ዕድገት/21
ያደገ ሰው መገለጫ
አይሆንም ሲባል ደስ ይለዋል
ስናድግ የተገነዘብናቸው ነገሮች ብዙ ናቸው ። ወላጆቻችን በሰጡን ነገር ብቻ ሳይሆን በከለከሉን ነገር ውስጥም ፍቅራቸው ሕያው መሆኑን ተረድተናል ። ሲከለክሉን ከፍቶን ፣ አልቅሰን ነበር ። እነርሱም ከዘለቄታው ሞታችን ጊዙያዊ ልቅሶአችንን መርጠው ከልክለውናል ። ቢለቁን ኖሮ ዛሬ የለንም ነበር ፣ ልቅሶ ግን አይገድልምና ዛሬ አለን ። ዛሬ ላይ በራሳችን አለማወቅ ስናፍር በወላጆቻችን እውቀትና ጥበቃ እንደነቃለን ። ትላንት ያናደዱን ባለማወቃችን ነው ፣ በሚመሰገኑበት ርእስ ተበሳጭተንባቸዋል ። በሕይወት ውስጥም እግዚአብሔር በሰጠን ነገር ብቻ ሳይሆን በከለከለን ነገሮችም መደሰት የምንችለው ስናድግ ነው ። ለምን አልሆኑም ? ብለን እግዚአብሔርን አኵርፈን ፣ ከቤተ እግዚአብሔር ርቀን ፣ አገልጋዮቹን ሳይቀር ጠልተን ነበር ። አሁን ላይ ግን እንኳን አልሆኑ ብለን ደስ ይለናል ። ያልሆኑት ስለማይጠቅሙን ነው ። የፈለግነው ሁሉ ቢሰጠን ኖሮ በሕይወት አንኖርም ነበር ። አንዳንድ ጊዜ የምንወዳቸው ሰዎች ሕመም እኛን ወደ ንስሐ ሕይወት ይጠራናል ። የልጁ ጉዳት ፣ የሚስቱ ሕመም ፣ የቤተሰቡ ችግር ፍጹም መንፈሳዊ ያደረገው ሰው ብዙ ነው ። እግዚአብሔር በሁሉ የሚናገር ከሆነ በችግር ውስጥም ይናገራል ። ሁልጊዜ የሚኖሩ መስለውን ችላ ያልናቸው ወዳጆቻችን ሲሞቱ ልባችን ይሰበራል ። ወደ እግዚአብሔርም መንገዳችንን እናቀናለን ። አንዳንድ ችግሮች ራሳችንን እናገኝባቸዋለን ። ለማግኘት ማጣት መንፈሳዊ ሕግ ነው ። አንድ ነገርን ስናገኝ አንድ ነገርን አጥተናል ማለት ነው ። በእግዚአብሔር ለማመንም ራስን መካድ ግዴታ ነው ።
አዳም የተከለከለውን ነገር ቢያከብር ኖሮ ዛሬ የምናየውን የግፍ ምድር ፣ ስቃይ ያለበትን ኑሮ አናተርፍም ነበር ። ኃጢአታችን በክርስቶስ ደም ቢሻርም የኃጢአት ውጤት የሆኑት ነገሮች ዛሬም ድረስ እያወኩን ነው ። በተከለከለ ነገር ውስጥ ያለ ጥፋት መቆሚያ የለውም ። ይልቁንም እግዚአብሔር የተፈጥሮአችን ምንጭ ስለሆነ እርሱ የከለከለን ነገር ሰውነታችንን የሚጠብቅ ነው ። እርሱ የከለከለንን ነገር ስናደርግ ኢኮኖሚያችን ፣ ጤናችን ፣ ሰላማችን ፣ ማኅበራዊ ግንኙነታችን ፣ አስተዳደራችን መታወክ ይጀምራል ። መከልከል ለጊዜው ያሳዝናል ፣ ቆይቶ ግን ደስታ ይሰጣል ። ስናድግ የምንገነዘበው ነገር እግዚአብሔር ፍቅሩን የገለጠው በከለከለን ነገር ውስጥ እንደሆነ ነው ። በሰጠን ነገር ውስጥ ባለጸጋነቱን ሲገልጥ ፣ በከለከለን ነገር ውስጥ ግን ጥበቃውን ፣ እንደ ዓይኑ ብሌን እኛን መንከባከቡን ነው ። የሚነካችሁ ስለሚነካኝ እከለክላችኋለሁ ፣ ጣጣችሁ ስለሚተርፈኝ ፣ ኀዘናችሁ ስለሚያሳዝነኝ ፣ ውድቀታችሁ ስለሚያባዝነኝ አይሆንም እላችኋለሁ የሚለው ድምፁ አሁን እየተሰማን ነው ።
