እግዚአብሔር ፍጥረታትን ለክብሩ ፈጥሮአል ። ሥራውን እያየ ሠሪውን የማያመሰግን የለም ። ፍጥረታት የእግዚአብሔር መመስገኛዎች ናቸው ። ፍጥረታት አስተማሪዎች ናቸው ። በዚህ ዓለም ላይ ከተደሰተ የተጨነቀው ሰው ብዙ ነው ። ሰው ችግሩን መፍታት ካልቻለ ባይጨነቅ ፣ ከቻለ ጉልበቱን ሳያባክን መፍትሔ ቢፈልግ መልካም ነበር ። የሰማይ ወፎች እንዴት ይሆንልኛል ለሚለው ሰውና እንቅስቃሴ ሳያደርግ በምኞት ብቻ ቀኑን ለሚገፋ ወገን ትልቅ ትምህርት ናቸው ። አይዘሩም አያጭዱም ግን ምግባቸውን ለማግኘት ይበራሉ ። ፍጥረታት ለኑሮና ለሕይወት ብቻ ሳይሆን ለዘመናዊ ግኝቶቻችንም ትምህርት ናቸው ። በሰማይ የሚበረው አውሮፕላን ቅርጹና የበረራ ስልቱ ከወፎች የተወሰደ ነው ። ፍጥረታት ለዘመናዊው ግኝት ትምህርት ቤት ናቸው ። እየተገለጠ ያለ ምሥጢር እንጂ አዲስ ነገር በምድር ላይ የለም ። ሠርክ አዲስ እኛ የምናመልከው ክርስቶስ ብቻ ነው ።
ወፎች አመስጋኞች ናቸው ። ጨለማው ሳያልፍ ምስጋና ይጀምራሉ ። ምስጋና ድል አለውና ወዲያው ሌሊቱ ይነጋል ። በጭንቀት ውስጥ ስናልፍ መዘመር መልካም ነው ። ምክንያቱም ጭንቀት ችግሩ ትልቅ ሁኖ ሲታየን የሚመጣ ስሜት ሲሆን ዝማሬ ደግሞ እግዚአብሔር ትልቅ ሁኖ እንዲታየን የሚያደርግ ነው ። ጭንቀት ችግርን ማተለቅ ፣ ዝማሬ እግዚአብሔርን ከፍ ማድረግ ነው ። ዝማሬ ፣ ድምፅን ከፍ አድርጎ በግልና በኅብረት መዘመር በጣም አስፈላጊ ነው ። ልባችን በድርብ ሲመታ ፣ አቅላችን ሊከዳን ሲዳዳ ፣ ሁሉም ነገር ጨለማ ሁኖ ሲታየን ፣ ጉልበታችን ሲዝል ፣ ብቻዬን ነኝ የሚለው ስሜት ሲነቀንቀን ዝማሬ መጀመር መልካም ነው ። ድምፅ በድምፅ ይሻራል ። ድባቴ ከባድ ብርድ ልብስ ነው ። እየሞቀና እየተጫነ ከመኝታችን ላይ ሊያስቀረን የሚፈልግ ነው ። ዝማሬ ስንጀምር የድባቴው ጭነት ብን ብሎ ይጠፋል ። ምስጋና መጀመር ያለብን ሲነጋ ሳይሆን ጽኑ ጨለማ ሳለ ነው ። ለችግራችን የእግዚአብሔርን ታላቅነት መንገር አለብን ። ሕፃን ልጅ እንኳ “ቆይ ለአባቴ እነግርልሃለሁ” እያለ የጎዳውንና ያስለቀሰውን ያስፈራራል ። እኛም የምንነግረው አባት አለን ።
ሊነጋ ሲል ይጨልማል ። ሊነጋ ሲል ያለው የጨለማው ጥልቀት ከሌሊቱና ከረጅሙ ጽልመት የበለጠ ነው ። ችግር ተሰናብቶ ሊሄድ ሲል ብዙ ጭንቀት ይመጣል ። በግራና በቀኝ የፈተና ብዛት ያማታናል ። ማረፊያ እንዳጣች ወፍ ያቅበዘብዘናል ። የምናየው በር ሁሉ ዝግ ሁኖ ይታየናል ። የሚፈርድብን ብዙ ይሆናል ፣ የቅርባችን ሰዎች ሩቅ ቆመው ይተኩሱብናል ። ዘመዶቻችን ስሜት እንዳለን እንኳ ረስተው ከባድ ፍላጻዎች ያቆስሉናል ። እውነተኛ ጠላት ስናተርፍ ሐሰተኛ ወዳጅ እናመርታለን ። ወዳጁ የውሸት ፣ ጠላቱ ግን የእውነት ይሆናል ። ያቀፈን ሁሉ ሲገፈትረን ይሉኝታ እንኳ የለውም ። መደናገርና የት ልውደቅ የሚል ግራ መጋባት ያስጨንቀናል ። ግን ንጋቱ ደርሷልና መዘመር ፣ በትዕግሥት መጠበቅ ይገባል ። ደግሞም ድል ያለው በመጋፈጥ ብቻ አይደለም ፣ ዘወር ማለትም አንዱ የድል ስልት ነው ።
ወፎች በድቅድቁ ጨለማ ይዘምራሉ ። በምስጋና እርስ በርስ ይተባበራሉ ፣ ይጠራራሉ ። እግዚአብሔርን አመስግኑልኝ የሚሉ ባለ ስእለቶች አሉ ። እኔ ብቻዬን ምስጋናውን መዝለቅ አልችልምና አግዙኝ እያሉ ነው ። የነገር ደቦ በሚጠራበት ዓለም ላይ የምስጋና ደቦ የሚጠሩ ሰዎች የተባረኩ ናቸው ። አመስግኑልኝ ብለው ሲጣሩ ለእኔም ተስፋ አለኝ ብሎ የቆዘመው ሰው ይጽናናል ። በምስጋና ማፈር አይገባም ። እንደ ዳዊት ከዘመርን እንደ ሜልኮል የሚያሽሟጥጡ አይጠፉም ። ምስጋና ግን ጎንን ሳይሆን ሰማይን እያዩ የሚቀርብ መባ ነው ።
ወፎች ድምፃቸው ያማረ ነው ። የተኛውን ሰው ለምስጋና ይቀሰቅሳል ። ከወፎች ይልቅ የተደረገለት ሰው ሊያመሰግን ይገባዋል ። ወፎች መልካቸው ያማረ ነው ። አንድ ቦታ ግን ብዙ ደቂቃ አይቆዩም ። ሲያደንቁአቸው ይሰወራሉ ። ሰውም ያማረ ነገር ካለው የአድናቆት ሱሰኛ መሆን የለበትም ። የሚያደንቀው ሲያጣም የራሱን መልክአ እገሌ እየደረሰ ማዜም የለበትም ። ቤተ ክርስቲያን አንድን ሰው ቅዱስ ብላ ለመሰየም ሃምሳ ዓመት ትጠብቃለች ። ሰውን ቅዱስ ለማለት መቸኮል ርኵስ ለማለትም መቸኮልን ያመጣል ። በራሳችንም ብዙ ከመደነቅ እስከ ሃምሳ ዓመት መጠበቅ አስፈላጊ ነው ። ትክክለኛውና ኃያሉ የዕድሜ ዘመን የሚጀምረው ከሃምሳ ዓመት በኋላ ነው ።
ብቻ ከኃይለኛ ዝናብ በኋላ ፀጥታ ይሆናል ። እንደ መሸ ፣ እንደ ዶፈ አይቀርም ። ከጨለማ በኋላ አስደናቂና የማትጠገብ የንጋት ፀሐይ ትመጣለች ። ከዝናብ በኋላም ያለው አየር ልብን የሚያሳሳ ነው ። ከማዕበል ቀጥሎም ማዕበል አይመጣም ፣ ያስጨነቀን ዘመን አልፎ የዕረፍት ዘመን ይመጣል ። ከጦርነት በኋላም ጦርነት አይሆንም ፣ መጨባበጥና መታረቅ ይመጣል ። ረግረጉ ከሌለ ሩዝ አይበቅልም ፣ ክፉ ከመሰለው ነገርም መልካም ነገር ይወጣል ። ቀኑ ላይ ሲደረስ አቅርቦቱ ይመጣል ። ከደመናው በላይ ፀሐይ አለች ። ሁሉ በር ዝግ አይሆንም ፣ የአንዱ በር መዘጋት የሌላው በር መከፈት ምልክት ነው ። የሳሎኑን በር ስትዘጉ የመኝታ ቤቱን በር እየከፈታችሁ ነው !
ዘምሩ !!!
ይቀጥላል
ኅዳር 15 ቀን 2019 ዓ.ም.