መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የታይታ ጥማት » የታይታ ጥማት -5

የትምህርቱ ርዕስ | የታይታ ጥማት -5

ጌታችን ምጽዋታችንን በስውር እንድናደርግ ያስጠነቀቀን ለራሳችን ጥቅም ነው ። ታይታ ካለው ክብሩ ይቀንሳል ፣ ተቀባዩንም ያሳቅቃል ። ያን ድሀ ሆዱን ሞልቶ ሕሊናውን ማራቆት ይሆናል ። እግዚአብሔርም፡- “ትልቅ ዋጋ ከፋይ እኔ ሳለሁ እንዴት ከፍጡር ዋጋ ይጠብቃል ?” ብሎ ያዝንብናል ። አዋቂዎችም ይታዘቡናል ። ዘመዶቻችን አልጠግብ ባይ ከሆኑ ለእኛ መስጠት ይገባ ነበር ብለው ይቀየሙናል ፣ የሰጠናቸው ወዳጆችም ለእኔ አሳነሰብኝ ብለው ጥርሳቸውን ይነክሱብናል ። ሌቦችም አለው ፣ እንዝረፈው ብለው ይመጣሉ ። የቸገረው ሰው የሚያየው ችግሩን ብቻ እንጂ የእኛን ሁኔታ አይደለምና የጎደለበት ሁሉ ወደ እኛ ይገሰግሳል ፣ መስጠት ብንችልም ለሁሉም ችግረኛ መስጠት አንችልም ። ደግሞም አገሩ ቸርን አጥቂ ነው ፣ ብዙ ስስታሞች ያጠቃናቸው ቸሮች ናቸው ፣ ብዙ ቢስ የሆኑ በጭካኔ የነጠቅናቸው ደጎች ናቸው ። “ቸር ሲያጠቁት ቢስ ይሆናል እንዲሉ ። የሚያበሉንን እስቲ እናንተ ብሉ ለማለት አልታደልንም ። ደጉን በቁሙ ጨርሰን በሞቱ ለመውረስ ገና እናቅዳለን ። ይህ መልካሞች ፣ ሰጪዎችና ትሑታን የተጨነቁበት ዘመን ነው ። ክፉዎች ስለበዙ መልካሞች ተገፉ ። ነጥቆ ሯጭ ስለበዛ ሰጪዎች አዘኑ ። አክባሪን የሚያዋርድ ትውልድ ስለመጣ ትሑታን እንዴት ብንሆን ጥሩ ነው  ብለው ግራ ተጋቡ ።

ጌታችን ስጦታችንን በስውር እንድናደርግ ያስጠነቀቀን ለእኛ ጥቅም ነው ። ሰዎች ማወቅ የሌለባቸው ሁለት ጥብቅ ነገሮች አሉ ። የመጀመሪያው የገቢያችንን ምንጭ ማወቅ አያስፈልጋቸውም ። ሁለተኛ ከመንፈሳዊ አባት ጋር ብቻ ልንነጋገር የሚገባውን ንስሐችንን ማወቅ የለባቸውም ። የታይታ ግብዣዎች ትችትን እንጂ ምስጋናን አያመጡምና መድከም ተገቢ አይደለም ። ለእኛ ጮማ ከሚቆርጥ ድሀ እናቱን አይረዳም ነበር ወይ ? ብለው ሰዎች እየበሉ ያሙናል ። ስጦታን በሚመለከት ሦስት ዓይነት ሰዎች አሉ ። እንደ እግዚአብሔር ደብቀው የሚሰጡ ፣ ጨርሰው የማይሰጡና ለታይታ የሚሰጡ ናቸው ። ከሁሉም ሳንሆን የምንቀረው በታይታ ስጦታ ነው ።

