የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሕይወት ምንጭ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ሰኞ የካቲት 21/2008 ዓ.ም.
ወንጌላዊው ዮሐንስ፡- “ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” ያለውን አይተናል፡፡ በሕይወት ውስጥ ከሚያስደስቱን ነገሮች፣ መራራውን ከምናጣጥምባቸው አቅሞች አንዱ ከእግዚአብሔር እውቀት ያመለጠ ምንም ነገር እንደሌለ ስናስብ ነው፡፡ “ለምን እንዲህ ሆነ?” “ለምን ዝም አለ?” እንላለን፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር በእርሱ እውቀት ውስጥ እንዳለፈ ስንረዳ ለምን ሆነ? ማለታችንን እናቆማለን፡፡ የሚሆኑት ነገሮች  ሁሉ እግዚአብሔር ሳይችል ቀርቶ የሆኑ አይደሉም፡፡ እግዚአብሔር እያወቀና እየቻለ እንደሆነ ሲገባን ጠያቂው ልባችን ዕረፍትን ያገኛል፡፡ የእርሱ እውቀት ልብን ይደግፋል፡፡ የሚታየውና የማይታየው ዓለም አስገኚ እግዚአብሔር ነው፡፡ ግኝት ሁሉ አስገኚ አለው፡፡ ሁሉ በእርሱ ሆኗል፡፡ እርሱ ግን በማንም አልሆነም፡፡ የተወለደ እንጂ የተፈጠረ አይደለም፡፡ እርሱ ሠሪ የሌለው ሠሪ፣ ጌታ የሌለው ጌታ ነው፡፡ ጎድሎበት እገሌ ይሞላልኛል ብሎ ማንንም ተስፋ አያደርግም፡፡ ሄደን፣ ሄደን መቆሚያ ከሌለ ፍለጋ አያልቅም፡፡ ወደ ኋላም ወደፊትም መቆሚያው እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ አልፋና ኦሜጋ ነውና፡፡ ሁሉ በእርሱ ሆነ ሲል ለሁሉም ነገር መልስ የለውም የሚል ጥቅስ በውስጣችን ያስተጋባል፡፡  የሁሉም ነገር መልስ እግዚአብሔር ነው፡፡
ይህ ዓለም ባለቤት ያለው ዓለም ነው፡፡ ባለቤት ዳግመኛ ሲመለስ ስለ ቤቱ መዝረክረክ ይቀጣል፡፡ የጌታ ዳግመኛ መምጣትም ለዚሁ ነው፡፡ ይህ ዓለም ጥሪ ደርሶት በስድስት ቀን እንደ መጣ ትእዛዝ ደርሶትም በቅጽበት ያልፋል፡፡ ሲያሳልፈውም ክስረት አይደርስበትም፡፡ ጸጋ በረከቱ ራሱ ነውና፡፡ ዓለማትን ያደራጀው የእግዚአብሔር ቃል ክርስቶስ ነው፡፡ ይሁን ሲል ሁሉ የሚሆንለት እርሱ ብቻ ነው፡፡ ባንችልም ሁሉን የሚችል አምላክ አለን፡፡
“ሁሉ በእርሱ ሆነ”ሲል ከበደል በኋላ የሆነው ክፋት ጥፋት ሁሉ በእኛ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በዓለም ላይ የምናየው ጥፋትና ጉስቁልና የኃጢአት ውጤት ነው፡፡ ሁሉ በእርሱ ሆነ ሲል የቁስ መገኛው ቁስ ነው የሚሉትን ድል የሚነሣ ትምህርት ነው፡፡ ሁሉ በእርሱ ከሆነ በሁሉም ነገር ውስጥ የእርሱ ዓላማ አለ ማለት ነው፡፡ ዛሬ የምናየው ቴክኖሎጂ ካለ መኖር ወደ መኖር የመጣ ሳይሆን እግዚአብሔር በታትኖ ያስቀመጠውን ነገር የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ባገኘው እውቀት ሰበሰበ ማለት ነው፡፡ ስለ ዛሬው ቴክኖሎጂም ምስጋናውን መቀበል አለበት፡፡ ያማ ባይሆን ሐኪም ቤት መሄድም መድኃኒት መውሰድም ጣኦት አምልኮ በሆነብን ነበር፡፡ ያለ ጥቅም የተፈጠረ አረም የመሰለን ነገር የለም፤ አጠቃቀሙ ስላልገባን ነው፡፡ የሁሉም ነገር አስጀማሪ እርሱ ነው፡፡ የጊዜ ፈጣሪ፣ የታሪክ መሪ እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህ የምናየው ውስብስብ ፍጥረተ ዓለም ና ሲባል ለምን? ሳይል እንደ መጣ ሂድ ሲባልም ወዴት? ሳይል ይሄዳል፡፡ “ሆነ” የሚለው ቃል እርጋታንና ጸጥታን ያሳያል፡፡ ሁን እንዳለው ያልሆነ ማንም የለም፡፡ ሰውና ከፊል የመላእክት ወገን ብቻ ሁኑ እንዳላቸው አልሆኑም፡፡ ቢሆንም ሁን ያለውን አይለውጥምና እንደገና ሊፈልገን መጣ፡፡ ፍጥረት የረጋው በዚህ ጠባዩ ነው፡፡ አሊያ ሰው ሲበድል ሰውን ድንጋይ እያደረገ ድንጋዩን ሰው ያደርገው ነበር፡፡
