የመጨረሻው ክፍል
“የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት”
የሐዋ. 3 ፡ 15 ።
ከተማን የሚጠብቅ
ግሪኮች ከተማን የሚጠብቅ አምላክን አርኬጎስ ብለው ይጠሩት ነበር ። ያለ እግዚአብሔር ጠባቂነት የጥበቃ ጓዶች ከንቱ ናቸው ። የጠባቂዎች ጠባቂም መድኃኔዓለም ነው ። እርሱ የከተማው ጠባቂ ነው ። ተኝተን የሚጠብቀን ፣ ተዘናግተን የሚያሻግረን ፣ ረስተን የሚያስታውሰን ነው ። ከተማው የእርሱ ነውና በመተማመን መውጣትና መግባት ይኖርብናል ። የሰው ልጅ ቤቱን ለመሥራት ፣ ኑሮውን ለማዋቀር በብርቱ ይደክማል ፣ እግዚአብሔር በሥራችን ላይ ካልሠራበት ግን ሁሉም ነገር የእንቧይ ካብ ነው ። ሕይወትን ለማቆየት ብዙ የብልጠት መንገድ እንጠቀማለን ፣ ጥሪ ከመጣ ግን ብልሃታችን ሞኝነት ይሆናል ። እግዚአብሔር ሆይ ቤቴን ሥራ ብሎ መለመን ይገባናል ። ወደሚኖሩበት ከተማ መራቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ወደምኖርበት ምራኝ ብሎ መለመን ተገቢ ነው ። ብዙ ሰዎች እየኖሩ አይደለም ፣ የመኖር ርእስና ምኞት አላቸው ፣ መኖርንም በቁሳዊ ነገር ለውጠውታል ፣ የሚፈልጉትን ስለማያውቁ አግኝተውም ይፈልጋሉ ፤ ብዙዎች ገበታውን አንጥፈው ፣ ማዕዱን ዘርግተው ፣ ሰሐኑን አቅርበው ፣ ታጥበው ቀርበው ፣ ለመጉረስ ሲጠቀልሉ ዘመናቸው ተጠናቋል ። እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል ተብሏል ። የምንበላው የምንጠጣው ነገር ሁሉ ከእምነት ጋር የተያያዘ ነው ። ተመርዟል ስንል ንጹሕ ቢሆንም መርዝ ሁኖ ይጎዳናል ። የከተማው ጥበቃ ፣ የመኖር ዋስትናም ከእምነት ነው ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ስንሆን በተከበበ ከተማም ሰላም ይሰማናል ፣ አሊያ በሰላም ከተማም እንታወካለን ። ከተማን ለሚጠብቀው ከተማውን አሳልፎ መስጠት ይገባናል ። የሰው ጠባቂማ ራሱ ይገርፋል፣ ይዘርፋል ። ለጥበቃው ቅዱስ ተብሎ የሚጠራው አርኬጎስ የተባለው ክርስቶስ እርሱ ከእኛ ጋር ነው።
መንገድ ከፋች
መንገድ ሳለ አይታወቅም ፣ ሲዘጋ ግን ይናፍቃል ። መንገድን የሚከፍት ኃይልና ሥልጣን ያለው ነው ። መንገድን ከፍቶ ሂዱ እለፉ የሚል ባለሥልጣን አርኬጎስ ተብሎ ይጠራል ። ጌታችን መንገድን የከፈተ ብቻ ሳይሆን ወዴት እንደምንሄድ ግራ እንዳይገባን መንገድ የሆነልንም ነው ። መንገድን የሚከፍት ባለሥልጣን በደስታም በኀዘንም ጊዜ ይታያል ። መንገዱ ተሠርቶ እስኪያልቅ ድረስ ለመንገደኛ ዝግ ነው ፣ አዲሱን መንገድ መርቆ ሲከፍተው ከባለሥልጣኑ በኋላ ሕዝቡ ይተማል ። ድንበሮች ሲከፈቱ የሁለት አገር ነገሥታት ይገኛሉ ። ከዚያ በኋላ አእላፋት ይጓዛሉ ። በአዳም ኃጢአት የነፍስ መንገድ ተዘግቶ ፣ ገነትም ለወራሾችዋ ቁልፍ ሁና ነበር ። ፍርድ እስኪሰጥ ድረስ ንብረት ታግዶ እንዲቆይ ገነትም ታግዳ ነበር ። መስቀልን ዙፋኑ አድርጎ ዳኑ የሚል ፍርድን በሰጠ ጊዜ ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያት ተከፈተች ። ፈያታዊ ዘየማን የቀኙ ወንበዴ ደመ ማኅተሙን ይዞ የገነትን በር ጥሶ ገባ ። ደመ ማኅተሙን እንኳን ርኵስ መንፈስ ቅዱስ ኪሩብም መከልከል አልቻለም ። የደሙ ማኅተም ላላቸው መንገዱ ክፍት ነው ። መንገድ ዕድል ነው ፣ መንገድ ራእይ ነው ፣ መንገድ ዕድሜ ነው ። ይህን ሁሉ መንገድ የሚከፍተው በርግጥም አርኬጎስ የተባለው ክርስቶስ ነው ።
ሐዋርያው፡- “የሕይወትንም ራስ ገደላችሁት” ይላል ። ተጠያቂ ሳይሆን ተነሣሒ እያደረጋቸው ነው ። ባለቤቱ ይቅር ያላቸውን ሐዋርያው አይከስምና ። ሰው ግን ለኃጢአቱ ኃላፊነት መውሰድ አለበት ። መንፈሳዊነትም ፣ ማኅበራዊ ኑሮም ጸንቶ የሚቆመው ስህተትን በማመን ነው ። እርሱ የማይሞት ሕይወት ሳለ በለበሰው ሥጋ ሞተ ። ሞቱ ለጊዜው የተፈጸመ ሲሆን ትንሣኤው ግን ለዘላለም ይነገራል ። በራሱ ሕይወተ ባሕርይ ነዋሪ ነው ። መግደል ሲችል መሞቱ ይገርማል ። አምላክ ቢገድል አይደንቅም ፣ የአንድ አገር ንጉሥ ሞትን ቢፈርድ የሚገረም የለም ። አምላክ ለሰው ፍቅር መሞቱ ግን ይደንቃል ። የሕይወትን ራስ ከገደሉ ፣ የሕይወታቸውን ሕይወት ከገፉ ቀጥሎ ሟች ናቸው ። እህል ቢያንቅ በውኃ ይውጡታል ፣ ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡታል ? ገላ ቢያብጥ በምላጭ ይበጡታል ፣ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡታል ? “ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡ ፣ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ” እንዲሉ የሕይወትን ራስ ገድለው በምን ይኖሩታል ? ለእግዚአብሔር ቀንተው ሰው የሆነውን እግዚአብሔር ለመግደል ተነሡ ። ስሙን እየጠሩ ባለ ስሙን መቃወም እንዴት ያለ መታለል ነው ( የማይሞተው ሞተ ፣ መሞት የሚገባቸውን ሊያድን ሕያው ጌታ ሞትን ቀመሰ ። እርሱ የሕይወታችን አስጀማሪ ፣ የመንገዳችን ብርሃን ፣ የሩጫችን ግብ ነው ። ለእርሱም ለዘላለም ክብር ምስጋና ይሁን ።
ተፈጸመ
ሰኔ 24 ቀን 2018 ዓ.ም.