ዓርብ ኅዳር 4 ቀን 2019 ዓ.ም በቦሌ መድኃኔ ዓለም ሸገር ሕንፃ አጠገብ በባንክ ጥበቃና በአንድ ወጣት መካከል አለመግባባት ተፈጠረ ። ከዚህ በፊት አይተዋወቁም ፣ ያጣላቸው ጉዳይም ቅጽበታዊ የሆነው የመኪና ማቆም ጉዳይ ነው ፤ ጥበቃው አትችልም ሲል ወጣቱ አቆማለሁ ብሎ አቁሞ ገብቶ ሲመለስ በጥይት እንደ ተመታና ሕይወቱ እንዳለፈ ሰምተናል ። በጣም የሚያሳዝን ዜና ነው ። ማነው ጥፋተኛው የሚለውን ፍርድ እንተወዉና በምንም መንገድ የሰው ሕይወት መጥፋት አይገባውም ብለን መከራከር አለብን ። ይህ ክስተት የገባንበትን ችግር በጉልህ የሚያሳይ ነው ። ካለብን የኑሮ ጫና ፣ የመንፈስ ጭንቀት የተነሣ የምንንቀሳቀሰው ሆደ ባሻ ሆነን ነው ፣ ስለዚህ ለቅጽበት ያገኘነውን ሰውና ለዘላለም ለማናገኘውን ወገን ክፉ ልናደርግበት እንችላለን ።
ያ ጥበቃ የተኮሰው ተንቄአለሁ በሚል ስሜት ነው ። ይህ ስሜት መላውን የአገር ሕዝብ እየገዛ ነው ። እኔ የተናቅሁ ነኝ ፣ የተበደልሁ ነኝ የሚል ብሶትን ጥለው የሄዱት የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞች ናቸው ። ጀግናውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሶተኛ አደረጉት ። አገራችን የሚበዛው አማኝ የሆነበት አገር ነው ። አማኝ እግዚአብሔር በመልኩ ፈጥሮኛል ፣ ክርስቶስ በደሙ ገዝቶኛል ብሎ የሚያምን በመሆኑ እናቃለሁ የሚል ስሜት ሊኖረው አይችልም ። ሰው ክቡር ነው ፣ እኔ የእግዚአብሔር አምሳል ነኝ ፣ ዋጋዬ ብርና ወርቅ ሳይሆን የክርስቶስ ደም ነው ብሎ የሚያምን የበታችነት ስሜት ሊኖረው አይችልም ።
ተንቄአለሁ ተበድያሁ የማይል ሕዝብ ማግኘት ከባድ ነው ። ሁላችንም የተበደልን ከሆንን የበደልነው ሁላችንም ነን ማለት ነው ። አንድ የጦር መሣሪያ የሚይዝ ባለሙያ ትዕግሥተኛ ለመሆን መሰልጠን ያስፈልገዋል ። በወታደር እጅ የምድርና የአየር ኃይል አለ ፣ ስልጠና ግን ትዕግሥተኛ ስለሚያደርገው በእጁ ያለውን አቅም ለግል ክብር መጠበቂያ አያደርገውም ። የባንክ ቤት አወቃቀር እንኳን ደምበኛውን ገንዘብህንም አላስነካም የሚል ነው ። በባንክ ደጃፍ ላይ የሚቆም የጥበቃ ጓድም የደምበኛውን ገንዘብ ጠባቂ ነው ። ታዲያ ገንዘብን በሚጠብቅ ተቋም ፊት ሰውዬው ሲገደል ፣ ብሩ ጥበቃ አግኝቶ ባለ ገንዘቡ ሲሞት ይህ አሳፋሪ ክስተት ነው ። መኪና ያቆመው ግለሰብ ቢያጠፋ እንኳ እርሱን የሚያዝዘውና የሚቀጣው የትራፊክ ፖሊስ ነው ። በአካባቢው ላይ ደግሞ በቅርብ ርቀት አለ ። ይህን ወጣት መግደል የሕግ የበላይነትና የሥልጣን ተዋረድ እየጠፋ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ። ከሁሉ በላይ የሰው ሕይወት በጣም እየረከሰ መጥቶአል ። የዓርቡን ሞት በቅዳሜ ሌላ ሞት ረስተነዋል ። የሞት ዜና ዓይናችንን ከድነን እስክንገልጥ ድረስ እጅግ በዝቷል ።