መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የኃጢአት ስሞች » የኃጢአት ስሞች -1

የትምህርቱ ርዕስ | የኃጢአት ስሞች -1

የሰው ልጆች ኃጢአትን እንደ ግል ዝንባሌ ሊመለከቱት ፣ ስህተት ብቻ ብለው ሊያልፉት በብዙ ይጥራሉ ። ኃጢአትን የመሥራት ነጻነታቸው ውጤቱንም የመምረጥ ነጻነት እንዲሆንላቸው ብዙዎች ይመኛሉ ። ዘመናዊነት የኃጢአትን ትክክለኛ ስም ሊነግረን አይችልም ። ምሁራንና ፈላስፎች ፣ የሥነ ቋንቋ ተመራማሪዎች የኃጢአትን ፍቺ የማስረዳት አቅም የላቸውም ። ኃጢአትን በትክክለኛ ስሙ የሚጠራው እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ኃጢአት የእግዚአብሔርን ክብር መገዳደር በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮአችን የማይስማማ በመሆኑም መተው ይገባናል ። ሰው ለጽድቅ እንጂ ለኃጢአት አልተፈጠረም ። የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ተፈጥሮ ነበረ ፣ በምርጫው ግን ወደቀ ። ከዚያ በኋላ አዳም ልጆቹን በራሱ መልክና ምሳሌ ወለደ ። “አዳምም… ልጅን በምሳሌው እንደ መልኩ ወለደ” ይላል (ዘፍ. 5፡3) ። እንደ ምሳሌው የወለደው ቃየንም ወንድሙን አቤልን የሚገድል ሆነ ። የሰው ልጆች የተመቸ ኑሮ ቢገጥማቸው ኃጢአትን እንደማይሠሩ የሚያስቡ ሰዎች አሉ ። አዳም ግን የበደለው ወደር የሌለው ደስታ በነበረባት በገነት ነው ።

በቀስት የሚገድሉ ሰዎችን ሁሉም ሰው ኋላ ቀር ብሎ ያወግዛቸዋል ። በድሮን የሚገድሉትን ፣ በሚሳኤል የሚጨርሱትን ግን አወይ ሥልጣኔ ብሎ ያደንቃቸዋል ። መቀማት ኃጢአት ማታለል ግን ኃጢአት የማይመስለው ብዙ ወጣት አለ ። ዝሙትን ተፈጥሮ ነው ብሎ የሚያሞካሽ ሰው ፣ ወጣ ያለና እርሱ የማይሠራውን ስህተት የሚሠራውን ግን የሚያወግዝ ብዙ ነው ። ሰዎች ኃጢአት የሚሉት እነርሱ የማያደርጉትን ነው ። ሰው ሁሉንም ኃጢአት ሊፈጽም አይችልም ። ሰይጣን በአንዱ ደጋግሞ የሚጥለን ከሆነ በሌላው አይፈትነንም ። በስስት ሰው በረሀብ ሲሞት የምናይ ፣ የእግዚአብሔር ሥራ በገንዘብ እጥረት ሲታጎል የሚያስችለን ከሆነ ለሰይጣንን ትልቅ ግቡ ነውና በዝሙትም በስካርም አይፈትነንም ። ራስ ወዳድነትም ነፍሰ ገዳይነትም ሁለቱም ኃጢአቶች ናቸው ።

ኃጢአት የተለያዩ ስሞች ተሰጥተውታል ። “ዓላማ መሳት” የሚለው ትልቁ የኃጢአት ትርጉም ነው ። “ወዴት ነህ ?” ብሎ አዳምን የፈለገው ዓላማውን ስለ ሳተ ነው ። ኃጢአት ሩቅ እያዩ ቅርብ የሚያሳድር ነው ። መንግሥተ ሰማያትን እያሰቡ በምድር የሚያስቀር ነው ። ሰው ራሱን ስቶ ወደቀ ስንል ሚዛን አጣ ፣ ራሱን መሸከም አቃተው ማለታችን ነው ። ኃጢአት ራስን የሚያከስር ፣ ከራስ ጋር የሚያጣላ ነው ። “ለክፉዎች ሰላም የላቸውም” ተብሎ እንደ ተጻፈ በኃጢአት የሚኖሩ ሰዎች ሰላም የላቸውም (ኢሳ. 48፡22)። ቀኑን በመግደል ፣ ፍርድ በማጓደል ፣ በቅሚያ ፣ በማጭበርበር የሚውሉ ሌሊቱን በሙሉ በየመጠጥ ቤቱ ሲዘዋወሩ ያድራሉ ። ሰውን የሚያስተኛው በጎነቱ እንጂ ምቹ ትራሱ አይደለም ። በርግጥ እነዚህ ሰዎች ከራሳቸው ለመደበቅ መሞከራቸው ገና ሕያው የሆነ ነገር በውስጣቸው ስላለ ነው ።