ወንጌላዊው በመቀጠል፡- “በእርሱ ሕይወት ነበረች ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች”ይላል /ዮሐ. 1፡4/፡፡ ለእጽዋት የልምላሜን፣ ለእንስሳት የእንቅስቃሴን፣ ለሰው የዘላለማዊነትን ሕይወት የሰጠ እርሱ ነው፡፡ ሕይወት መኖር፣ መንቀሳቀስና ለግብ መብቃት ነው፡፡ የእርሱ ሕይወት ለዚህ ሁሉ ህልውና መሠረት ነው፡፡ መነሻችን፣ መንቀሳቀሻችን፣ ግባችን እርሱ ነው፡፡ ከዚህ ሕይወት ውስጥ ለሰው የሚወጣ ብርሃን አለ፡፡ እርሱም የእውነት እውቀት ነው፡፡ ሕይወትን ያገኘነው በአፉ እስትንፋስ ነው፡፡ በእኛ ውስጥ ያስቀመጠው እስትንፋሱን ነው፡፡ ያለ እርሱ መኖር የማንችለው ለዚህ ነው፡፡ ዛሬ ሞት እንዳለብን እናውቃለን፣ መሞት እንዳለብን ግን አንቀበልም፡፡ ምክንያቱ ይህች እስትንፋስ ከእግዚአብሔር ዘላለማዊነት የተሰፈረች መሆኗ ነው፡፡ ሞት ጣልቃ የገባብን ጉዳይ እንጂ የተፈጠርንበት ዓላማ አይደለም፡፡ ኃጢአትም ሆነ ሞት የባሕርያችን አይደሉም፡፡ ባሕርያችንን የጎዱ ነገሮች ናቸው፡፡
ጠቢቡ፡- “በአፉ መሳም ይሳመኝ፥ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ መልካም ነውና” ብሏል/መኃ. 1፤2/፡፡ ይህ የአፍ መሳም በዘፍጥረት 2፡7 ላይ ያለውን፡- “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ” የሚለውን ያስታውሰናል፡፡ ያ እስትፋስ ሰውን ከአፈርነት ያነሣ፣ ለገዢነት ያበቃ ነው፡፡ ጌታችን በአፉ መሳም በእስትንፋሱ፣ ከጭቃ ማንነት እንዲያነሣው ወይም እንደገና እንዲፈጥረው እየለመነ ነው፡፡ የዛሬ የአፉ መሳም ቃሉ ነው፡፡ በየቀኑ ከአፈር ቀና የሚያደርገን ይህ እውነት ነው፡፡ጌታችን የመጀመሪያ ቀን የመጨረሻውን ስጦታ ይሰጠናል፡፡ በወልድ ያመንን ቀን የዘላለም ሕይወትን ይሰጠናል /ዮሐ. 3፡36/፡፡ በእኛ ዓለም ስጦታ አዳጊ ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን የመጨረሻውን ይሰጠናል፡፡ በክርስቶስ ካመንን በኋላ ምንም ብንከስር የማይደንቀን የመጨረሻው ስለ ተከፈለን ነው፡፡ የመጨረሻው የተከፈለው ቢያገኝ ቢያጣም ምንም አይጠቅመውም፡፡ ቢሰደብ ቢመሰገን የመጨረሻው ተከፍሎታልና ምን ይሆናል ብላችሁ ነው?
እግዚአብሔር መነሻ የሌለው ዘላለማዊ ሲሆን ሰው ደግሞ መነሻ ያለው ዘላለማዊ ነው፡፡ ተፈጥሮ እንዳልተፈጠረ መሆን አይችልም፡፡ ህልውናው በገነት አሊያም በሲኦል ይቀጥላል፡፡ ለዚህ ነው ዛሬ እግዚአብሔርን መምረጥ ያለበት፡፡ በእግዚአብሔር ትዕግሥት ፍጥረት  ረግቷል፡፡ ሰው ሰው ሆኖ የቀጠለው እግዚአብሔር ስለ ታገሠ ነው፡፡ ሕይወት ያለው የሚንቀሳቀሰው በብርሃን ነው፡፡ ያ ሕይወት ሌጣ አይደለም፤ በውስጡ ለሰው የሚሆን የመንፈስ ብርሃን አለው፡፡ እውነት ያንቀሳቅሳል፡፡ እውነትን ያወቀ ሲንቀሳቀስ ይገኛል፡፡ ያ እስትፋስ የሚዳብረው በብርሃን ነው፡፡ ያለ ብርሃን ይቅርና በከፊል ብርሃን እንኳ መንቀሳቀስ እንፈራለን፡፡ ብርሃን ሂደት ሳይሆን ክስተት ነው፡፡ ቤታችን ገብተን የምናበራው የተደበቀ ነገር እንዲታየን ሳይሆን ለራሳችን ብለን ነው፡፡ የክርስቶስ ብርሃን ያስፈለገን ሌሎችን ለመመዘንና ለማቃለል ሳይሆን ለራሳችን ነው፡፡
ጸጋው ያግዘን፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