የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እውነተኛ ስጦታ

“ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ” /ዮሐ. 1፡41/።
መጥምቁ ዮሐንስ የክርስቶስን ታላቅነት ገለጠ። ክብሩ ከክርስቶስ ክብር እንደሚበልጥ የሚያስቡ ነበሩና እኔ የጫማውን ጠፈር እንኳ መፍታት አይቻለኝም አለ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቻ የሌለው በመሆኑ ከእርሱ ቀጠሎ የሚባልለት ተቀራራቢ የለበትም። የእግዚአብሔር ባሕርይ ብሑተ ሕላዌ ወይም ብቻውን ነዋሪ ነው /1ጢሞ. 1፡17፤ 6፡16፤ ሮሜ. 16፡27/። አንዳንድ ጊዜ ክርስቶስን አንደኛ የሚል ስያሜ ሲሰጠው እንሰማለን። አንደኛ ግን ተቀራራቢ ሁለተኛ አለበት። እርሱ ግን ብቻውን ኃይለኛ ነው። በእርሱ ታላቅነት ፊት ፍጥረት ሁሉ እንደ እንግጫ ዝቅ ዝቅ ይላል። እንደ ሕጉ ቢሆን ዮሐንስ በምድረ በዳ የሚጮህ ሳይሆን በመቅደስ የሚሠዋ ነበር። ብቻውንም የሚኖር ሳይሆን በካህናትና በሚራዱ ሌዋውያን ተከብቦ የሚኖር ነው። ክርስቶስን ግን ያገኘው በሞቀው መቅደስ ሳይሆን ጭው ባለው በረሃ ነው። ዮሐንስ በክህነት መንገዱ ቢሄድ ኖሮ ኃጢአትን የሚያዳፍኑ መሥዋዕቶችን ያቀርብ ነበር። አሁን ግን ኃጢአትን የሚያስወግደውን በግ ሰበከ። ዮሐንስ ወደ እርሱ የሚመጡትን ወደ ጌታችን ይመራ ነበር። ይህ እምነት ነው። ይስሐቅ ወደ አብርሃም መጣ፣ አብርሃምም ወደ እግዚአብሔር ሸኘው። መልሶ አገኘው። ሰዎች የእኛ ወይስ የክርስቶስ ወዳጅ ናቸው? የእኛ ወዳጆች የክርስቶስ ወዳጆች ላይሆኑ ይችላሉ። የክርስቶስ ወዳጆች ግን የእኛ ወዳጆች መሆናቸው አይቀርም። እርሱ የሚያስተምረው ፍቅርን ነውና።
ዮሐንስ በታላቅ ቅድስና የኖረ ነው። ነገር ግን በመጨረሻ አንገቱ ተቆረጠ። ትልቅ ደግነት ትልቅ መከራ ሊያመጣ ይችላል። እውነተኛ ደግነት በመከራ ውስጥም የሚቀጥል ደግነት ነው።
ዮሐንስ የእግዚአብሔር በግ በማለት ለአይሁድ፣ ለተነሣህያንና ለደቀ መዛሙርቱ ተናገረ። በብሉይ ኪዳን ብዙ ሺህ መሥዋዕቶች ቀርበዋል። ነገር ግን ምሕረት አልተገኘም። ሰሎሞን እንኳ በመቅደሱ ምርቃት ቀን በአንድ ቀን 22ሺህ በሬዎችንና 120 ሺህ በጎችን አቅርቧል /1ነገሥ. 8፡63/። በእነዚህ ሁሉ መሥዋዕቶች ግን የሰማይ ደጅ ሊከፈት አልቻለም። ወይ ከገንዘባቸው ወይም ከመልሱ አልሆኑም። በዚህ ሁሉ ድካማቸው ግን የሚያጽናናቸው ክርስቶስ እንደሚመጣ ማሰባቸው ነው። በዚህ ዓለም ላይ የብክነት በጀቶች ይኖራሉ፣ የምንረጋው ግን ክርስቶስን ስናገኝ ነው። ከብዙ ሙከራዎችና ትርምሶች የሚያድነው ክርስቶስ ነው። ትላንት እንደ ፈረሰኛ ወንዝ ይጋልብ የነበረው ኃጢአት በክርስቶስ ታገደ፣ ዛሬም እንደ ፈረሰኛ የሚጋልበውን መከራ ክርስቶስ በምጽአቱ ይገድበዋል። ዮሐንስ ይህን መልካም መፍትሔ፣ ይህን መልካም ገበያ፣ ይህን መልካም ማትረፊያ፣ ይህን መልካም ወዳጅ ለደቀ መዛሙርቱ አሳያቸው። የእጁን ቀስት ተመልክተው ጌታን ተከተሉት። ጌታም ምን ትፈልጋላችሁ? በማለት እርሱ በመፈለግ መከተል እንዳለባቸው ተናገረ። እርሱ ሁሉንም ያፈቅራል፣ ከወደደ መጥላት አይሻም። ግን ማንንም አያባብልም። ሰዎች ዋጋ ተምነው እንዲከተሉት ይፈልጋል። ዮሐንስ ከዚህ በኋላ ይጣላል ማለት አይደለም። የሚጮህ ሰው የሚጮህለት ነገር ሲደርስ ያርፋል። ዕረፍት ያገኛል። እግዚአብሔር ማንንም ተጠቅሞ አይጥልም።
አራቱም ወንጌላት ስለ ደቀ መዛሙርቱ ጥሪ በተለያየ መንገድ ዘግበዋል። ጌታን ወስነው ለመከተል የዮሐንስ መጥምቅ ትምህርት፣ ጌታ ያሳያው ተአምራት፣ የዮሐንስ ጥቆማ፣ የእንድርያስ ጥሪ አስተዋጽኦ አድርገዋል። “ሰዓቱ ሲደርስ አምባ ይፈርስ” እንዲሉ ሰዓቱ ደርሶአልና ድምፅ በዛባቸው። ተአምራት አዩ። ጌታን እሺ ብለው የተከተሉባት ያች ቀን ግን የተለወጡባት ቀን ናት። የጌታችን ደቀ መዛሙርት የተለያየ ስብጥር ነበራቸው። የነገድ ስብጥራቸው ከአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ነበር። የመጀመሪያይቱ ማኅበር እስራኤል በአሥራ ሁለቱ ነገድ ተመሠረተች። አዲሲቱ ቤተሰብ ቤተ ክርስቲያንም በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አእማድነት ተመሠረተች።
ተራ ቊ.