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች “ንቆት ነው የገደለው” እያሉ ሲናገሩ ሰምተናል ። እነዚህ ሰዎች ለናቃቸው ሰው የመደቡት ቅጣት ሞት ከሆነ ብዙ ገዳዮችን ተሸክመናል ማለት ነው ። ጥፋተኛን ተበዳይ የመጠየቅና የመቅጣት ሥልጣን የለውም ። ይህን የሚመለከት አካል መኖሩን መቀበልና ሕጋዊ መንገዶችን መከተል ይገባል ። ቀጣዩ ስጋታችን ሁሉም ሰው ራሱን እንደ ፖሊስ ሊያስብ ፣ የበደለውንም የሚቀጣበት የግል እስር ቤት ሊያቋቁም ይችላል ። ይህን የሚወልደው የሕግ መላላት ነው ። ሁሉም እርስ በርስ የሚቀጣጣበት አገርን ከፈጠርን የመፍረስ አደጋ ውስጥ እንገባለን ። ከተማው ላይ ያለውና አብሮ እየኖረ የሚመስለው ግን አብሮ የማይኖረው ወገን እየበዛ ነው ። ስለዚህም የተለያየንባቸው የአሳብ መስመሮች ፣ መጥቻለሁ የሚለው የቆየውን የሚመለከትበት ዓይን ፣ ተወላጅ ነኝ የሚለው ደግሞ መጣ የሚለውን የሚቀበልበት ልብ እንደገና መመርመር አለበት ።
ያ የ27 ዓመት ወጣት ከሦስት ደቂቃ በፊት ፎቁ ላይ ወጥቶ ያናገራቸው ሰዎች ወደ ታች ቁልቁል ሲያዩ እርሱ ሞቷል ። ሕይወት ቅጽበት ናት ። መግደልም ቀላል እየሆነ ነው ። የሰውን ንብረቱን ፣ ስሙን ፣ ትዳሩን የመጠበቅ ግዴታ ነበረብን ፣ አሁን ግን ክቡር ሕይወቱን እያጠፋን ነው ። ስለ ኢሉሚናቲ ብዙ እናወራለን ። በእንግሊዝኛው የእናቶቻችን ዛር ማለት ነው ። ኢሉሚናቲ ካለ ያለው የእኛ አገር ውስጥ ነው ፣ ግብሩም የሰው ደም ነው ። የሞቱት ሁለቱም ናቸው ። ያ የጥበቃ ጓድም ሚስቱን ፣ ልጆቹን ትቶ ወደ ወኅኒ ይወርዳል ፣ ለረሀብ ይዳርጋቸዋል ፣ ጸጸትም ወዲያው ይጀምረዋል ። ለቀጣይ ሃያ ዓመታት እስረኛ ይሆናል ። ገዳይም ለካ በቁም ሟች ነው ። የሰማነውም እኛ በሕሊና እየሞትን ነው ።
ሁላችንም በኑሮአችንና በእንቅስቃሴአችን ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ጊዜ ላይ ነን ። ተጠንቅቀንም ይህን ቀን ካለፍነው ዕድለኞች ነን ። መጸለይ ፣ ከክፉ አታጋጥመኝ ብሎ መለመን ይገባል ። ትዕግሥትን በጣም ማዳበር አለብን ። መግባባትም እየቸገረን ስለሆነ ለማስረዳት ልበ ሰፊ መሆን ያስፈልገናል ። አጠገባችን ያሉትን በቂ ትምህርት የሌላቸውንም ማስተማርና ከሰው ጋር የመኖርን ዘዴ መንገር አለብን ። ሁላችንም እኩል ነን ። እኛም አገልጋዮች ስንሰደብ የምንውል ነን ። መናቅና መሰደብ ትልቅ ርእስ አይደለም ። እግዚአብሔር ካከበረን ማንም ሊንቀን አይችልም ። እንደውም ለሚንቁን መጸለይ ሲገባን በመናቃችን ግን ደስታ ሊሞላብን ያስፈልጋል ።
ቃሉ፡- “ሰዎች ስለ ሰው ልጅ ሲጠሉአችሁ ሲለዩአችሁም ሲነቅፉአችሁም ስማችሁንም እንደ ክፉ ሲያወጡ፥ ብፁዓን ናችሁ ።… ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ ፥ ወዮላችሁ ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና” ይላል (ሉቃ. 6 ፡ 22፤26)። የሞተው ይህ ወጣት ያሳዝናል ፣ ይህ ክስተት ግን ሊታሰብበት የሚገባ ነው ።
ገዳይም ሟችም ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሆኑበት ታሪካችን መለወጥ አለበት ። ኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይ ናት ፣ ራስዋን ግን መቀበል አልቻለችም ። እግዚአብሔር አምላካችን የሞቱትን ያሳርፍልን ፣ ያሉትን ያጽናልን !
እሑድ ኅዳር 6 ቀን 2019 ዓ.ም.