በዚህ ዘመን ታይታ የበዛው ለምንድነው ? ትልልቅ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሳይቀሩ እውነተኛውን ችግር ከመቅረፍ ጉድጓዱ ላይ አበባ ምንጣፍ ማንጠፍን ፈልገዋል ። የብቻ ኑሮ ስለ በዛ ፣ ጓደኝነትም እየፈረሰ ስለ መጣ ሰዎች የማያውቁት ሰውን ማውራትና በማያውቁት ሰው መደነቅን ፈልገዋል ። የውድድር ኑሮ በዝቷል ። የምንወዳደረው ግን በሥራ ሳይሆን በጌጥና በመኪና ነው ። ሥልጣኔ የሚባለው ነገር ልብስና ተንቀሳቃሽ ስልክ መግዛት መስሎን ተዋርደናል ። ማኅበራዊ ሚዲያም ለታይታ ኑሮ አሳልፎ ሰጥቶናል ። እውነተኛውን ኑሮ ስለማይነግሩን ሰዎች አሳስተውናል ፣ እኛም ታናናሾቻችንን እያሳሳትን ነው ። ቦሌ ላይ እንዲሁ ሲጓዝ የሚውል ወጣት የተታለለ ወጣት ነው ። ተበድሮ መማር ሲገባው ተበድሮ ሰው ያጫውታል ። የዝና ጥማት በጣም በዝቷል ። ጥቂት ዝነኞች የሰውን ምግብና ልብስ እየመረጡለት ነው ። ሰው የሌላውን ኑሮ እየኖረ የራሱን ሰርዟል ። ውጫዊነት ወይም ፈሪሳዊነት የተለሰነ መቃብር አስመስሎናል ። ሰው ለቅንነቱ ሳይሆን ለፊቱ እየተጨነቀ ነው ። በዚህም እውነተኛውን ሰው ከውስጣችን ከስረነዋል ፤ ለራሳችንም ታማኝ አይደለንም ። የመረሳት ስቃይ ስላለብን በክብርም በውርደትም ርእስ መሆን እንፈልጋለን ። እንደ አበደ ውሻ ያገኘነውን ፣ አንዳንዴም ያሳደጉንን እንነክሳለን ። ታይታ ፈጣን ዋጋን ፍለጋ ነው ። የበሰለው ዋጋ ከእግዚአብሔር የሚገኝ ነው ።

የቻይናው ዉ ዮንግኒንግ ገና የ26 ዓመት ወጣት ነበር ። ከአንድ ሚሊየን በላይ የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ነበሩት ። አድናቆትን ለማግኘት በዚያውም የተዘጋጀ የገንዘብ ሽልማትን ለማፈስ ከ62 ፎቅ ላይ ያለ ምንም የደኅንነት መከላከያ ትርኢት ሲፈጽም ወድቆ ሞቷል ። ዝና ፍለጋ ብዙ ወጣቶችን በማለዳው ሠርክ እንዲሆንባቸው አድርጓል ። ላይክና ሼር ከሞት አይመልስም ። ሕይወት የረጅም ርቀት ሩጫ ናት ። በአንድ ትንፋሽ ልንጨልጣት አይገባም ። አንተ ወጣት “ፈሪ የእናቱ ልጅ ነው” ተብሏልና ለእናትህ ትረፍላት ! ብዙ ወጣቶችን ቀብሬአለሁ ። የአንዳንዶቹ እርምጃቸው እንደሚሰነብት አልነበረም ፣ ከሞኝ ትዕቢተኛ ብልጥ ተንኮለኛ ዕድሜ እንዳገኘ አያለሁ ። ሰው በቀኑ ይሞታል ፣ ያለ ቀኑም ተቀስፎ ይሞታል ። ዕድሜና ስንቅ እንደ ያዥው ነውና ተጠንቀቅ ።

የታይታ ጥማት ቅጣቱ ግልጽ ነው፡- እዩኝ እዩኝ ያለ ገላ ደብቁኝ ደብቁኝ ይላል ! የዘፈን ቤት ሳይፈርስ አይቀርም ! የተጨፈረበት ቤት በግድ ይለቀስበታል ! ደስታንም ኀዘንንም በልክ መያዝ ግን ያስከብራል !

አቤቱ ቸር ሰው ወዳጅ ሆይ የታይታ ሳይሆን የውስጥ ሰው አድርገን !

ኅዳር 7 ቀን 2019 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