የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትሕትና መሠረት ነው። እርሱ ራሱን ዝቅ አድርጎ ወደ መጥምቁ ዮሐንስ ሄደ። መጥምቁ ዮሐንስም ራሱን የሚያስቀምጥበት እስኪያጣ እኔ የጫማውን ጠፈር ልፈታ አይገባኝም አለ። የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ትሕትናን ይማራሉ። ስለዚህ መምህራቸው እንዳዘዛቸው ጌታችንን ተከተሉ። ከሁለቱ አንዱ ዮሐንስ ወንጌላዊም የእንድርያስን ስም ጠቅሶ ራሱን ግን ሰወረ።  ተስፋ ቆርጠው በኤማሁስ መንገድ ላይ ይጓዙ የነበሩት ሁለት ደቀ መዛሙርትን እናስታውሳለን። ሉቃስና ቀለዮጳ ናቸው። ሉቃስ ግን ጸሐፊው እርሱ ነውና ራሱን ሰወረ /ሉቃ. 24፡13-18/። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም እስከ ሦስተኛ ሰማይ ተነጥቆ ሲመለስ አንድ ሰው እያለ ራሱን ሰወረ እንጂ የራእዩ ባለቤት እኔ ነኝ አላለም /2ቆሮ. 12፡2-5/። ብዙ የተቀደሱ ጽሑፎች ጸሐፊዎቻቸው ራሳቸውን በመሰወራቸው የእገሌ ናቸው የእገሌ እያልን እንድንመራመር አድርገውናል። በርግጥ ይህ በሦስት መንገድ ነው። መጀመሪያው ጽሑፉ ክብር እንዲያገኝ በአንድ ትልቅ ሰው ስም ያደርጋሉ። ሌላ ጊዜም ተቃዋሚዎቻቸው ተጨማሪ መቃወሚያ እንዳያገኙ ስማቸውን ይሰውራሉ። ከዚያ በላይ ግን ባለቤቱ እኔ አይደለሁም ለማለት ለትሕትና ይህን ያደርጋሉ። የሰው ጽሑፍ ተሰርቆ የእኔ ተብሎ የሚታተምበት  ይህን ዘመን ስናስብ በዚያ ትሕትና ፊት መቆም ይችል ይሆን? እንድንል ያደርገናል። ምን ያህልም ከትሕትና እንደ ራቅን እንረዳለን።
ለትሕትና ዝቅ የሚያደርገን የጌታችን ተግባር ነው። እርሱ ሥራውን ሁሉ በትሕትና ፈጸመ። ንጉሥ ወንበር ትተው መሬት ላይ ቢቀመጡ ወንበሩን የሚቀማ ሰው አይኖርም። ሁሉም ራሱን የሚከትበት ጉድጓድ እስኪያምረው የበለጠ ዝቅታ ይመኛል። የሰማይ የምድሩ ጌታ ራሱን ዝቅ አድርጎ ሲታይ ትሑት ያደርገናል። በገለጥናቸው ትሑታን ውስጥ የትሕትናን ትርጉም እናገኛለን፡-
    ትሕትና ማለት በሚያንሱን ለመገልገልና ለመማር ፈቃደኛ መሆን ነው።
    ትሕትና ማለት ከምሰጠው የምቀበለው ይበዛል ብሎ ማሰብ ነው።
    ትሕትና ማለት እውነተኛ ታዛዥ ሆኖ ክርስቶስን መከተል ነው።
    ትሕትና ማለት ስለ ራስ ከመናገር መቆጠብ ነው።
መጥምቁ ዮሐንስ የጌታችንን መሥዋዕትነቱንና ትሕትናውን ለመግለጥ እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ። በግ ትሑት ነውና /ዮሐ. 1፡29 ቊ. 36/። የእግዚአብሔር በግ መሆኑን ለሁለተኛ ጊዜ መሰከረ። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር በግ መሆኑን መግለጥ ብዙ ቋሚዎችን ይነካል፡-
 