ያ ግንኙነት መፍረስ አልነበረበትም ። ሰው የካበው ግን የእምቧይ ካብ ነውና ይናዳል ። የገነባው እጅ ሳይመለስ ካቡ መፍረስ ይጀምራል ። ሳንተዋወቅ እንናናቃለን ፣ አንድ ቀን ተገናኝተን እንተዛዘባለን ፣ እንገናኛለን የሚል ቃል ሰጥተን ላለመገናኘት በውስጣችን እንወስናለን ። ይልቁንም ያለንበት ዘመን ፍቅርም ጠብም ያለቀበት ዘመን ነው ። ሰዎች በመረሳሳት አንዱ አንዱን ይተዋል ። ይህ ዘመናዊነት ሆኗል ። ስልኩን አትደውል አይልም ፣ ስልክ አላነሣም ብሎም ቅያሜውን አይገልጥም ። አንሥቶ “እባክህ ወንድሜ ቆይቼ ልደውል?” በማለት ላይደውል ይጠፋል ። ይህ ዘመናዊ ጠብ ነው ። ሰውዬው ድጋሚ ከደወለ አልሰለጠነም ፣ አልገባውም ይባላል ። በዚህ ሁሉ ፍቅርና ጠብ ባለቀበት ዘመን ግንኙነቶቻችን ባይሳኩ ብዙ ማዘን የለብንም ። በእጮኝነት ዘመን ላይ ማረም በትዳር ጊዜ ላይ ከማረም የተሻለ ነው ። ብዙዎች ትዳርን አስበው ሳይሳካ ቀረ ። ባለመሆን ውስጥም ያለውን ምሥጢር የምንረዳው ቆይቶ ነው ። ተቀጣጥረን ስላልተገናኘን እንበሳጫለን ፣ ተቀጣጥሮ መጣላትም አለና እንኳን ሆነ ማለት አለብን ። ዛሬ ምርምር ሲበዛ ምንም የሚጣል ነገር እንደሌለ እየተረዳን ነው ። የጣልናቸው ምግቦች ሁሉ ይቆጩናል ። እግዚአብሔር ለሚወዱት ሁሉን ለበጎ ያደርግላቸዋል ።
ብዙ ሰው ወደ መንፈሳዊ ሕይወት የሚመጣው በአብዛኛው ችግር ሰቅዞ ይዞት ነው ። በምንሰማው ውጣ ውረድ እናዝናለን ። ልባችን ይሰበራል ። እነዚያ ሰዎች እግዚአብሔር እንዲጎበኛቸው በብርቱ እንጸልያለን ። የሚፈልጉት በእጃቸው የገባ ቀን ግን ይክዳሉ ። ለምስጋና የሚመለስ ፣ በተሰጠው ነገር እግዚአብሔርን የሚያመሰግን ፣ አብረው ካለቀሱ ጋር ለደስታ የሚቆም የለም ። ብዙ መታዘብ እንችላለን ፣ ብዙ ነገሮችን ስለምናውቅ ፣ ለሰው መጸለይ እስክንፈራ ድረስ ሆነናል ። እግዚአብሔር ያንን ሰው ስለሚያውቀው ገመዱን እንዳሳጠረበት ቆይቶ ይገባናል ። አለመሳካት ሰውን የሚጠብቀው አጥር ነው ። አንዳንድ ሰው ፍላጎቱ ከተሟላ በሕይወት ላይኖር ይችላል ። ጥጋብን ማስተዳደር የማይችል ብዙ ሰው አለ ። ሕይወትን በኑሮ ለመለወጥ ሲነሣ እግዚአብሔር ሕይወቱን አትርፎለት ኑሮውን ያዝ ያደርግበታል ።
“በሬ ካራጁ ይውላል” ይባላል ። ከሚገድለን ምኞትና ምርጫ ጋር የምንኖር ነን ። ከጎረቤታችን ይልቅ ልባችን ሊያሳስበን ይገባል ። ጎረቤት ቢጣላን ከአምላክ አይለየንም ፣ የውስጣችን ፍላጎት ግን ይለየናል ። ሰው ትልቅ ጠላቱ ያለው ካጠገቡ ሳይሆን ከውስጡ ነው ። እርሱም ክፉ ልብ ነው ። ክልከላው ለምን እንደሆነ ገብቶን ምስጋና ብንጀምር ያልታሰበ ነገር እግዚአብሔር ያደርግልናል ። ውስን እውቀታችን በፍጹሙ እውቀት ሲታረም ግን ደስተኛ መሆን አለብን ። ያደገ ሰው ወዳጁ እንኳ ሲሞት እኔ ጋ ይሻለዋል ብሎ እግዚአብሔር እንደ ወሰደው ያምናል ። ያ ሰው ቢቆይ ለሦስቱም አይጠቅምም፡- ለራሱ ፣ ለእኛና ለእግዚአብሔር ። ስናድግ አቤቱ ወደ አንተ የመጡትን አሳርፍ ፣ የእኔንም መንገድ አቅናው ብለን በደስታ እንጸልያለን ። የሚጎዳኝን ነገር ባልቅስም አትስጠኝ ። አሜን!
ይቀጥላል
ግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም.