ቍጣን ለማብረድ
ቍጣችን ሊናቅ እንደሚችል ማሰብ
ንቀት ሰዎች እያለን እንደሌለን ሲቆጥሩን ነው ። በአካል አለን ፣ እንደ ዕቃ መታየታችን ፤ እንናገራለን ነገር ግን እንደ ሬድዮ ድምፅ መቆጠራችን ፣ እናዛለን ነገር ግን የሚፈጽም ማጣታችን ፣ እንመክራለን ነገር ግን የሚተገብር አለመኖሩ ፣ እናስጠነቅቃለን ነገር ግን ምን ታመጣላችሁ በሚል ስሜት ሰዎች ሲንጎራደዱ ፣ እንቆጣለን ነገር ግን የውሸት መደንገጥ እያሳዩን ወጣ ሲሉ የሚስቁብን ከሆነ ንቀትን እያስተናገድን ነው ። ንቀት በተለያየ መንገድ ሊመጣ ይችላል ። ቃሉን የማይጠብቅ ሰው ይናቃል ። ራሱን የማይጠብቅ ከንጽሕና የጎደለ ሰው ይናቃል ። ዝሙትና ሱስም ንቀትን ያስከትላሉ ። ከአጉል ባልንጀሮች ጋር መታየትም ንቀትን ያመጣል ። ብዙ መናገር ፣ ብዙ መቆጣት ንቀትን ይወልዳል ። ከልክ በላይ ሰዎችን መቅረብ ፣ የማይችሉትን ምሥጢር መንገር የንቀት መነሻ ይሆናል ። ያለንን ነገር ሁሉ ፍጹም ገልጦ ማሳየት ፣ የትዳራችንን ምሥጢር ለደካማ ሰዎች ማውራት ንቀትን ያመጣል ። ስህተታችንንና ውድቀታችንን ላልበሰሉ ሰዎች መንገር ንቀት ያመጣል ።
ንቀትን ልናሸነፍ የምንችለው የመጀመሪያ ቁም ነገረኛ ሰው በመሆን ነው ። ለሚያከብሩን ሰዎች ቅድሚያ መስጠት ፣ አክባሪዎቻችንን ማክበር እርሱ ንቀትን ያስወግዳል ። ፉከራን ትቶ ማድረግን መለማመድ ንቀትን ያርቃል ። ሁልጊዜ አፍ ለአፍ ከመገጣጠም ፣ የቃላት ምልልስ ከማድረግ አንድ ቀን ቁጭ ብሎ በወሳኝነት መንፈስ መነጋገር ንቀትን ያርቃል ። ሐሜትን አርቆ ጉዳዩን ለሚመለከተው ሰው መንገር ንቀትን ያጠፋል ። ለራስ ክብር መስጠት እርሱ ትዕቢት ሳይሆን የመረጥነው የኑሮ ደረጃ ነው ። ንጹሕ ፣ የምንናገረውን ቃላት የምንመርጥ ፣ የብልግና ጨዋታዎችን የምንጸየፍ ፣ አጉል ቦታ የማንገኝ ፣ ለሚሰድቡን ምላሽ የማንሰጥ ከሆንን ክብራችንን እየጠበቅን እንመጣለን ። ሚዲያዎችን ማዘውተር አንድ ቀን የዘመናትን ካብ የሚንድ ስህተት ይወልዳል ። ቁጥብ ሆኖ መኖር ፣ ባልንጀራ አለማብዛት ፣ በየሰው ቤት አለመዞር ፣ አክብሩኝ እያሉ አለመታገል ፣ ብልጥ አለመሆን ያስከብራል ። ብልጥ ሰው በጣም የተናቀ ነው ። ሕፃን ሳይቀር ብልጠቱን ያውቅበታልና ሁሉ ይሸሸዋል ።
