የመጨረሻው ክፍል
ወንዶች ለወንዶች ከሚራሩት ይልቅ ለሴቶች ይራራሉ ፣ ሴቶችም ለሴቶች ከሚያዝኑት ይልቅ ለወንዶች ያዝናሉ ። መራራት ያለብን ለሰው እንጂ ለጾታ መሆን አይገባውም ። ርኅራኄ እንኳን ወዳጅን በችግሩ ቀን ጠላትንም ማለፍ የለበትም ። ርኅራኄ ሰው መሆናችንን ፣ ስሜት ያለን ፍጡራን እንደሆንን ፣ ከድንጋይ ከፍ ማለታችንን ፣ በድን አለመሆናችንን የሚገልጥ ነው ። መራራት በሕይወት አለሁ ማለት ነው ። ከሰው ጋር ያለን ኑሮ ውጤታማ የሚሆነው በእምነታችን ነው ። ሴት አይሆነኝም የሚሉ ሴቶች እንደ እምነታቸው ሊሆን ይችላል ። የጾታ እኩያችንን ከመሸሽ ማገዝ ተገቢ ነው ። ምክንያቱም በቀላሉ ስሜታቸውን መገንዘብ እንችላለንና ። ወንዶች እየተገናኙ ስለ ትዳራቸው ቢነጋገሩ ፣ ሴቶችም ከመሰሎቻቸው ጋር ስለ ኑሮ ቢያወጉ የተሻለ መፍትሔ ይመጣል ። ይኸውም የጋራ ስሜት ስለሚገኝ ችግሬ የሚሰማው ሰው አለ የሚል ደስታ ይፈጥራል ። አንዱ የደከመበት ሌላው የበረታበት በመሆኑ ድካማችንን ጥለን የማሸነፊያ ጥበብን እንማራለን።
ብዙ ወንዶች ከመሰሎቻቸው ይልቅ ከሴቶች ርኅራኄ ያገኛሉ ። ይበልጥ እናቶች ወንድ ልጅን በኑሮውም በሞቱም አይረሱትም ። ወንዶች ለተራበ ሌላ ወንድ ከመስጠት ለጠገበች ሴት መስጠትን ይመርጣሉ ። ወንዱን ተቸግሮ ሲያዩት ሠርቶ አይበላም ወይ ? ይላሉ ። የሚሠራውን ሥራ ግን ማቅረብ አይችሉም ። ወንድ ልጅ ቸገረኝ ሲል ርቦት ነው ብሎ ከማሰብ ሊጠጣበት ነው ብሎ ማሰብ ይቀለናል ። አብዛኛው ወንድ ወደ ወንጀል የሚገባው ከ20-30 ዓመት ባለው ዕድሜ ነውና ስህተቱ ያለ መብሰል ውጤት ነው ። ንቃትን በሚመለከት ሴቶች ከወንዶች የተሻሉ ናቸው ። ተገቢውና ጤናማው ፍርሃት ስላላቸው ሴቶች በብዛት ወደ ወንጀል አይገቡም ። ወንድ ልጅ ለቤተሰቤ ያለሁት እኔ ነኝ በሚል ሞራል ስለ ተፈጠረ የእናቱንና የቤተሰቡን ችግር ቆሞ ማየት ይከብደዋል ። ጭንቀቱም መፍትሔ ከመፈለግ ግብታዊ ውሳኔ እንዲወስን ያደርገዋል ። አንድ በስርቆት ወንጀል የታሰረ ወጣት በእስር ቤት አግኝቻለሁ ። ዓይነ ስውር እናቱ ርቦአቸው ሲያይ እንደ ሰረቀ ነግሮኛል ። በሰው አገር በረሃ ላይ የሚንከራተቱት ወጣት ወንዶች እናቴ እያሉ ሲናገሩ ይሰማል ። ፍቅራቸውን በሚያማምሩ ቃላት መግለጥ ስለማይችሉ ብዙዎቹ የሚከፍሉት ዋጋ አይነገርላቸውም ። በማዕድን ጉድጓድ ውስጥ መሬት ተንዶባቸው የሚሞቱ ወንዶች በጣም ያሳዝናሉ ። ለቤተሰባቸው የከፈሉት ዋጋ ነውና ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባ ነበር ።
