ከወፎች ተማሩ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ” ብሎ አዘዘን ። እንኳን ከሰው ይቅርና ከሰማይ ወፎችም መማር ይገባናል ። እውቀት የሚገኝበት ምንጩ ሁሉን ሳይንቁ መስማት ነው ። ከትምህርት ነጻ የሆነ አንድም ፍጡር የለም ። “እንደ እባብ ብልህ ሁኑ” ሲባል እባብ የክፉ ምሳሌ ነው ። ከክፉዎችም ትምህርት እንዳለ የሚያስረዳን ነው ። ከርግብ ብቻ ሳይሆን ከእባብም እንማራለን ። ለእውነቱ ካየነው እንደ ክፉዎች ያስተማረን ማንም የለም ። ደጎች ለሕሊናችንና ለአካላችን ሲጠነቀቁ ብዙ ትምህርት አልሰጡንም ። ይሉኝታ የሌላቸው ክፉዎች ግን ብዙ አስተምረውናል ። ምቀኞች ዕቃ አስገዝተውናል ። ቀናተኞች ጥንቃቄን አስተምረውናል ። ተንኮለኞች የዓለምን መልክ አሳይተውናል ። ገዳዮች ለሕይወታችን ዋጋ እንድንሰጥ አድርገውናል ። ገፊዎች ትልቅ ቦታ አድርሰውናል ። እግራችንን የረገጡ ክንፍ እንድናወጣ አግዘውናል ። ስማችንን ያጠፉ አንሰን እንዳንገኝ ጉብዝናን ሰጥተውናል ። ሰዎች ለመቅበር የወረወሩትን ድንጋይ ቤት መሥሪያ ማድረግ ከቻልን እንደ ክፉዎች ባለ ውለታ አናገኝም ። ደግሞም ስለ እኛ ክፉ የሚናገሩት ስለሚፈሩን ነው ፣ የሚነሣሡብን መዳረሻችን እየታያቸው ነው ። እግዚአብሔር በጠላቶቻችን ፊት ለፊት ዘይት ይቀባናል እንጂ ጠላቶቻችንን ጨርሶአቸው ቅባቱን አያፈስብንም ። በእኛ የሹመት ቀን የጥሪ ግብዣ የሚላከው ለጠላቶቻችን ነው ። እግዚአብሔር ክፉዎች ለጥፋት ያመጡትን እርሱ ለልማት ይለውጠዋል ። ከሁሉም ትምህርት ይገኛል ።
የሰማይ ወፎች እንጂ የምድር ወፎች አይባሉም ። ወደ ምድር የሚወርዱት ምግባቸውን ፍለጋ ብቻ ነው ። ምግባቸውን ካገኙ ወደ መሳፈሪያቸው ይወጣሉ ። እኛም ለእንጀራችን ብንደክም ፣ በምድራዊ ተግባር ብንሰማራም ሰማይ አገራችንን መርሳት የለብንም ። ማረፊያችንም ጸጋ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ማሰብ አለብን ። ወፎች ልጆቻቸውን በዛፍ ላይ ይወልዳሉ ። በምድር ላይ እንቁላላቸውን አይጥሉም ። ልጆቻችንን ስለ ሰማያዊ ነገር ማስተማር አለብን ። ለራሳቸው ጥቅም ይሆናል ፣ እኛም በልጅ የማናዝን ያረፍን ወላጆች እንሆናለን ። እግዚአብሔርም በትውልድ ላይ ይከብራል ። አገራችን በሰማይ መሆኑን ስንነግራቸው ግፍን የሚጸየፉ ፣ ሰውን የሚወዱ ፣ ዘረኝነትን እንደ ቆሻሻ የሚርቁ ይሆናሉ ። ሰማይ ከፍ ያለ ነው ፣ ከፍ ካለ አስተሳሰብ መዋል ያስፈልጋል ። ጽድቅና ኵነኔን በማሰብ ብቻ ሳይሆን “እኔ እንዴት ይህን ርካሽ ነገር እፈጽማለሁ” ማለት ያስፈልጋል ። ጽድቅን መምረጥ ራስን ማክበር ነው ። ደግሞም ለምድራዊ ኑሮም ሰላምን የሚሰጥ ነው ። ለጤና ከሚያስፈልጉ ነገሮች የመጀመሪያው ጽድቅ ነው ።