ቍጣችን በሁሉ ነገር ፣ በሁሉ ቀን ከሆነ “ጀመረው” እንባላለን ። ሰዎች የመዝናኛ መርሐ ግብርን በሬዲዮ እንደሚሰሙት ያህል ቍጣችን እንደዚያ የሚሰማ ይሆናል ። ዝምታችን ፣ አይተን ማለፋችን ሰዎች ራሳቸውን እንዲመረምሩ ሊያግዛቸው ይችላል ። ቍጣችን ዘላቂ ከሆነ ወደ ኩርፊያ ይለወጣል ። ሰላማችን እየታወከ ፣ ደስታ እያጣን ፣ መቆያ ስፍራችን እያስጠላን ይመጣል ። ሰዎችም ስህተታቸውን ከመረዳት በእኛ ቍጣ ውስጥ መደበቅ ይጀምራሉ ። የቍጣችን ተጎጂዎች እርስ በርስ በመቧደን መጣ መጣ እያሉን ፣ አንዱ እየጠበቀ አንዱ ይሰርቃል ። አንዱ እየበደለ አንዱ ይከራከርለታል ። በቤታችን አጉል ፍቅር እንዲጀመር ፣ ገለልተኛ ሰዎች እንድንሆን ፣ በምናስተዳድረው ስፍራ ባይተዋር እንድንደረግ ይሆናል ። ቍጣችንን ማባከን የለብንም ። መድፍ አለኝ ተብሎ ለቁንጫ የታንክ ጥይት አይተኮስም ። ለሚረባውም ለማይረባውም ነገር ኃይልን መጠቀም ጉልበትን ይጨርሳል ፣ ቶሎ ያደክማል ፣ ዕድሜን ያሳጥራል ፣ ደስታን ይጋፋል ። እንኳን ሰዎች የገዛ ሥራችን እኛኑ እያስቆጣን የምንኖር ነው ። ጠብን ካልናቅን ፣ አለፍ ካላልን ራሳችንን እየመረዝን ለመኖር ወስነናል ማለት ነው ። ከብልጦች ፣ ከራስ ወዳዶች ፣ ወሬን ከሚያመጡ ፣ ሆዳቸውን ከሚፈቅሩ ሰዎች ጋር ያለንን ኑሮ ቶሎ ማሰብ መልካም ነው ። ብልጥ ሰው እኔ እንጂ ሌላው አያውቅም ብሎ የሚያስብ ነውና ሊማር አይችልም ። ራስ ወዳድም በሌሎች ሞት ላይ የሚኖር ፣ ራሱ ጣዖት የሆነበት ነው ። ወሬን የሚያመጣ የሰላማችን ጠላት ነው። ሆዱን የሚወድ ፈጣሪውን የሚክድ ፣ ይሉኝታ የሌለው ፣ መናቁ የማይገባው ፣ ጨካኝ ነው ።
ቍጣችን ቱግታ ሲሆን ቍጣችን መንገድ ማሳየት ሲያቅተው ይናቃል ። በምን እንደ ቀጣናቸው ልጆች ካላወቁ አይታረሙም ። ስለ ተናደድን ብቻ መጮኽ ለውጥ አያመጣም ። ያጠፉትን ነገር በትክክል መንገር ያስፈልጋል ። ቍጣችን ብቻ ሳይሆን ተቆጥተን መብረዳችን እንዲሁም ይቅርታ ማድረጋችን ሊያስተምራቸው ይገባል ። ቍጣችን ጠባይ እንዳይሆንብን ፣ አታካች ሰዎችም የቍጣ ጠባይን እንዳይሰጡን ቶሎ መወሰን አለብን ። ገንዘባችንን ከሚሰርቅ ሌባ አመላችንን የሚሰርቅ አልምጥ እርሱ ትልቅ ቀማኛ ነው ። የገንዘብ ሌባስ የሰረቀውን ይጠቀምበት ይሆናል ፣ ቅንነታችንን የሰረቀን ሰው ቅን መሆን አይችልም ። ቅንነትን የሚሰርቁ ፣ ትዕግሥትን የሚፈታተኑ ሰዎች በዓለም ላይ ክፉዎች እንዲበዙ ያደርጋሉ ። ቍጣዬ ሊናቅ ይችላል ብሎ መታገሥ ቍጣን ለማብረድ ከሚረዱ ነገሮች አንዱ ነው ።
ይቀጥላል
መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም.