ሁሉንም የብርሃን ውበቶችና ሰማያዊ ድምቀቶች ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ይቀበላሉ ።
                                                                                                                                                                                          
10. እንዲህ ከሆነ እንዴት ሁላችንም በማመን ፣ በመታገል ፣በመልካም አኗኗር ፣በተስፋና በትዕግሥት ሰማያዊውን ኃይል አሁን ለመቀበል የተገባን እንድንሆን ፣ሥጋችን ሲሞት የምንለብሰውን የመንፈስ ቅዱስን ክብር በነፍሳችን ውስጥ  ለማግኘት አንፈልግም ? እንዲህ ከሆነ፡-“ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም” (2ቆሮ.5:3)።“ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል” (ሮሜ8፥11) የሚለው ቃል ይፈጸምልናል ። ሙሴም ማንም ሰው አትኩሮ ሊያየው በማይችለው ፊቱ ላይ በነበረው የመንፈስ ቅዱስ ክብር ይህንን በምሳሌ አሳይቷል ። በጻድቃን ትንሣኤ ቀን የተገቡ ሁነው የተገኙት የእነዚያሰውነት እንዴት አይከብር ? ነገር ግን ይህ ክብር አሁን በቅዱሳንና በአማኞች በውስጣዊ ሰውነታቸው እንዲኖር የተሰጣቸው ነው። ዘመኑም ሲፈጸም በሙላት ይገለጣል ። መጽሐፉ፡-“እኛ ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት” ሲል በውስጣዊ ሰውነታችን ለማለት ነው ይህን ካለ በኋላ   እንዲህ ይላል፡-“የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን” (2ኛ ቆሮ 3፥18) ። በተመሳሳይ መልኩ ሙሴ በመጽሐፍ እንደ ተጻፈው አርባ ቀንና አርባ ሌሊት እንጀራ ሳይበላ ውኃም ሳይጠጣ በተራራው ላይ ነበር ። ሥጋ መንፈሳዊ ምግብ ካላገኘ በቀር የቅዱሳን ነፍስ በመንፈስ የሚመገበውንየመንፈስ ቅዱስ ስጦታም ካላገኘያለ ምግብ ረጅም ጊዜ መኖር አይችልም ።                                                                                                                                                                                 
11.የሙሴ ሕይወት በሁለት መንገድ ክርስቲያኖች የሚገኙትን ብርሃን ያሳያል ። ይህ ከመንፈስ ቅዱስ የሆነው የብርሃን ክብር ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች አሁን በዚህ ሕይወት ሳሉ የተሰጣቸውን በትንሣኤም ጊዜ በሙላት የሚኖራቸውን ቁሳዊ ያልሆነ መንፈሳዊ ደስታ በዚያንጊዜ በሰውነታቸው ሁሉ እንደሚገለጥ ያሳያል ። አስቀድመን እንዳልነው ቅዱሳን አሁን በነፍሳቸው ያላቸው ክብር እርቃነ ሰውነታቸውን ይሸፍናል ። ወደ መንግሥተ ሰማያትም ያስገባቸዋል ። ይህም ከሆነ በኋላ ሥጋና ነፍሳችን በመንግሥተ ሰማያት ከጌታ ጋር ያርፋሉ ። እግዚአብሔር አዳምን ሲፈጥረው እንደ ወፎች ያለ ክንፍ አላበጀለትም ። ነገር ግን በትንሣኤ የሚሰጥ የመንፈስ ቅዱስ ክንፍ አዘጋጅቶለታል ። ይህም ክንፍ መንፈስ ቅዱስ እንደ ወደደ ከፍ እንዲያደርገውና እንዲይዘው ያደርጋል ። የቅዱሳን ነፍሶች ይህ ጸጋ እንዲኖራቸው የተገቡ ሲሆኑ በሰማያዊው የአሳብ መቃን ውስጥ ገብተው እንዲከንፉ ያደርጋቸዋል ። ክርስቲያኖች የራሳቸው የሆነ ሌላ ዓለም ፣ሌላ የማዕድ ጠረጴዛ ፣ሌላ ልብስ ፣ሌላ የደስታ ዓይነት ፣ሌላ ኅብረት ፣ሌላ የአስተሳሰብ መንገድ አላቸው ። በዚህም ምክንያት ከዓለማውያን ሰዎች ይበልጣሉ ። የእነዚህንም ነገሮች ኃይል በመንፈስ ቅዱስ አሁን በነፍሳቸው አለ ። ስለዚህ በትንሣኤ ሰውነታችው ዘላለማዊ ከሆነው የመንፈስ ቅዱስ በረከት ይካፈላል ።በምድርም ሳሉ ነፍሳቸው በቅምሻ ካየችው ከዚህ በረከት ጋር ይዋሐዳሉ ።                                                                                                                                                                                           
12. ስለዚህ ሁላችንም መታገል ፣መከራን መቀበል ፣ለተሰጡን ጸጋዎችም መጠንቀቅ ፣ማመን ፣ጌታም መንፈሳዊ ሕይወታችንንአሁንና እዚህ ምድር ላይ የክብሩ ተካፋይ እንዲሆን ያደርገው ዘንድ ፣ ነፍሳችንም ከመንፈስ ቅዱስ ቅድስና ጋር ኅብረት እንዲኖራት እርሱን መማጸን አለብን ። በዚህም ከክፉ ርኩሰታችን እንድንነጻ ፣ በትንሣኤም ሰውነታችን ርቃኑን ሲነሣየምንሸፍንበት ሀብት እንዲኖረን በዘላለማዊው መንግሥት መልካምነትን በማጎናጸፍ ፣እንድናነቃቃውና እንድናድሰው ያስችለናል ። በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ እንደ ተጻፈው ክርስቶስ ከሰማይ ወርዶ ከመጀመሪያው ጀምሮ ያንቀላፉትን የአዳም ዘሮች ሁሉ ያስነሣና የተነሡትንም ለሁለት ይከፍላቸዋል ። የእርሱ ምልክት ማለትም የመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ያላቸው የራሱ ስለሆኑ ወደ እርሱ ይጠራቸውና በቀኙ ያስምጣቸዋል ። ጌታ እንዲህ አለ ፡- ”በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል“ (ዮሐ 10፥14፤17) ። የእነርሱም ሰውነት ከመልካም ሥራቸው የተነሣበመለኮታዊ ክብር ይደምቃል ። በመንፈስ ቅዱስም ክብር ይሞላል ። ጌታን በአየር ለመቀበል ወደ ሰማይ ይነጠቃሉ ። እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ ፡- ፍጻሜ በሌለው ዘላለም ከጌታ ጋር  ሁነን እየተደሰትን እንኖራለን አሜን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