የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምን ትፈልጋላችሁ?

“ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት። ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ፡- ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው” /ዮሐ. 1፡37-38/።
ዮሐንስ መጥምቅ ኋላ ወንድሙን ያዕቆብን የሚያመጣውን ዮሐንስን፣ ኋላ ወንድሙን ጴጥሮስን የሚያመጣውን እንድርያስን ክርስቶስ የእግዚአብሔር በግ መሆኑን ነገራቸው። ዮሐንስ መጥምቅ ክርስቶስ የመሥዋዕቱ በግ መሆኑን ወደ ዓለም የመጣበት ዓላማ ለቤዛነት ወይም ስለ ሌሎች ለመሞት መሆኑን አስቀድሞ ነገራቸው። ለምን ይህን መናገር አስፈለገው? ስንል ሥጋዊ ክብርን ተስፋ አድርገው ከተከተሉት እንዳይከስሩና የጌታችንንም አገልግሎት እንዳያውኩ ነው። ሥጋዊ ነገርን ብቻ ተስፋ አድርጎ ወደ እግዚአብሔር የሚመጣ በራሱ ይከስራል፣ የእግዚአብሔርንም ቤት ይወካል። ጠባዩም ቁጠኛና ኃይለኛ ይሆናል። ዮሐንስ መጥምቅ የሚናገረው የወደፊቱ ታይቶት ነው። በጌታችን ደቀ መዛሙርት መካከል የነበረው የዘወትር ክርክር ከመካከላችን ትልቅ ማነው? የሚል ነው /ማቴ. 18፡1-4/። ያስጨንቃቸው የነበረው የዚያች ሰዓት ትልቅ ሳይሆን ክርስቶስ ሲነግሥ ማነው ራስ፣ ማነው ደጃዝማች የሚሆነው? የሚለው ነው። ይህ አሳብ በጣም ከገዛቸው መካከል አንዱ ዮሐንስ ወንጌላዊና ወንድሙ ያዕቆብ ነበሩ /ማቴ. 20፡20-28/። ነገሩ እንዲከብድ ብለውም እናታቸውን ልከው ክርስቶስ ሲነግሥ የቀኝና የግራ ሥልጣንን ለምነዋል።
ይህ ክርስቶስ በበግ መልክ መምጣቱን መጥምቁ ዮሐንስ አስቀድሞ የነገራቸውን መርሳት ነው።  እግዚአብሔር በቤቱ ውስጥ ወደፊት ለምናሳየው ጠባይ፣ ለምንፈተንበትና ሌሎችንም ለምንፈትንበት ፈተና በመጀመሪያው ቀን መመሪያና ማሳሰቢያ ይሰጠናል። ብዙ ጊዜ ስለምንረሳው ግን የመጀመሪያውን ቀን ማሳሰቢያ ስንሽረው እንኖራለን።
ደቀ መዛሙርት ጌታችን ከሞት ከተነሣ በኋላ እንኳ በምድራዊ ዙፋን ይቀመጣል፣ እኛም ከእርሱ ጋር እንከብራለን ከሚል ስሜት አልተላቀቁም ነበር። “ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?” በማለት ጠይቀውታል /የሐዋ. 1፡6/። መንፈስ ቅዱስ እስኪወርድ ድረስ እከብር ባይ ልብ ገዝቷቸው ነበር። መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ ግን ከዚህ ቀንበር ተላቅቀዋል። መንፈስ ቅዱስ ዓለምን የሚያስንቅ ኃይልን ይሰጣል። ስለዚህ ዮሐንስ መጥምቅ እነሆ የእግዚአብሔር በግ በማለቱ ሁለት ነገሮችን ገልጦላቸዋል፡- የመጀመሪያው፡- አስቀድሜ ስነግራችሁ የነበረው ይኸው መጣ፣ በቃል ለነገርኳችሁ ሁሉ ማኅተሙ እርሱ ነው የሚል ደስታ ሲሆን ሁለተኛው ግን ከምድራዊ ምኞት ርቃችሁ ከክብር ጥማት ተላቅቃችሁ ተከተሉት ማለቱ ነው። ውኃ በተጓዘ ቊጥር ይጠራል። ሰውም በኖረ ቊጥር እየተለወጠ ይመጣል። እግዚአብሔርም እስኪለወጡ ይታገሣል። ይህ በደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ተከናወነ።
የዮሐንስ መጥምቅ ደቀ መዛሙርት የነበሩት ዮሐንስና እንድርያስ እነሆ የእግዚአብሔር በግ የሚለውን ድምፅ ሰምተው ጌታን ተከተሉት። ትሑታን ደቀ መዛሙርት ሳያንገራግሩ የመምህራቸውን ቃል የሚያዳምጡ ናቸው። ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ነበሩት። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ደቀ መዛሙርት ነበሩት። አገልግሎት የሚቀጥለው በደቀ መዛሙርት ነው። ደቀ መዛሙርት ከቀን ተማሪዎች የሚለዩት ከመምህራቸው ከቃሉ ብቻ ሳይሆን ከኑሮው የሚማሩ ናቸው። መምህራቸው ለሚገጥመው የሕይወትና የአገልግሎት ትግል ከሚሰጠውም ምላሽ ይማራሉ። አገልግሎት ቀጣይ የሚሆነው በቀን ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በአዳሪ ተማሪዎች ነው። አገልግሎት ቀጣይ የሚሆነው በትርፍ ጊዜ አገልጋዮች ብቻ ሳይሆን በሙሉ ጊዜ አገልጋዮችም ነው። ዛሬ እነዚህ ሁለት ነገሮች አደጋ እየገጠማቸው ነው። ደቀ መዛሙርት እየተመናመኑ ነው። የኢንተርኔት ተማሪዎች እንጂ የእጅና የእግር ውኃ የሚያቀርቡ ደቀ መዛሙርት እየጠፉ ነው። በዘመናዊ መገናኛዎች መማር መልካም ነው። ደቀ መዝሙር ለመሆን ግን ብዙ ትግሎች ይኖሩታል። ምክንያቱም ደቀ መዝሙር ከጉባዔ በኋላ መምህሩን በግል የሚጠይቅ፣ መምህሩን በቅርበት ሆኖ የሚያግዝ ነው። ደቀ መዝሙር ለመሆን በርቀትም በአሳብና በምክር እየተደጋገፉ ይቻላል። የአገራችን የቆሎ ተማሪዎች ለመምህራቸው በየመንደሩ ለምነው ያበሉ ነበር። ዛሬ ካለው ሀብት ላይም የሚያበላ ከተገኘ መልካም ነው።
ሁለተኛው የቤተ ክርስቲያን አደጋ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እየተመናመኑ መምጣታቸው ነው። የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች እየጠፉ ሲመጡ የትርፍ ጊዜ አገልጋዮች ይኖራሉ። እነዚህ አገልጋዮች ሥራቸው እስካልተጫናቸው ድረስ ብቻ ይገኛሉ። በዚህ በትልቁ የሚጠየቁት ምእመናን ናቸው። እግዚአብሔር ከሰጣቸው ላይ በሚገባ አሥራት በኩራት መስጠት ባለመቻላቸው አገልጋዮች እንጀራ ፍለጋ ይሰደዳሉ። በትርፍ ጊዜያቸው ባገለገሉ ቊጥር ከድካምና ከመባከን ወጥተው ስለሚያገለግሉ የጠራ መልእክት አያመጡም። አገልጋዮች የማይጠፋውን ሲሰጡን እኛ ደግሞ የሚጠፋውን ደመወዝ ልንቆርጥላቸው ይገባል። ስለ አምባሳደር ደኅንነት የተላከበት አገርና ሕዝብ ተጠያቂ ነው። ስለ ክርስቶስ አምባሳደሮችም ተጠያቂዎች ምእመናን ናቸው።
በእውነት ደቀ መዛሙርቱን ስናስብ ምንም የማያውቁ የገሊላ ገበሬዎች ብቻ አድርገን ማሰብ የለብንም። ማንኛውም አይሁዳዊ ከሰባት ዓመቱ እስከ አሥራ ሁለት ዓመቱ የዕብራይስጥን ፊደልና የብሉይ ኪዳንን ንባብ ያጠናል። በሃይማኖት ትምህርቱ መግፋት ከፈለገ ትርጓሜንና የተለያዩ ትምህርቶችን እስከ ሃያ ዓመቱ አጥንቶ መምህር ወይም ረቢ ይባላል። ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ትምህርት ፈጽሞ መምህር የተባለ ሲሆን ቅዱስ ጴጥሮስ ግን እስከ አሥራ ሁለት ዓመታቸው ተምረው በተግባረ ዓለም ከሚሰማሩት ውስጥ የሚመደብ ነው። የጌታችን ደቀ መዛሙርት የሆኑት አብዛኞቹ ቢያንስ ስድስቱ ደግሞ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት የነበሩ ናቸው። ደቀ መዛሙርቱ ለክርስቶስ የተዘጋጀ ማንነት ነበራቸው። ለምሳሌ ቅዱስ ጴጥሮስ የብሉይ ኪዳን እውቀት እንደነበረው እየጠቀሰ ከተናገራቸው ማየት እንችላለን /የሐዋ. 1፡15-20፤2፡16፤ቊ. 35/።
ጌታችን የዮሐንስ መጥምቅን ድምፅ ሰምተው እየተከተሉት ላሉ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው። አስቀድሞ ዮሐንስ የእግዚአብሔር በግ እነሆ በማለት ያመለከታቸውን እንደገና የሚያስታውስ ነው። ምን እና ማን ልዩነት አለው። ምን ለቁሳቁስና ለዓለም እሴቶች የሚነገር ነው። ማን የሚለው ግን ሕይወት ላለው ነገር የሚነገር ነው። ስለዚህ ጌታ የሚፈልጉትን እንዲያጠሩ ይጠይቃቸዋል። ዛሬም ምን ፈልገን ነው ወደ እግዚአብሔር ቤት የመጣነው? ምን ፈልገን ነው አገልጋይ የሆነው ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ራሱን ክርስቶስን ካልፈለግን የእግዚአብሔር በግ መሆኑን መረዳት እንቸገራለን።
እነዚህ ደቀ መዛሙርት ግን የሰጡት መልስ እንዲህ ተጽፏል፡- “እርሱም፦ ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ ትርጓሜው መምህር ሆይ ማለት ነው” መኖሪያውን መጠየቃቸው ጉዳያችን ብርቱ ነውና በመንገድ አንነግርህም ማለታቸው ነው። ደግሞም ጥያቄአችን ብዙ ነውና በመንገድ አናቆምህም በማለት እርሱን ማክበራቸው ነው። መኖሪያን የሚጠይቅ ብርቱ ወዳጅነትን የሚፈለግ ነው። መኖሪያውንም የሚያሳይ ልቡን የከፈተ ወዳጅ ነው። ጌታም፡- መጥታችሁ እዩ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ” /ዮሐ. 1፡40/። ከጌታ ጋር ያሳለፉት አሥር ሰዓት ያህል ቢሆንም ዋጋ ያለው ሰዓት ነው። ነቢዩ፡- “ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ” ይላል /መዝ. 83፡10/።
እኛስ ምን ፈልገን መጣን?

ያጋሩ