ዒላማውን የሚስት ሰው ሁለት ነገሮች ያባክናል ። የመጀመሪያው ጥይት ያባክናል ፣ ሁለተኛው ያለበትን አድራሻ ለጠላት ያሳውቃል ።

አዳምና ሔዋን ጠፍቷቸው መንገዱ
ለሰው ልጅ መከራን ትተውለት ሄዱ ።

ይህ ግጥም ኃጢአት መቆም ሳይሆን መሄድ መሆኑን ግን ወደ ተሳሳተ ግብ መገስገስ እንደሆነ ያሳያል ። ሰው በሊፍት ወይም በአሳንሰር ላይ ተሳፍሮ ወደ ላይም ወደ ታችም ቢሄድ እየተጓዘ ነው ። ስላልቆመ እያደገ የሚመስለው ብዙ ሰው አለ ። ወይ በጽድቅ እያደገ ነው አሊያም በኃጢአት እያደገ ነው ። ባለበት የሚቆም ምንም ነገር የለም ። ዛፍ ወደ ታችም ወደ ላይም ያድጋል ። ሥልጣናቸው ፣ ተሰሚነታቸው ፣ ሀብታቸው ፣ ዝናቸው ፣ ተፈሪነታቸው ፣ የማስፈጸም አቅማቸው እያደገ ስለሆነ ከፍ ያሉ የሚመስላቸው ሰዎች ይኖራሉ ። በአብዛኛው የዚህ ዓለም ክብር ለሰይጣን በመስገድ የሚገኝ እንደሆነ ተጽፎአል (ሉቃ. 4፡6) ። ለዚህ ነው ብዙ የዓለም ገዥዎች ሕሊና ፣ ባለጠጎችም ጨዋነት ሲያጥራቸው የምናየው ። እያደግን ነው ፣ የቆመ ማንም ሰው የለም ። ወይ ወደ ታች አሊያ ወደ ላይ እናድጋለን ። ከተወለድን ጊዜ አንሥቶ እየሞትን ነው ። እንዲሁም ከእግዚአብሔር ከተወለድን ቀን አንሥቶ ለኃጢአትና ለዓለማዊ ምኞት እየሞትን እንመጣለን ። ኃጢአት ዓላማ መሳት ነው ። ሾፌሩ መንገድ ከሳተ የተሳፈረው ሁሉ አብሮ ይስታል ። አዳም ሾፌሩ ነበርና እርሱ ሲስት ሁላችንም አብረን ሳትን ። አንድ የአገር መሪ የሚናገረውን ስንሰማ በመላው ዓለም እኛም አብረን እየተናገርን ነው ። ምክንያቱም መሪ ራሱን ሳይሆን ሕዝብን የወከለ ነውና ። አዳም የእኛ መሪ ብቻ ሳይሆን ምንጭም ነው ። እርሱ ሲስት ልጆቹም በስህተት መንገድ ሄዱ ።

ብቻ ኃጢአት ዓላማን መሳት ነው ። ስንት ዘማርያን የነበሩ ፣ አገልጋይ የነበሩ በዓለማዊነትና በዘፋኝነት ስተዋል ። ከበደል በፊት የሚያስጠነቅቅ እግዚአብሔር ፤ የበደሉትን ደግሞ በንስሐ ሊቀበል ደጅ ደጅ ያያል ። እርሱ ይቀበለናል ።

ይቀጥላል

ሰኔ 10 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