በዓለም ላይ እርዳታ የሚያገኝ የሚያለቅስና ቸገረኝ ብሎ እሪ የሚል ነው ። ብዙ የማይናገሩና የማያለቅሱ ወንዶች ወደ ውስጣቸው እያለቀሱ በውስጣቸው እየተናገሩ እንደሆነ አምላክ ያውቀዋል ። በእጓለ ማውታ ወይም በሕፃናት ማሳደጊያዎች ላይ ሴቶችን የሚወስዱ በብዛት አሉ ። ወንድ ሕፃንን ግን የሚወስድ ጥቂት ነው ። ብዙ የተጣሉ ወንዶች በአገር ውስጥ ባሉ ሞግዚቶች የማደግ ዕድል እያጡ ነው ። ወንድ ልጆቻችንን የውጭ ዜጎች እንጂ የአገር ውስጥ አሳዳጊዎች እየወሰዱ አይደለም ። በዚህ በማሳደጊያ ቦታ ያደጉ ወንዶች ሥራ የሚቀጥራቸው አያገኙም ፣ ተያዥ ማግኘትም ይቸገራሉ ። ሰው ሥራ ለመቅጠር እንኳ ጀርባን ያያል ።
የወንዶች ችግር የሚጀምረው ገና በሕፃንነት ዕድሜ ነው ። ያለ ጥፋታቸው ንዴትን ለማብረድ መደብደብ በጥላቻ እንዲያድጉ ያደርጋቸዋል ። የእገሌን ልጅ አታይም ወይ? የሚል ንጽጽርም ግራ መጋባት ውስጥ እንዲገቡና ቀናተኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ። እንዲህ መማርና መሆን አለብህ የሚለው የግል ምርጫችን በአቅማቸው እንዳይሆኑ መሰናክል ይሆንባቸዋል ። ይህ ልጅ የእኛን ቤት አይመስልም የሚል ንግግርም እኔ ማን ነኝ ? እንዲሉ ያደርጋል ። እናቱን ያጣ ልጅ ሰባራና አልቃሻ ሲሆን አባቱን ያጣ ልጅ ግን ቁጠኛና ኃይለኛ ይሆናል ። ከቤት እቤት እየተንከራተቱ ማደግ ለወንዶች ገና በሕፃንነታቸው ብዙ ስቃይና ብዙ ኃጢአት እንዲያዩ ያደርጋቸዋል ። ቂምንና ዘረኝነትን ማስተማር የደስታ ጊዜአቸውን መብላት ነው ። ብዙ ወንድ ልጆች በዘረኝነት ስሜት እየተሰቃዩ እንዴት እንደሚያለቅሱ ይልቁንም ከክርስትና ጋር እየተጋጨባቸው እንደሚጸጸቱ አውቃለሁ ። በዘረኝነት ልጅን ማሳደግ ፍቅርን ሳይሆን ቂምን መጋት ነፍሰ ገዳይን ማሰልጠን ነው ። ነቀፋ ማንንም አያንጽም ። እየነቀፍንና እየሰደብን ያሳደግናቸው ግን እኛንም ማኅበረሰብንም እየጠሉ ያድጋሉ ። የማንነት ጥያቄ ያለባቸው ወንዶች ለተለያየ ሱስ ይዳረጋሉ ። የማንነት ጥያቄ ከውስጥ የሚነሣ ሲሆን መልሱን ቢያገኙት መልካም ነው ። ለክርስቲያን ግን ሥላሴን የሚያህል አባትና እናት እያለው ወላጅ የለኝም ብሎ የሚጨነቅ ከሆነ አላመነም ማለት ነው ።