ወፎች ሲበሩ በመስቀል ቅርጽ ነው ። መስቀሉ ትልቅ ስጦታችን ነው ። መስቀሉ የክርስቶስ ሕማምና ሞት ነው ። መስቀል ዓላማችን ነው ። በመስቀሉ ውስጥ ትልቅ ፍቅር አለ ። የምንኖረው ለፍቅር ነው ። በመስቀሉ ውስጥ ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር ሰላም መፍጠር እንዳለብን እንማራለን ። ሥራችንን ሁሉ መሥራት ያለብን የመስቀሉን ዓላማ ባከበረ መንገድ ነው ። መስቀል በአንገቱ አድርጎ የሰውን ገንዘብ የሚቀማ ፣ የድሀን ላብ የሚበላ ፣ የሚከፍለውን አሠሪ የሚሰርቅ በእውነት ክርስቲያን አይደለም ። መስቀሉን የሚቃረን ሕይወት ይዘን የመስቀሉን ምልክት መያዝ ተገቢ አይደለም ። በአንድ ክርስቲያን ልግመኛነት ፣ ራስ ወዳድነትና ገንዘብ አፍቃሪነት ሁሉም ክርስቲያን ይወቀሳል ። ለሰዎች መዳን እንቅፋት እንዳንሆን መስቀሉን መኖር ይገባናል ። መስቀሉን በአንገታችን ስናደርግ አንገቴን ለሃይማኖቴ እሰጣለሁ እያልን ነው ። አንገቴ ይቆረጥ እንጂ ግፍን አልፈጽምም ፣ የማይገባኝን ዋጋ አልወስድም እያልን መሆን አለበት።
ወፎች ሌሎችን የሚቀሰቅሱት በዝማሬ ነው ። ደስ በሚል ድምፅ የተኙትን ይቀሰቅሳሉ ። ቀኑ ደስ የሚል ነው ተነሡ ይላሉ ። በማለዳ ተነሥታችሁ አመስግኑ በማለት ይጣራሉ ። ወንጌል የምሥራች ነው ። ሰዎችን የምሥራች ስንል “ምሥር ብላ” ይላሉ ። የምሥራቹን ወንጌል ስንናገር ሰዎች በደስታ እስኪቀበሉ ድረስ ጣዕም ያለን መሆን አለብን ። ከእኔ ይውጣ ለማለት ወንጌል አይሰበክም ። ሌሎችን ለማሸማቀቅና ለመክሰስ ወንጌል አይሰበክም ። ወንጌልን የብሽሽቅ ርእስ ካደረግነው በወንጌል አላመንም ማለት ነው ። ወንጌል የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ፣ ዕርገትና ምጽአት ነው ። ሌሎችን ከእንቅልፍ ስናነቃ ፣ ከስህተት ስንመልስ ለራሳቸው ያላቸውን ዋጋ እንዳያጡ አድርገን በትሕትና መሆን አለበት ። “ካነጋገር ይፈረዳል ፣ ካያያዝ ይቀደዳል” እንዲሉ አነጋገራችን ጣዕም ያለው መሆን አለበት ። ወፎች ሌሎችን ከቀሰቀሱ በኋላ ዝም ይላሉ ። ሁልጊዜ መናገር ተገቢ አይደለም ። የሌሎችን ልብ ከማረክን ፣ በዓላማችን ብዙዎችን ካስከተትን በኋላ ዝምና ዞር ማለት አለብን ። ብዙ ከሠራን በኋላ ዝምታ ወሳኝ ነው ። ንግግር ሥራን ያበላሻል ። ራሱ ሥራው አፍ አውጥቶ ካልተናገረ አልሠራንም ማለት ነው ። ያልተሠራውን መሥራት እንጂ የሠሩትን ሲያወሩ መኖር ቆሜአለሁ መራመድ አልችልም እንደ ማለት ነው ።
የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ አለን ። ወፎች መምህራን ናቸው ። ንጽሕናቸውን ይጠብቃሉ ። ውኃ ሲያገኙ አያልፉትም ። እኛም በየጊዜው ንስሐ መግባትና ይቅር መባባል አለብን ። በቃሉ ውኃ ዘወትር መታረም ያስፈልገናል ። ወፎች ትጉሆች ናቸውና ክንፋቸውን ያበጥራሉ ። ይህ ለንጽሕና ብቻ ሳይሆን ለመበረራ ዝግጁ ያደርጋቸዋል ። በየዕለቱ ራስን በአካላዊና በሥነ ልቡናዊ ዝግጅት ውስጥ ማሳለፍ ያስፈልጋል ። ያለነው ጉብኝት ላይ ሳይሆን ብርቱ ጦርነት ናት በተባለችው ሕይወት ውስጥ ነው ። ወታደር ሲቀመጥ መሣሪያውን ይወለውላል ፣ ወፎች ክንፋቸውን ያበጥራሉ ። አማኝም ራሱን ለመንፈሳዊ ትግል ያዘጋጃል ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 19 ቀን 2019 ዓ.ም.