1-  ለአይሁድ መርዶ ነው፡- የዮሐንስን ነቢይነት መቀበል አቅቷቸው ይከራከሩ ለነበሩት አይሁድ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ በማለት ነገራቸው። የሚያንሰውን መቀበል ሲያቅታቸው የሚበልጠውን ነገራቸው። የመቅደሱ ሥርዓት የመሥዋዕቱ ሕግ እንደሚያበቃ አረዳቸው። በርግጥም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከተሠዋ በኋላ ዐርባ ዓመት የንስሐ ዘመን ተሰጣቸው። እነርሱም ሊመለሱ ስላልቻሉ እነርሱና መቅደሳቸው ተደመሰሱ። ከ70 ዓ.ም. እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶችን አቅርበው አያውቁም። ይህ የሚያሳየን የጌታችን መሥዋዕትነት አሸንፎ መቆሙን ነው። መሥዋዕቱ በፈቃድ ላልተቀበሉትም በግድ አሸንፎ ቆሟል።
 
2-  ለኃጢአተኞች ተስፋ ነው፡- ለመጥምቁ ዮሐንስ እየተናዘዙ የንስሐ ጥምቀት ይወስዱ የነበሩ ብዙ ኃጢአተኞች ኢየሱስ የእግዚአብሔር በግ መሆኑን ሲሰሙ በኃጢአታቸው ለዘላለም እንደማያዝኑ በመሥዋዕቱ ግን ለዘላለም እንደሚደሰቱ የሚገልጥ ነውና ተስፋቸውን ያለመልማል። የታመሙ የመድኃኒት ድምፅ ሲሰሙ ጆሮአቸው እንደሚነቃ ኃጢአተኞችም ስለ አዳኙ ሲሰሙ ልባቸው በዕረፍት ይሞላል። 
 
3-   ለዮሐንስ መጥምቅ ደስታ ነው፡- ዮሐንስ መጥምቅ የአባቱን የዘካርያስን ወንበር ቢወርስ ሊቀ ካህናት ይሆናል። የሚያቀርበው ግን የማያድኑ መሥዋዕቶችን ነው። ተስፋውን ከማገልገል ፍጻሜውን ለማገልገል በቃ። ምሳሌውንም ከማገልገል እውነቱ ለመግለጥ በቃ። የክርስቶስ መንገድ ጠራጊ አልሆንም ብሎ ሊቀ ካህናት ቢሆን በክርስቶስ መምጣት ዘመኑን ይጨርስ ነበር። ስለዚህ ያለቀውን የብሉይ ኪዳን አገልግሎት ትቶ የአዲሱ ኪዳን አገልጋይ ሆነ። እግዚአብሔር ሲጠራን የተጠራንበት ስፍራ አገልግሎቱን የጨረሰ ስፍራ ነው። ቀረብኝ ብለን እንዳንቆጭ፣ ለጌታዬ ይሆን ተውኩለት ብለን እንዳንመካ አስጨርሶ ይጠራናል። ከመጨረሻው ይጀምራል።
 
4-  ለዮሐንስ ደቀ መዛሙርት የልብ ሙላት ነው፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበግ መልክ መገለጡ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ልባቸውን ይሞላል። እስከ ዛሬ የሚያስከትሉ አዝማቾች የሚገድሉ ናቸው። እርሱ ግን የሚሞት ነው። እንዲህ ያለ የማይጎዳን ጌታን መከተል የልብ ሙላት ነው። ስለዚህ ዮሐንስ እነሆ የእግዚአብሔር በግ ማለቱ ስነግራችሁ የነበረ ይኸው መጣ የሚል የናፍቆትና እርካታ ደግሞም እመኑኝ ድምፅ ያለው ሲሆን በአራት አቅጣጫ ላሉ አራት ዓይነት መልስ አለው፡-
·       ለትምክሕተኞች ፍርድ። እርሱም የተመኩበትን መፍረስ ነው
·       ለተነሣህያን ስርየት
·       ለአገልጋዮች ደስታ። ስለ ብዙዎች ስብራትና መንከራተት ያዝናሉና።
·       ለደቀ መዛሙርት የልብ ሙላት
 በዮሐንስ ወንጌል ስለ በግ ተጠቅሷል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር በግ መሆኑ ተነግሯል። በዮሐ. 5፡2 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበጎች በር መግባቱ ተገልጿል። ይህ በር በቤተ መቅደሱ ለመሥዋዕት የሚቀርቡ በጎች የሚገቡበት ሲሆን የቤተ ሳይዳ መታጠቢያም ታጥበው ለመሥዋዕት ብቁ የሚሆኑበት ነበር። ጌታችን ለዘመናት በዚህ በር የሚጓዙትን ነገር ግን ድኅነት ሊፈጽሙ ያልቻሉትን ብዙ በጎች ሳያስብ አይቀርም። በሰው በር አልገባም። በዚያ በር የሚገቡ መሥዋዕት የሚያቀርቡ ነበሩ። እርሱ ግን መሥዋዕት የሚሆን ነውና በበጎች በር ገባ። በርግጥም ዮሐንስ እንደ መሰከረው የእግዚአብሔር በግ በበጎች በር ገባ። በዮሐ. 10 ላይም እኛን በጎች ያሰኘናል። ሕይወቱን ብቻ ሳይሆን ስሙን ያካፍለናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡-
    በግ ተብሎ በጎች /ዮሐ. 1፡29፤10፡7/
    እረኛ ተብሎ እረኞች /ዮሐ. 10፡11፤የሐዋ. 20፡28/
    ብርሃን ተብሎ ብርሃን /ዮሐ. 8፡12፤ማቴ. 5፡14/
    መቅደስ ተብሎ መቅደስ /ዮሐ. 2፡19፤1ቆሮ. 3፡16/
    መሥዋዕት ተብሎ መሥዋዕት /ዕብ. 12፡24፤ሮሜ. 12፡1/
    የማዕዘን ራስ ድንጋይ ተብሎ ሕያዋን ድንጋዮች /ኤፌ. 2፡20፤1ጴጥ.5፡5/
    ነቢይ ተብሎ ነቢያት /ማቴ. 21፡11፤ኤፌ. 4፡11/
    ሐዋርያ ተብሎ ሐዋርያት /ዕብ. 3፡1፤ኤፌ.4፡11/
    ካህን ተብሎ ካህናት /ዕብ. 4፡14፤ 1ጴጥ. 2፡9/
    ንጉሥ ተብሎ ነገሥታት /ራእ. 19፡16፤ 5፡10/
    ልጅ ተብሎ ልጆች /ዕብ. 1፡5፤ 1ዮሐ. 3፡1/
    ክርስቶስ ተብሎ ክርስቲያን አሰኝቶናል /ሉቃ. 2፡11፤ የሐዋ. 11፡26/።
 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግ የተባለው በአዲስ ኪዳን ብቻ አይደለም። ነቢዩ ኢሳይያስ መሥዋዕትነቱን ለማስረዳት፡- “ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም” ብሏል /ኢሳ. 53፡7/። በዚህ ገለጻ ጌታችን በየዋህነት ገዳዮቹን መከተሉን፣ ከመብት ጥያቄና ከእኔነት ነጻ እንደሆነ፣ ማጉረምረም እንዳላሳየ ያስረዳል። ነቢዩ እንደ ተነበየው እንዲሁ ሆነ።
በመጨረሻም፡- “ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው” ተብሏል /ራእ. 19፡9/። ከሁሉ በላይ፡- “በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ”  ይላል /ራእ. 5፡6/። አንድ በግ ሲታረድ ይወድቃል እንጂ አይቆምም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የታረደ በግ ቢሆንም የቆመ፣ ሞትን ያሸነፈ ነው። የዕለተ ዓርብ ስቅለቱንም ስናይ መውደቅ የሌለበት መቆም ነው። እጆቹን ዘርግቶ እንደ ብራና ተወጥሮ ቀጥ ብሎ ቆሟል። እርሱ ሞትን ድል የነሣ የትንሣኤ ጌታ ነውና የቆመው በግ፣ ነባቢው/ተናጋሪው/ መሥዋዕት ነው /ዕብ. 12፡24/።
በአገራችን የነገሥታት ልማድ አንድ ንጉሥ ሲሞት የሚነገረው አዋጅ  “የሞትነውም እኛ፣ ያለነውም እኛ ባለህበት እርጋ” የሚል ነው። መንገሥ የሚያምረው ካለ ልቡ እንዲያርፍ ነው። የሞተውም እርሱ፣ የተነሣውም አማኑኤል ነውና ባለንበት እንርጋ።
የታረድከውም አንተ፣ የቆምከውም አንተ ነህ። ምስጋና ይድረስህ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