ወንዶች የሚጠፉት በባልንጀሮች ነው ። በለጋነት ዕድሜ በሚበልጡአቸው ሰዎች ይለከፋሉ ። ካደጉ በኋላ በእኩዮቻቸው መሪነት ከመንገድ ይወጣሉ ። ሰው ውሎውን ይመስላል ። ሱስ የዚህ ዘመን ወረርሽኝ ነው ። ደስታን በሞት መፈለግ እርሱ ሱስ ይባላል ። ሁሉንም ነገራችንን የሚጎዳ ነገር ሱስ ነው ። ሰው ራሱ ምን አድርጎት ነው እንዲህ የሚቀጣው ? ብዙ ወንዶች ዕድሜአቸው ከ25 ዓመት ካለፈ በኋላ ብቻቸውን መኖር ወይም ትዳር መያዝ ይፈልጋሉ ። የትዳሩ ዘመን እየረዘመ ሲመጣ ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ ። ወደ ኑሮ ለመግባት ብዙ ወንዶች አቅም ማጣት እየታገላቸው ነው ። አለመብሰል ትልቁ የወንዶች ችግር ነው ። ለመብሰል ማንበብ ፣ መማርና አዋቂዎችን መጠየቅ ያስፈልጋል ። ገንዘብ አስፈላጊ ቢሆንም የኑሮ ዋስትና አይደለም ። ልካቸውን በማጣት የሚንከራተቱ ወንዶች ብዙ ናቸው ። ገንዘባቸውን ደግሞ ያዩታል እንጂ አይበሉትም ። ልብሳቸውን አይቀይሩም ፣ ልጆቻቸው ወርቅ ሲለብሱ ግን ደስ ይላቸዋል ። ግብታዊነትና የስሜት ውሳኔዎች ብዙ ወንዶችን ወደማያውቁት አገር እንዲሰደዱና በአገር ውስጥ ደግሞ በወንጀል ወኅኒ እንዲገቡ አድርጓቸዋል ። የትዳር አጋር ሲመርጡም መስፈርታቸው መልክ በመሆኑ ብዙዎቹ ተጎድተዋል ። ቁንጅና እስከ ትዳር እንጂ ለትዳር መቀጠል ዋስትና አይሆንም ። ብዙ ቆንጆ ፣ ቆንጆ ምግባር የለውም ። ጨካኝ ነገሥታት የወጡት ከተናጋ ትዳር ውስጥ ነው ። የወንዶች ጭካኔ መሠረቱ ቤተሰብ ላይ ያዩት ነገር ነው ።
ወደ ትዳር ከገቡ በኋላ በእናትና በሚስት መካከል የሚሰቃዩ ብዙ ወንዶች አሉ ። እናትን ከማረም ሚስት ብትታረም ዕድሜው ይረዝምለታል ። ከአስቸጋሪ ውሎ በኋላ ወደ ቤቱ ሲገባ ጭቅጨቅ የሚገጥመው ከሆነ ከባድ ነው ። ብዙ ወንዶች በጨዋነት ሲገቡ ጭቅጭቅ አለ ፣ ጠጥተው ሲገቡ ግን በእንክብካቤ ቶሎ ተኛ ይባላሉ ። በዚህ ምክንያት መጠጥ የሚያስከብራቸው ይመስላቸዋል ። ሚስቶች የማይረካ ፍላጎት ካላቸው ባሎች ሌባና ዕረፍት የለሽ ይሆናሉ ። ኑሮ ይበቃኛል ማለት ሁሉንም ነገር ማትረፊያ ነው ። ጦርነት ወንዶችን በጣም ይጎዳል ። አምራች ኃይልን ያሳጣል ። በሳውዲ ዐረቢያ ሞት የተፈረደባቸውና ቅዱስ ፓትርያርኩ ምሕረትን የለመኑላቸው ወጣቶች ጦርነትን ፈርተው የተሰደዱ ፣ በትንሽ ወንጀል ክርስቲያን ናቸውና ሞት የተፈረደባቸው ናቸው ። አልቃሽ፡- “ታሞ ታሞ ፣ ሞት አለ ወይ ደሞ!?” እንዳለችው ሞት ሲፈረድባቸው ማየት ያሳዝናል ። ወጣት የሌላት ፣ ወጣት የተገፋባት አገር የነገ ተስፋ የላትም ። ወንዶች ተማሩ ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔርን ተለማመዱ ፣ አዋቂዎችን ጠይቁ ! ተስፋ አድርጉ !
ተፈጸመ
ሰኔ 4 5 ቀን 2018 ዓ.ም.