ስም ዝርዝር
ልዩ መጠሪያ
ነገዳቸው
ዕድሜአቸው
ቀረቤታቸው
መልእክታቸው
1
ጴጥሮስ
የዮና ልጅ፣ ስምዖን፣ ኬፋ
ሮቤልና ስምዖን
ሽማግሌ
የእንድርያስ ወንድም
1ኛ ና 2ኛ ጴጥሮስ
2
እንድርያስ
ሮቤልና ስምዖን
ሽማግሌ
የጴጥሮስ ወንድም
3
ያዕቆብ
የዘብዴዎስ ልጅ
ይሁዳና ሌዊ
ወጣት
የዮሐንስ ወንድም
4
ዮሐንስ
ወንጌላዊ፣ ፍቊረ እግዚእ
ይሁዳና ሌዊ
ወጣት
የያዕቆብ ወንድም፣ የእንድርያስ ጓደኛ
አንድ ወንጌል ሦስት መልእክታት፣ አንድ የራእይ መጽሐፍ
5
ፊልጶስ
ዛብሎን
ወጣት
የናትናኤል ጓደኛ
6
በርተሎሜዎስ
ንፍታሌም
ወጣት
7
ቶማስ
ዲዲሞስ
አሴር
ወጣት
8
ያዕቆብ
ወልደ እልፍዮስ፣ የጌታ ወንድሞች ከተባሉት አንዱ፣ ታናሹ ያዕቆብ
ጋድ
ወጣት
የይሁዳ ወንድም
የያዕቆብ መልእክት
9
ማቴዎስ
ሌዊ፣ ቀራጩ
ይሳኮር
ወጣት
የማቴዎስ ወንጌል
10
ታዴዎስ
ልብድዮስ፣የያዕቆብ ወንድም የተባለው የጌታ ወንድሞች ከተባሉት አንዱ
ዮሴፍ
ወጣት
የያዕቆብ ትንሹ ወንድም
የይሁዳ መልእክት
11
ናትናኤል
ቀነናዊው ስምዖን
ይሁዳ
ወጣት
የፊልጶስ ጓደኛ
12
ይሁዳ/በምትኩ ማትያስ
የአስቆሮቱ ይሁዳ
የማትያስ ነገዱ ዳን
ወጣት
   ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አብዛኛዎቹ ዘመዳማቾች ናቸው። ጴጥሮስና እንድርያስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ፣ ያዕቆብና ይሁዳ ወንድማማቾች ናቸው። ይልቁንም ትንሹ ያዕቆብና የአስቆሮቱ ያይደለው ይሁዳ የጌታ አብሮ አደጎች ናቸው። ፊልጶስና ናትናኤልም በጣም የሚዋደዱ ባልንጀሮች ናቸው። ፊልጶስ ባይወደው ኖሮ ወደ ክርስቶስ አያመጣውም ነበርና። የሚቀራረቡ ዘመዳማማቾችን ያደረገው ለሰላማቸውና ለኅብረታቸው ነው። አብሮ አደጎች መሆናቸውም አንዱ የአንዱ ጠባይ እንዳይከብደው ያደርጋል። ዛሬም የዘመድ ቄስ አጠገባቸው ያደረጉ ብዙ አይጠቁም። ሐዋርያት የተለያየ የሥራ ጠባይና አቋምም ነበራቸው። ስድስቱ ቢያንስ ዓሣ አጥማጅ ናቸው። ትንሹ ያዕቆብና ይሁዳ አናጢዎች ይሆናሉ። ማቴዎስ ቀራጭ ነው። ናትናኤል ቀነናዊ ቀናተኛ ነው። እስራኤል ከሮማውያን ባርነት ነጻ የምትወጣው በትግል ነው በማለት የአርበኞች አባል ነበር። በሙያቸው መሠረት ቢሆን ማቴዎስ ሒሳብ ያዥ ይሆን ነበር። በእግዚአብሔር ቤት ከሙያችን ጸጋችን ተፈላጊ ነው።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